Back to Top

6/ተውሒድ ማለት ምንማለት ነው?

ተውሂድ ማለት ”ወሐደ” አንድ አደረገ፤ “ዩወሒዱ” አንድ ያደርጋል፤ ከሚለው የአረብኛ ስረውቃል የመነጨ ነው። ይህም ማለት አንድ ነገርን አንድ ማድረግ ማለት ሲሆን ይህ የሚረጋገጠው ”ኢስባት” በማጽደቅና “ነፍይ” ውድቅ በማድረግ ነው።

አንድ ተደርጎ ከተነጠለው አካል ውጭ ፍርድን ውድቅ ማድረግ። ስለዚህም አምልኮትን ከአላህ ውጭ ካሉ አማልክት ውድቅ አድርጎ ለአላህ ብቻ ማጽደቅ ይገባል። የሰው ልጅ ላ ኢላህ ኢለላህ ብሎ በመመስከር አምልኮትን ከአላህ ውጭ ካሉ አማልክት ውድቅ በማድረግ ለአላህ ብቻ ካላፀደቀ ተውሒዱ የተሟላ አይሆንም። ያለ ማፅደቅ ውድቅ ማድረግ ይህ ማራቆት ይባላል። ውድቅ ሳያደርጉ ማጽደቅ ብቻውን ሌላውን አካል እንዳያጋራ አይከለክልም።

ለምሳሌ ፦ እገሌ ቆሟል ብለህ ብትናገር  ሰውዬው መቆሙ አረጋገጥክ ማለት ነው። ነገር ግን መቆም በሚባለው ድርጊት እርሱን ብቻ አልነጠልከውም። ምክንያቱም ሌላውም አካል በዚህ ድርጊት ሊጋራው ይችላልና። “አልቆመም” ብለህ ብትናገር ደግሞ መቆም የሚባለውን ድርጊት ከሁሉም ውድቅ አደርግክ። በዚህም የተነሳ ለአንድም አካል መቆምን አላፀደቅክም ማለት ነው። ነገርግን ዘይድ እንጂ ማንም አልቆመም ስትል ዘይድ መቆም በሚባለው ድርጊት ነጥለሀዋል ማለት ነው። ከርሱ ውጭ ያሉ አካሎችን መቆም በሚባለው ድርጊት  ውድቅ ስላደረግክ።

ተውሒድን በተጨባጭ ማረጋገጥ ማለት ይህ ነው። ማለትም  ተውሒድ ተውሒድ የሚሰኘው “ኢስባት” ማጽደቅና “ነፍይ”(ውድቅ) ማድረግን በውስጡ ሲያካትት ብቻ ነው ።

8/የተውሒድ ክፍሎችን ከተጨማሪ ማብራሪያና ምሳሌዎች ጋር ቢዘረዝሩልን?

አላህን አስመልክቶ የተጠቀሱ የተውሒድ ክፍሎች በሙሉ ጥቅላዊ የተውሒድ ትርጓሜ ውስጥ ይካተታሉ። እርሱም አላህን ሱብሃነሁ ወተዓላ በሚነጠልበት እና ከፍጥረታቱ በሚለይበት ነገር ሁሉ ለይቶ ማምለክ ማለት ነው።የተውሒድ ክፍሎች ሦስት ሲሆኑ እነርሱም፦

አንደኛው ተውሒዱ ሩቡቢያህ ይባላል። እርሱም አላህን በመፍጠር በማስተዳደር እና በማስተናበር መነጠል ማለት ነው። አላህ ብቻውን ፈጣሪ ነው ከርሱ ውጭ ሌላ ፈጣሪ የለምና።

አላህ እንዲህ ይላል፦

“ከአላህ ሌላ ፈጣሪ አለን? ከሰማይና ከምድርም ሲሳይን የሚሰጣችሁ አለን?” [ፋጢር:3]
የከሃዲያን አማልክቶች ውድቅ መሆናቸውን ሲገልፅ አላህ እንዲህ ይላል፦ “የሚፈጥር እንደማይፈጥር ነውን? አታስተውሉምን?” [አን ነሕል:17]

አላህ ብቻውን ፈጣሪ ነው ሁሉንም ነገር ከፈጠረ በኋላ በልኩና በመጠን አደረገው። መፍጠር ሲባል የእርሱ እና የፍጥረታት ድርጊቶችን ያካተተ ነው። ለዚህም ሲባል በቀደር ማመን የተሟላ የሚሆነው አላህ የባሮችንም ድርጊት የፈጠረ መሆኑ ስናምንና ስናረጋግጥ ብቻ ነው። አላህ እንዳለው፦

«አላህ እናንተንም የምትሠሩትንም የፈጠረ ሲኾን፡፡» [አሷፋት:96]

