Back to Top
አምስተኛው የእምነት ማእዘን ማለትም በመጨረሻው ቀን ማመን አስመልክቶ በምን መልኩ ነው ማመን ያለብን?

ጥያቄ(25): አምስተኛው የእምነት ማእዘን ማለትም በመጨረሻው ቀን ማመን አስመልክቶ በምን መልኩ ነው ማመን ያለብን?
መልስ:

በመጨረሻው ቀን ማመን ማለት በቂያማ ቀን ማመን ማለት ነው። የመጨረሻው ቀን የተባለበት ምክንያት ከሱ ቀን በኋላ ሌላ የዱንያ ቀን ስሌለ ነው። የሰው ልጅ መጀመሪያ ካልነበረበት በእናቱ ማህፀን እንዲፀነስ ተደረገ ከዚያም ወደ ዱንያ መጣ፤ከዚያም ወደ ቀብር በርዘኽ እና ወደ ቂያማ ህይወት ይሸጋገራል። እነዚህ አምስት ሂደቶች ማንኛውም የሰው ልጅ የሚያልፍባቸው ሂደቶች ናቸው።

“በሰው ላይ የሚታወስ ነገር ሳይኾን ከዘመናት የተወሰነ ጊዜ በእርግጥ አልፎበታል፡፡” [አልኢንሳን:1]

ይህ የመጀመሪያው ሂደት ሲሆን ምንም የሚታወስ ነገር አልነበረም።  ከዚያም በእናቱ ማህፀን ተረግዞ ወደ ዱንያ መጣ።

“አላህም ከእናቶቻችሁ ሆዶች ምንም የማታውቁ ሆናችሁ አወጣችሁ፡፡” [አንነሕል:78]

ከዚያም ዱንያ ላይ ይለፋል፤ይሰራል።ከዚያም በዱንያና በቂያማ ቀን መካከል ወዳለው በርዘኽ ወደሚባለው አኼራ አገር ይሸጋገራል።ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ ዐቂደቱ አልዋሲጢያህ በተሰኘው መፅሓፋቸው ላይ በመጨረሻ ቀን ማመን አስመልክቶ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “በመጨረሻ ቀን ማመን ማለት፤ በአጠቃላይ ከሞት በኋላ የሚከሰቱ ነገሮችን  አስመልክቶ መልክተኛው የነገሩን ማለትም ቀብር ውስጥ ቅጣት እና ደስታ ተድላ፤የቂያም ቀን እንዳለ በቀንድም እንደሚነፋ፤ ምርመራ እንዳለ፤ስራዎች የሚሰፈሩበት ሚዛን እናዳለ እና የሱና ሰዎች ውሃ ለመጠጣት ወደ ሐውዱ እንደሚሄዱ … ባጠቃላይ አላህ በቁርኣን ወይም መልክተኛ በሐዲሳቸው ከሞት በኋላ ይሆናል በማለት የተናገሯቸው በሙሉ በመጨረሻ ቀን ማመን ከሚለው ርዕስ ስር የሚካተቱ ናቸው።

ስለ ቀብር ፈተና ትንሽ ሰፋ አድርገን ብናወራ ጥሩ ይመስለኛል። እርሱም አንድ ሟች ከተቀበረ በኋላ «ጌታህ ማን ነው? ሀይማኖትህ ምንድን ነው? ነብይህ ማን ነው? » የሚሉ ሶስት ጥያቄዎችን እንደሚጠየቅ በሐዲስ ተዘግቧል። አማኝ ከሆነ አላህ በማፅኛዋ ቃል ያፀነዋል። ስለዚህም አማኝ የሆነ ሰው “የአላህ ባርያና መልዕክተኛ እንደሆኑ እመሰክራለሁ” ብሎ ይመልሳል። አማኝ ያልሆነ ግን ሃ! ሃ! አላውቀም ሰዎች የሆነ ነገርን ሲሉ ሰምቼ እል ነበር ይላቸዋል። ከዚህ ፈተና በኋላ ቂያማዋ እስክትቆም ደስታ አሊያም ስቃይ ይሆናል። ሙስሊም ካልሆነ እስከ ቂያማ በቅጣት ይሰቃያል። ሙእሚ ሆኖ ወንጀለኛ የሆነ አላህ ብቻ የሚያውቀው ጊዜ ያህል ይቀጣል። ከዚያም ቅጣቱ ይነሳለታል፤ ይህ ቀብር ውስጥ የሚከሰተው ቅጣትም ይሁን ደስታ መሰረቱ በሩሕ ላይ ሲሆን ምናልባትም አካል ሩህን ተከትሎ ሊሰቃይ ይችላል። ዱንያ ላይ አካል ሲሰቃይ መንፈስም አብሮ እንደሚሰቃየው ማለት ነው።  ለምሳሌ ፦ ዱንያ ላይ ግርፋት ወይም ድብደባ አካል ላይ ሲከሰት የስቃዩ ስሜት አካል ላይ ቢሆንም ነፍስም የግርፋቱ መጥፎ ተፅእኖ ያርፍባትና ትሰቃያለች። ስለዚህም ነፍስ ታዝናለች፤ትጨናነቃለችም። ቀብር ውስጥ ያለው ግን በተቃራኒው ነው። ቅጣትም ይሁን ደስታ ሩህ ላይ ሲሆን ነገር ግን አካልም የደስታው ወይም የስቃዩ ተካፋይ ይሆናል።

ታላቁ ቂያማ ሲከሰት ደግሞ የሰው ልጆች ከቀብራቸው ጫማ የሌላቸው ራቆታቸውና ያልተገረዙ ሲሆን ይቀሰቀሱና ታላቁ የዓለማት ጌታቸው ዘንድ ይቆማሉ።እግራቸውን ከአደጋ የሚከላከልላቸው ጫማም ይሁን ኹፍ የላቸውም። ገላቸው ላይ ጣል የሚያደርጉት ጨርቅ እንኳ የላቸውም። የሰው ልጅ ከቀብሩ ሲወጣ በተሟላ አካሉ ይቀሰቀስ ዘንድ ዱንያ ላይ እያሉ ሲገረዙ ተቆርጣ የተጣለችው ቁራጭ ስጋ እንኳ ትመለሳለች። አላህ እንዳለው ማለት ነው።

“የመጀመሪያን ፍጥረት እንደ ጀመርን እንመልሰዋለን፡፡” [አልአንቢያ:104]

ከዚያም በቁርኣንና በሐዲስ ላይ እንደመጣው ሒሳብ ወይም ምርመራ ይከሰታል። ከዚያም በስተመጨረሻም ወደ ጀነት ወይም ወደ እሳት ይሆናል። ጀነት የገባ እስከ ዘላለም በውስጧ ይኖራል። ወንጀለኛ አማኝ የአላህ እዝነት ወይም ሸፈዓ ሳያገኝ ቀርቶ እሳት ውስጥ ከገባ ለወንጀሉ የሚገባውን ቅጣት ካገኘ በኋላ ከእሳት ይወጣል። እሳት ውስጥ አይዘወትርም። ካፊር ግን ዝንተ ዓለም እሳት ውስጥ ለዘላለም ሲቀጣ ይኖራል።
Share

ወቅታዊ