ይህም የሆነበት ምክንያት የሰው ልጅ ድርጊቱ ከባህሪያቱ የሚመደብ ሲሆን የሰው ልጅ ደግሞ በአላህ ችሎታ የተፈጠረ ነው።አንዳችን ነገር የሚፈጥር ባህሪውንም ፈጣሪ እርሱ ነውና። ሌላኛው ደግሞ አንድ ሰው የሚፈፅመው ድርጊት በተሟላ ችሎታና በቁርጠኛ ውሳኔ ነው። ፍላጎትና ችሎታ ደግሞ ሁለቱም ፍጡር ናቸው። ቀጣዩ የቁርኣን አንቀፅ እንደሚጠቁመው መፍጠር ከአላህ ውጭ ላለ አካል ፀድቆ ሊመጣ ይችላል፦

“ከፈጣሪዎችም (ከቀራጮችም) ሁሉ በላጭ የሆነው አላህ ላቀ፡፡” [አልሙእሚኑን:14]

  እንዲሁም የአላህ መልክተኛ ሰዓሊያንን አስመልክቶ እንዲህ ብለዋል፦

“የፈጠራቹት ነገር ላይ ህይወት ዝሩበት ይባላሉ።”

ለዚህም መመሳሰል ምላሽ የሚሆነው ከአላህ ውጭ ያለ አካል መፍጠሩ እንደ አላህ አይሆንም የሚል ይሆናል። ምክንያቱም ሰዓሊ ያልነበረን ነገር ወደ መኖር አይቀይርምና። የሞተንም ሕያው ማድረግ ይሳነዋል። ከአላህ ውጭ ያለ አካል የተወሰኑ ለውጦችን ሲያስገኝ  ፈጠረ የሚል ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። ከአንድ ገፅታ ወደ ሌላ ገፅታ መለወጥ ግን ይህ የአላህ ድርጊት ወይም ፍጥረት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ለምሳሌ አንድ ፎቶ የሚያነሳ ሰው ፎቶ ቢያነሳ ምንም የፈጠረው ነገር የለም። እዚህ ላይ የመጨረሻ ሊባል የሚችለው ነገር ቢኖር አንድን ነገር ወደ ሌላ ነገር ለወጠ ነው የሚባለው። እንደዚሁም በጭቃ የወፍ ቅርፅን አሊያም ቢሰራ ፤ የግመል ቅርፅ በቀለማት ነጭ ሉክን ቢያቀልም ቀለማት ሁሉ የአላህ ፍጥረት ናቸው ነጩም ወረቀት እንዲሁ። "ሰዎች ይፈጥራሉ" እና "አላህ ይፈጥራል" ሲባል በመሃላቸው ያለው ልዩነት ይህ ነው። ስለዚህም አላህ ፍጥረታት በማይጋሩትመልኩ  ለየት ያለ መፍጠር ለርሱ አለው ማለት ነው።

ሁለተኛው ከተውሒድ አሩቡቢያ አካል ከሆነው መካከል አንዱ አላህን በሹመት መነጠል ነው። አላህ ብቻውን አስተዳዳሪ ንጉስ ነው። አላህ እንዳለው፦

“ያ ንግሥና በእጁ የኾነው አምላክ ችሮታው በዛ፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡” [አልሙልክ 1]

እንዲህም ይላል፦ «የነገሩ ሁሉ ግዛት በእጁ የኾነ እርሱ የሚጠብቅ በእርሱ ላይ የማይጠበቅ (ጥበቃ የማይሻ) ማን ነው? የምታውቁ እንደኾናችሁ (መልሱልኝ)» በላቸው፡፡” (ሙዕሚኑን :88) ልቅ የሆነና ያልተገደበ ንግስናና ስልጣን ያለው ለአላህ ብቻ ነው። ከአላህ ውጭ ያለ አካል ንጉስ ነው ሲባል አንፃራዊ ንግስና ነው። አላህ በቁርኣን ውስጥ ፍጡር ለሆነ አካል ንግስና አፅድቆለት እናገኘዋለን። አላህ እንዲህ ይላል፦

“ወይም መክፈቻዎቹን የበላይ በሆናቹበት ቤት (ብትበሉ) ኀጢአት የለባችሁም፡፡” [አኑር:61]

እንዲህም ይላል፦

“በሚስቶቻቸው ወይም እጆቻቸው በያዟቸው (ባሪያዎች) ላይ ሲቀር፡፡” [አልሙእሚኑን :6]

እነዚህና ሌሎች ሹመትን ከአላህ ውጭ መኖሩን የሚገልፁ አንቀፆች ይኖራሉ ነገርግን ይህ ንግስና እና ሹመት እንደ አላህ አይደለም። ምክንያቱም ሹመቱ ጎደሎ እና የተገደበ ነው። ለምሳሌ ዘይድ የሚባለው ግለሰብ የተሾመበት ቤት ዐምር የሚባለው ግለሰብ አያስተዳድረውም (አይሾምበትም)። በተጨማሪም ንብረቱን ያለ ገደበ እንደፈለገ ማባከን አይፈቀድለትም። አላህ በሚወደው ነገር ላይ እንጂ በሌላ ነገር ላይ ማዋል አይፈቀድለትም። ለዚህም ሲባል የአላህ መልክተኛ ገንዘብን ያለ አግባብ ማባከንን ከልክለዋል። አላህ እንዲህ ይላል።

“ቂሎችንም ያችን አላህ ለእናንተ መተዳደሪያ ያደረጋትን ገንዘቦቻችውን (የያዛችሁላቸውን) አትስጡዋቸው፡፡” [አኒሳእ:5]

የሰው ልጅ ሹመቱና ስልጣኑ ያልተሟላ እና የተገደበ መሆኑን ይህ አንቀፅ ይጠቁማል። የአላህ ሹመት ግን ፍፁም ከዚህ የተለየ ነው። የእርሱ ሹመት ሁሉንም የሚያካትትና የሚያጠቃልል ስልጣን ነው። ለርሱ ሹመት ገደብ የለውም። ያሻውን የሚሰራ ከሚሰራውም ነገር ማንም ጠያቂ የሌለው ሀያል የሆነ ጌታ ነው። ሌላኛው የሩቡቢያ ማዕዘንና አካል ደግሞ አላህ በማስተናበር የተነጠለ ጌታ መሆኑን ማመን ነው። አላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ ፍጥረታትን፤ ሰማያትና ምድርን ለብቻው ያስተናብራል። አላህ እንዳለው፦

“ንቁ! መፍጠርና ማዘዝ የእርሱ ብቻ ነው፡፡ የዓለማት ጌታ አላህ (ክብሩ) ላቀ፡፡” [አል አእራፍ፡54]

ይኸኛው ማስተናበር ሁሉንም ያጠቃለለ የማስተናበር አይነት ነው። በሚያስተናብረው ነገር ላይ ከልካይና ተቃዋሚ አካል የለውም። አንዳንድ ፍጡሮች ንብረታቸውን ባሪያቸውን፤ ሰራተኛቸውን እና የመሳሰለውን ሊያስተዳድሩ ይችሉ ይሆናል ነገር ግን ይህ ውስንና የተገደበ ማስተዳደር ነው። ከዚህም ማብራሪያ በመነሳት ተውሒዱ ሩቡቢያ አላህን በፍጥረት ዓለሙ በሹመት እና በማስተናበር መነጠል ነው ብንል አልተሳሳትንም። ይህ ነው የተውሒድ አሩቡቢያ ፅንሰ ሐሳብ።

ሁለተኛው የተውሒድ ክፍል ደግሞ ፦ ተውሒድ ኡሉሂያ ነው። ትርጉሙም አላህን በአምልኮት ነጥሎ ማምለክ ማለት ነው። የሰው ልጅ ከአላህ ውጭ ያለ አካልን ልክ እንደ አላህ ሊያመልከውና ወደ እርሱ ሊቃረብ አይፈቀድለትም። ይኸኛው የተውሒድ ክፍል የመካ ሙሽሪኮች የጠመሙበትና መንገድ የሳቱበት የተውሒድ አይነት ሲሆን መልክተኛው በዚህ የተነሳ ተጋድለዋቸዋል። ሴቶቻቸውንና ዝርዮቻቸው ሊማረኩ ንብረቶቸውንና ግዛቶቻቸውንም  ሀላል ሊያደርጉ የቻሉበት ሚስጥር ይኸው ነው። መልዕክተኞች በሙሉ የተላኩበት ተልእኮ፤ከሰማይ መፅሐፍት የተወረዱበት ዓላማ። ተውሒድ አሩቡቢያ እና ተውሒዱ አስማኢ ወሲፋት የእርሱ አካሎችና መሰሎቹ ጋር ጎን ለጎን ቢጠቀሱም ዋነኛው ግን ተውሒዱ አልኡሉሂያ ነበር። ነግር ግን መልዕክተኞች ከወገኖቻቸው ጋር የሚጋፈጡበትና ከባድ ነቀፌታና ተቃውሞ የሚገጥማቸው በዚህ ተውሒድ ክፍል ላይ ነበር። ይህ የተውሒድ ክፍል ተውሒዱ አልኡሉሂያህ የሚባል ሲሆን መልዕክቱም የሰው ልጅ አካል ቅርብ መላኢካም ሆነ ነቢይና ረሱልነት ማዕረግ ያላቸው አካል፤ ወሊይም ሆነ ፃድቅ እንዲሁም ሌሎች ከአላህ ውጭ ላለ ለማንኛውም ፍጥረታት ከአምልኮ ቅንጣት ታክልም ቢሆን አሳልፎ መስጠት አይፈቀድለትም። በዚህ የተውሒድ ክፍል ላይ ክፍተት ኖሮበት በተውሒድ ሩቡቢያና አስማኡ ወሲፋት ላይ ምንም ችግር ባይኖርበትም እንኳ አካል እርሱ ሙሽሪክና ካፊር ይባላል። ምክንያቱም አምልኮ ከአላህ ውጭ ላለ አካል ለማንም አይገባምና። እንበልና ከሰዎች መካከል አንድ ሰው በአላህ ፈጣሪነት፤አስተናባሪነት እና የሚገቡትን ስሞችና ባህሪያቶችን በሚገባው አረጋግጦ ቢያምን ነግር ግን ከአላህ ጋር ከአላህ ውጭ ያሉ አካላትን የሚያመልክ ከሆነ በሩቡቢያና በአስማኡ ወሲፋት ማመኑ ብቻ ምንም ፋይዳ የለውም። ሩቡቢያና አስማኡ ወሲፋት ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ነገር ግን ቀብር ዘንድ ሄዶ የሞተን አካል የሚያመልክ አሊያም ለሙታን ስለትን የሚሳል ሰው ቢኖር ይህ ግለሰብ ሙሽሪክና ካፊር ነው ። እሳትም ውስጥ ዘውታሪ ይሆናል። አላህ እንዳለው፦

“እነሆ!  በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡” [አልማኢዳ:72]

ቁርኣን በሚገባ ያነበበ ሰው እንደሚረዳው መልክተኛው ዘመቻ የከፈቱባቸው፤ ደማቸውና ንብረታቸውን ሐላል ያደረጉባቸው፤ልጆቻቸውን፤ ሚስቶቻቸውን ፤ግዛቶቻቸውንና መሬቶቻቸውን የማረኩባቸው ሙሽሪኮች አላህ ፈጣሪና ጌታ መሆኑን ምንም ሳይጠራጠሩ ያጸድቁ ነበር። ነገር ግን ከአላህ ጋር ሌሎችን አማልክቶችን አብረው በማምለካቸው የተነሳ ደማቸውና ንብረታቸው ሐላል የተደረገባቸው ሙሽሪኮች ሆነዋል።

ሦስተኛው የተውሒድ ክፍል ደግሞ ተውሒዱ አል አስማኢ ወሲፋት ይባላል።  አላህን በስሞቹና በባህሪያቱ ብቸኛ መሆኑን ማመን ሲሆን አላህ እና መልዕክተኛው ያጸደቁትን ስሞችና መገለጫዎች ያለ ተሕሪፍ ትርጉም ሳይዛባ፤ ያለ ተዕጢል (ትርጉም አልባ ሳያደርጉ)፤ ያለ ተክዪፍ (ሁናቴው ሳይጠቀስ)፤ እና ያለ “ተምሲል” (አምሳያ ሳይደረግለት) በማጽደቅ ማመን ማለት ነው። ስለሆነም አላህ  እራሱን በሰየመበት ስያሜዎች እና እራሱን በገለፀበት መገለጫዎች በሐቂቃው ያለ “መጃዝ” ማመን ግዴታ ነው። ታዲያ ይህ መታመን ያለበት ያለ እንዴታ እና ከፍጥረታ ጋር ሳያመሳስሉ መሆን አለበት።

ይህ የተውሒድ ክፍል ከእኛ ጋር ወደ አንድ ቂብላ ዞረው የሚሰግዱ እራሳቸውን ወደ እስልምና ሀይማኖት የሚያስጠጉ በርካታ ጭፍራዎች በተለያየ መልኩ ጥመት ላይ የወደቁበት አጀንዳ ነው። ከነዚህም መካከል ነፍይ እና ተንዚህ ውድቅ ማድረግ ላይ ከልክ ያለፈ መንገድን በመከተላቸው ከኢስላም መውጣት ደረጃ አድርሷቸዋል። ከሙስሊም ጭፍሮች መካከል መካከለኛ አካሄድን የተጓዘ አለ። ከነርሱም መካከል ለአህሉ ሱና ቅርብ የሚባሉ አንጃዎችም አሉ። ነገር ግን ሰለፎች በዚህ የተውሒድ ክፍል ያላቸው አቋም አላህ እራሱን በሰየመበትና እራሱን በገለፀበት ባህሪያት በሐቂቃው ያለ ተሕሪፍ ፤ተዕጢል፤ተክዪፍ እና ያለ ተምሲል መሰየም ነው።

ለምሳሌ፦ አላህ እራሱን ከሰየመባቸው ስሞች መካከል “አል ሐዩ አል ቀዩም” የሚለው ይገኝበታል። ስለዚህም “አል ሐዩ አል ቀዩም” የሚለው ስም ከአላህ ስሞች መካከል አንዱ መሆኑን አምነን መቀበል ይኖርብናል። በተጨማሪም ይህ ስም በውስጡ ያካተተውን መገለጫ ባህሪ ማመን ይኖርብናል። ይህ ስም በውስጡ አቅፎ የያዘው ባህሪም ምሉዕ ሕይወት ማለትም ባለመኖር ያልተቀደመና መጥፋት(መሞት) የማይጠጋው ህይወት ነው። አላህ እራሱን ሰሚዕ እና ዓሊም ብሎ ሰይሟል።ስለሆነም አላህ ሰሚዕ ”የሚሰማ” የሚለው ስምና መስማት የሚለው መገለጫ ባህሪ እንዳለው ማመን ግዴታ ነው። እርሱም ይህ ስምና ባህሪ በሚያስፈርደው መልኩ “ሐከም” ፈራጅ ነው። ያለ መስሚያ ይሰማል ወይም የሚሰሙ ነገሮች ሳይደርስባቸው ይሰማል የሚባለው ፍልስፍና ተቀባይነት የለውም። በዚህ ምሳሌ መሰረት ሌሎችን እያመሳሰልክ እመን(ተገንዘብ)።

ሌላኛው ምሳሌ ፦ አላህ እንዲህ ይላል ፦

“አይሁዶችም «የአላህ እጅ የታሰረች ናት» አሉ፡፡ እጆቻቸው ይታሰሩ ባሉትም ነገር ይረገሙ፡፡ አይደለም (የአላህ) እጆቹ የተዘረጉ ናቸው፡፡ እንደሚሻ ይለግሳል፡፡” [አልማኢዳ:64]

 እዚህ ቦታ ላይ፦”አይደለም (የአላህ) እጆቹ የተዘረጉ ናቸው፡፡” ይላል። አላህ ሁለት የተዘረጉ እጆች እንዳሉት አረጋገጠ። ይህም ማለት ስጦታው እጅግ ሰፊ የሆነ ማለት ነው። ስለዚህም አላህ ጸጋዎችን በማደልና በመስጠት ላይ ዝርግ የሆኑ ሁለት እጆች እንዳሉ ማመን ግድ ይሆንብናል። ነገር ግን እነዚህ ሁለት እጆች በልባችንም ይሁን በአዕምሯችን እንዲሁም በአንደበታችን “ከይፊያ” ማነፃፀር ወይም ከፍጥረታት እጆች ጋር ለማመሳሰል ጥረት አለማድረግ ግዴታ ይሆንብናል። ምክንያቱም አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏልና

“ለርሱ ምንም አምሳያ የለውም፡፡ እርሱም ሰሚውና ተመልካቹ ነው፡፡” [አሽ ሹራ:11]

እንዲህም ይላል፦

«ጌታዬ እርም ያደረገው መጥፎ ሥራዎችን፣ ከርሷ የተገለጸውንና የተደበቀውን ኃጢኣትንም፣ ያላግባብ መበደልንም፣ በርሱም ማስረጃ ያላወረደበትን (ጣዖት) በአላህ ማጋራታችሁን፣ በአላህም ላይ የማታውቁትን መናገራችሁን ብቻ ነው» በላቸው፡፡” [አል አዕራፍ:33]

እንዲህም ይላል፦

“ለአንተም በርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር አትከተል፡፡ መስሚያ፣ ማያም፣ ልብም እነዚህ ሁሉ (ባለቤታቸው) ከእነሱ ተጠያቂ ነውና፡፡” [አል ኢስራእ:36]

እነዚህ ሁለት እጆች ከፍጥረታት እጆች ጋር ያመሳሰለ የአላህን ቃል እንዳስተባበል ይቆጠራል። “ለርሱ ምንም አምሳያ የለውም፡፡ እርሱም ሰሚውና ተመልካቹ ነው፡፡” [አሽ ሹራ:11] በተጨማሪም ይህን አንቀፅ በማመፁ አላህን ወንጅሏል።

አላህ እንዲህ ይላል፦

“ለአላህም አምሳያዎችን አታድርጉ፡፡” [አን ነህል :74] 

“ከይፊያ” ያደረገ ማለትም እጆቹ እንዲህ እንዲያ ናቸው ብሎ የተናገረ በአላህ ላይ የማያቀውን ተናግሯል። ዕውቀት የሌለው በሆነ ነገር ላይም ተከታይ ሆኗል።

 

 

11/ከዒባዳ አይነቶች አንዱን ከአላህ ውጭ ላለ አካል አሳልፎ መስጠት በሸሪዓው ምን ብያኔ አለው?

የዚህ መልስ ምናልባትም እስካሁን ከላይ ካሳለፍነው ነገር መረዳት ይቻላል። ተውሒድ ማለት አላህን በአምልኮ ነጥሎ ብቻውን ማምለክ ማለት ነው ብለናል። ከአላህ ውጭ ያለን አካል ከአምልኮቶች በአንዱ ማምለክ አይፈቀድም። እንደሚታወቀው እርድ የሚባለው የአምልኮ ዘርፍ አንድ ሰው ወደ ጌታው ከሚቃረብበት ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ምክንያም አላህ እርድ ለርሱ ብቻ እንዲሆን እንዲህ ሲል አዟልና።

“ለጌታህ ስገድ ለእርሱም ሰዋም(እረድ)።” [አልከውሰር:2]

ማንኛውም መቃረቢያ የተደረጉ ነገሮች በሙሉ ዒባዳዎች ናቸው። አንድ ሰው ለአላህ እራሱን በማስተናነስና አላህን በማላቅ ዕርድን እንደሚያቀርበው ከአላህ ውጭ ላለ አካል በማላቅ፤ እራስን በማስተናነስ ወደሱ ለመቃረብ በሚል እርድ ያቀረበ ከሆነ በዚህ ተግባሩ በአላህ ላይ አጋርቷል። ሙሽሪክ ደግሞ በርሱ ላይ ጀነት እርም እንደሆነች መኖሪያውም እሳት እንደሆነ አላህ በቁርኣኑ ገልፆታል።

ከዚህም በመነሳት አንዳንድ ሰዎች አውሊያዎች ናቸው ብለው የሚሞግቷቸው መቃብር ዘንድ በመሄድ የሚፈፅሙት የእርድ አይነት ሽርክን ከእስልምና መንገድ የሚያስወጣ ተግባር ነው። ለነዚህ ሰዎች የምንመክረው ፦ ከሚሰሩት ነገር ተፀፅተው ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መመለስ ይኖርባቸዋል። ተውበት በማድረግ ሰላትን፤ ፆምን ለአላህ ብቻ እንደሚያደርጉ ሁሉ እርድንም ለአላህ ብቻ ካደረጉ አላህ ያለፈውን በሙሉ ይቅር ይላቸዋል። አላህ እንዳለው፦

“ለነዚያ ለካዱት በላቸው፡- ቢከለከሉ ለእነሱ በእርግጥ ያለፈውን (ሥራ) ምሕረት ይደረግላቸዋል፡፡” [አልአንፋል:38]

እንዲያውም ከዚህ በላይ አላህ ያደርግላቸዋል። ያም ወንጀላቸውን ወደ መልካም ምንዳ ይቀይርላቸዋል። አላህ እንዲህ ብለዋል፦

“እነዚያም ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ የማይገዙት፣ ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ ያለ ሕግ የማይገድሉት፣ የማያመነዝሩትም ናቸው፡፡ ይህንንም የሚሠራ ሰው ቅጣትን ያገኛል፡፡ በትንሣኤ ቀን ቅጣቱ ለእርሱ ይደራረባል፡፡ በእርሱም ውስጥ የተዋረደ ኾኖ ይኖራል፡፡ተጸጽቶ የተመለሰና ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡ እነዚያም አላህ መጥፎ ሥራዎቻቸውን በመልካም ሥራዎች ይለውጣል፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” [አልፉርቃን:68_70]

ስለዚህም ለነዚህ ወደ ሙታን ለመቃረብ ብለው ቀብር ዘንድ እርድን ለሚፈፅሙ ሰዎች የምመክረው ከዚህ ተግባራቸው ተውበት እንዲያረጉ ነው ይህን ካደረጉ ከባለውለተኛው ጌታቸው ተውባ እንደሚያደርግላቸው ልናብስራቸው እንወዳለን። አላህ ተውበት በሚያደርጉ ሰዎች ይደሰታል።

13/የላ ኢላህ ኢለሏህ ትርጉም እያየን ነበር ሙሀመዱ ረሱሉላህ ማለት ደግሞ ምን ማለት ነው?

ሙሀመዱ ረሱሉላህ ማለት ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲላህ አልቁረይሺ አልሃሺሚይ ለፍጥረታት በሙሉ ለሰዎች እና ለጂኖች መልክተኛ መሆናቸውን በልብ ማመንና በዐንደበት ማረጋገጥ ማለት ነው። አላህ እንዳለው፦

«እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደናንተ ወደሁላችሁም የአላህ መልክተኛ ነኝ፡፡ (እርሱም) ያ የሰማያትና የምድር ንግሥና ለእርሱ ብቻ የኾነ ነው፡፡ እርሱ እንጂ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ያደርጋል፡፡ ይገድላልም፡፡ በአላህ በዚያም በአላህና በቃላቶቹ በሚያምነው የማይጽፍ የማያነብ ነቢይ በኾነው መልክተኛው እመኑ፡፡ ቅንንም መንገድ ትመሩ ዘንድ ተከተሉት፡፡» [አልአዕራፍ:158]

 

እንዲህም ይላል፦ “ያ ፉርቃንን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስፈራሪ ይኾን ዘንድ ያወረደው (አምላክ) ክብርና ጥራት ተገባው፡፡” [አልፉርቃን:1]

የዚህ የምስክር ቃል በተዘዋዋሪ ግዴታ የሚያስደርገው ነገር እነሆ፦ መልክተኛው የተናገሩትን እውነት ብሎ መቀበል፤ያዘዙትን መታዘዝ፤የከለከሉትን መከልከል፤በርሳቸው ሸሪዓ ብቻ አምልኮትን መፈፀም። በተጨማሪም መልክተኛው አንድም የፈጣሪነት መብት አላቸው፤ አምልኮት ይገባቸው እና ፍጥረተ ዓለሙ ላይ ያስተናብራሉ ብሎ አለማመን። እንዲያውም መልክተኛው ባርያ እንጂ አይመለኩም። የማይስተባበሉ መልክተኛ ናቸው። አላህ በሻው ነገር ቢሆን እንጂ። ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ጥቅምን ማስገኘትም ሆነ መከላከል አይችሉም2

አላህ እንዳለው፦

«ለእናንተ የአላህ ግምጃ ቤቶች እኔ ዘንድ ናቸው አልልም፡፡ ሩቅንም አላውቅም፡፡ ለእናንተም እኔ መልአክ ነኝ አልልም፡፡ ወደእኔ የሚወርድልኝን እንጅ ሌላን አልከተልም» በላቸው፡፡ «ዕውርና የሚያይ ይስተካከላሉን᐀ አታስተነትኑምን᐀» በላቸው፡፡” [አልዐንዓም:50]

መልክተኛው የታዘዘውን የሚከተል ባሪያ ነው። ይህን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ይላል

«እኔ ለእናንተ ጉዳትንም ሆነ ጥቅምን አልችልም» በላቸው፡፡ከአላህ (ቅጣት) አንድም አያድነኝም፡፡ ከእርሱም ሌላ መጠጊያን አላገኝም» በላቸው፡፡” [አልጂን:21_22]

እንዲህም ይላል፦

«አላህ የሻውን በስተቀር ለእራሴ ጥቅምንም ጉዳትንም ማምጣት አልችልም፡፡ ሩቅንም (ምስጢር) የማውቅ በነበርኩ ኖሮ ከመልካም ነገር ባበዛሁና ክፉም ነገር ባልነካኝ ነበር፡፡ እኔ ለሚያምኑ ሕዝቦች አስፈራሪና አብሳሪ እንጂ ሌላ አይደለሁም» በላቸው፡፡” [አልአዕራፍ:188]

ይህ ነው የላ ኢላህ ኢለሏህ ሙሐመደ ረሱሉሏህ መልዕክት። ከዚህም መልዕክት የምንረዳው መልክተኛውም ይሁን ከሳቸው በታች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ፍጥረታት ከአምልኮ ዘርፎች አንዱም አይገባቸውም። አምልኮ ለአላህ እንጂ የለሌላ የማንም መብት አይደለምና። የመልክተኛው መብት ደግሞ አላህ የሰጣቸው ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ብቻ ነው። እርሱም የአላህ ባሪያና መልክተኛ መሆናቸውን መመስከር።


2 በተጨማሪም መለዕክተኛው የሩቡቢያ እና የፍጥረተ አለሙን የማስተናበር መብት እንደሌላቸው፤ አምልኮም እንደማይገባቸው፤  እንዲያውም የሚያመልኩ እና የማያስተባብሉ ባሪያ መሆናቸውንናለራሳቸውም ሆነ ለሌላው አላህ ባሸው ነገር ቢሆን እንጂ ጥቅም ማስገኘትም ሆነ መከልከል እንደማይችሉ ማመን ያጠቃልላል። 

14/በልብ ማመንና በዐንደበት መመስከር ልዩነቱ ምንድ ነው? ሁለቱን በአንድ ላይ ማስገኘት ግዴታ ነውን?

አዎን።በልብ ማመንና በዐንደበት መመስከር ልዩነቱ ግልፅ ነው።አንዳንድ ሰው በዐንደበቱ ብቻ ቢመሰክርም በቀልቡ አያምንም ለምሳሌ ሙናፊቆች። ሙናፊቆችን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ይላል፦

“መናፍቃን በመጡህ ጊዜ «አንተ የአላህ መልክተኛ መኾንህን በእርግጥ (ምለን) እንመሰክራለን» ይላሉ፡፡[አልሙናፊቁን:1]”

አላህ ግ እንዲህ ይላል፦

“አላህም አንተ በእርግጥ መልክተኛው መኾንህን ያውቃል፡፡ አላህም መናፍቃን (ከልብ እንመሰክራለን በማለታቸው) ውሸታሞች መኾናቸውን አላህ ይመሰክራል፡፡” [አልሙናፊቁን:1]

እነዚህ መናፍቃን በልባቸው ሳይሆን በዐንደበታቸው መልክተኛው መልክተኛ መሆኑን መስክረዋል። ምናልባትም አንድ ሰው በቀልቡ አምኖ በዐንደበቱ መመስከር የሚከብደው ይኖራል። በምናየው ውጫዊ ተግባር ተነስተን ፍርድ እንሰጣለን እንጂ ውስጣዊ እምነቱ እኛ ዘንድ ምንም አይፈይደውም። ሆኖም በርሱና በአላህ መካከል ያለውን ጉዳይ አስመልክቶ እኛ የምናውቀው ነገር የለንም። ወይም ደግሞ ሊባል የሚችለው ፍርዱን ወደ አላህ እንተወዋለን። ነገር ግን ዱንያ ላይ ምንም አይጠቅመውም። በዐንደቱ እስካልመሰከረ ድረስ ሙስሊም የሚለው ብያኔ አይሰጠውም። ምናልባት መናገር የሚሳነው ከሆነና ምላሱ ላይ ችግር ኖሮ አሊያም እንዳይናገር የሚከለክለው ነገር ካለ እንደሁነታው ፍርድ ይሰጠዋል። ያም ሆነ ይህ በቀልብም ይሁን በአንደበት መመስከር ግዴታ ነው።

61/ጉልህ የሆኑ ቁርኣን ንበብ ደንቦችና ስርኣቶች ምንድን ናቸው?

ቁርኣንን የሚያነብ ሰው ከትልቁ(ጀናባ)እና ከትንሹ(ውዱን የሚያበላሹ) ሐደስ ጠሃራ ሊሆን ይገባል።ጀናባ ላይ ሆኖ አንድ ሰው ቁርኣንን ማንበብ አይፈቀድለትም።በሐዲስ ላይ እንደመጣው ጁኑብ ላይ የሆነ ሰው እስኪታጠብ ቁርኣንን ማንበብ ይከለከላል። የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ቁርኣንን ማንበብ ትችላለችን? የሚለውን ርእስ አስመልክቶ የእውቀት ባለቤቶች የተለያየ አቋም አላቸው።

ሁለት የተለያየ አቋም ያሏቸው ሲሆን  ከእነሱም መካከል ቁርኣን መቅራት ትችላለች ያሉ አሉ። ምክንያቱም ቁርኣን መቅራቷን የሚከለክል ግልፅ የሆነ የሐዲስ ማስረጃ የለምና። በሸሪዓችን ደግሞ አንድ ሰው ከጅማሬው ጫንቃው ከግዴታ የጠራ ነው፤አለማስገደድ፤ ከእንደገናም ባንድ ነገር ላይ አለመከልከል ነው መሰረቱ።አንዳንድ ዑለማዎች ደግሞ ሐይድ ላይ ሆኗ ቁርኣንን መቅራት አትችልም የሚል አመለካከት አላቸው። ምክንያቱም እንደ ጀናባ ትጥበት ይኖርበታል። እንዲሁም ሐይድ ላይ ያለችን ሴት ቁርኣንን መቅራት የሚከለክሉ ከመልዕክተኛው(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) ሐዲስ ተዘግበዋል።እኔ በዚህ ላይ ያለኝ አቋም መቅራት ብቻ ከሆነ አላማዋ ባትቀራ ይሻላል ባይ ነኝ።ነገር ግን ቁርኣን ካልቀራሁ እረሰዋለሁ የሚል ስጋት ካላት አሊያም አስተማሪ በመሆኗ ቁርኣን ተማሪዎቿና ልጆቿን ለማስቀራት፣ወይም ተማሪ በመሆኗ ቁርኣን ማሰማት ካለባት እና ለመሳሰሉት ጉዳዮች መቅራቷ ችግር የለውም። በተጨማሪም እለታዊ አዝካር ውስጥ ለምሳሌ አያቱል ኩርሲይ ብትቀራ ችግር የለውም። ይህ አቋም ለሐቅ የቀረበ ነው የሚል እምነት አለኝ። በጥቅሉ ሐይድ ላይ ያለችን ሴት አስመልክቶ ቁርኣን መቅራቷ ወሳኝ ከሆነ መቅራት ይፈቀድላታል።ሆኖም መቅራቷ ወሳኝና አስፈላጊ ካልሆነ መቅራት የለባትም።

እንደዚሁም አንድ ቁርኣን የሚቀራ ሰው ቁርኣንን በሚያነብበት ጊዜ የሚያነበውን የቁርኣን የላቀ መልዕክት ይረዳ ዘንድ ልቡን ጥዶ ማንበብ ይጠበቅበታል። አንቀፆቹ በውስጣቸው የያዙዋቸውን መልዕክቶች ታሪክ፣ዜና እና ህግጋትን ሁሉንም በእኩል ማስተንተን ይኖርበታል። ምክንያቱም ቁርኣን የወረደው ለዚህ ጥበብ ነውና።

“ (ይህ) ወዳንተ ያወረድነው ብሩክ መጽሐፍ ነው፡፡ አንቀጾቹን እንዲያስተነትኑና የአእምሮዎች ባለቤቶችም እንዲገሰጹ (አወረድነው)፡፡ “ [ሷድ ፡29]

የሰው ልጅ ልቡ ዝንጉ ሆኖና ልቡ ተጥዶ (እያስተነተነ) ቁርኣንን ሲያነብ በሁለቱ መሃል ከፍተኛ ልዩነት ያስተውላል።ቁርኣንን በማስተንተንና በማስተዋል ሲቀራ ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል። በዚህ መልኩ ቁርኣን ማንበብ ልቡ ውስጥ ጠንካራ ኢማን እና እርግጠኝነት፣የአላህ መፅሐፍ በውስጡ የሚያካትታቸውን ህግጋቶች መፈፀምና መታዘዝ ላይ ጠንካራ ተፅእኖ ያሳድራል።

ቁርኣን ሲነበብ ሊጠበቁ ከሚገቡ ስርኣቶች መካከል፦ ሲነበብ በርጋታ ሊሆን ይገባል፣አንዳንድ ፊደላት እስኪሳቱ ወይም ቃላቶች እስኪሰወሩ ድረስ በፍጥነት መቀራት አይኖርበትም። እንዲያውም በዝግታና በእርጋታ መቀራት አለበት ነገርግን ፊደላት ሳይጣሉ፣ኢድጋም መደረግ የሌለበትን ኢድጋም ሳይደረጉ እና የመሳሰሉት ህግጋት ሳይጣሱ አንዳንዴ መፍጠን ችግር  የለውም።