Back to Top
የሰላት ማዕዘናት ምን ምን ናቸው?

ጥያቄ(96): የሰላት ማዕዘናት ምን ምን ናቸው?
መልስ:

የሰላት አሰጋገድ ላይ ከላይ የጠቀስናቸው የሰላት ማዕዘናትን፣ዋጅቦች እና ሱናዎችን ያካትታሉ። የእውቀት ባለቤቶች ሰላት ውስጥ የሚፈፀሙ ተግባሮችን አርካን፣ዋጂባት እና ሱነኖች በማለት ለሦስት ይከፍሏቸዋል። ከፊል በሆኑ አርካኖች እና ዋጂባቶች ላይ ሲስማሙ በከፊሎች ላይ ደግሞ ይለያያሉ።

የሰላት አርካን(ማዕዘናት) ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት እንጠቅሳለን።

የመጀመሪያው ማዕዘን፦ የመቆም አቅም ያለው መቆም አለበት። ይህ ግን የሰላት ማዕዘን ሆኖ የሚቆጠረው ፈርድ ሰላቶች ላይ እንጂ ሱና ሰላቶች ላይ አይደለም። አላህ አዘወጀለ እንዲህ ይላልና፦

 “ሰላቶችን ተጠባብቃቹ ስገዱ” [አልበቀራ:238]

መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ደግሞ ለኢምራን ኢብኑ ሑሰይን ረዲየላሁ ዐንሁ  እንዲህ ብለውታል፦

“ከቻልክ ቆመህ ፣ካልቻልክ ደግሞ ቁጭ ብለህ፣ይህንም ካልቻልክ በጎንህ ጋደም ብለህ ስገድ።”

ከሰላት ማዕዘናት መካከል ሁለተኛው፦ ተክቢረተል ኢህራም ማድረግ ነው። ለዚህም ማስረጃችው ሰላትን ሳያስተካክል ለሰገደው ሰው መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ  ብለውታል፦

“ሰላትን ባሰብክ ጊዜ ቅድሚያ በደንብ ውዱእ አድርግ። ከዚያም ወደ ቂብላ በመዞር ተክቢረተል ኢህራም አድርግ።” አላሁ አክበር ማለት ይኖርበታል እንጂ “አላሁ አጅጀል” ወይም “አላሁ አዕዘም” እና የመሳሰሉት ተክቶ ማለት አይፈቀድም። እንዲሁም አላሁ አክበር ሲል አሊፉን መሳብ የለበትም። ይህን የሚል ከሆነ አላህ ትልቅ ነው የሚለው መልዕክት አላህ ትልቅ ነውን?ወደሚለው ትርጉም ይቀየራል።እንዲሁም “ባ” ፊደልን በመሳብ አላሁ አክባር ማለት አይቻልም። በዚህን ጊዜ የ”ከበር“ ብዙ ቁጥር ሲሆን ከበሮዎች የሚል ትርጉም ይሰጠናል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ “አላሁ ወክበር” ይላሉ ይህ አረብኛው ላይ አገባብ ስለማያጣ ሰላትን አይበላሽም።

ሦስተኛው ማዕዘን፦ ፋቲሓን ማንበብ ። መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋልና፦

 “ፋቲሓን ያልቀራ ሰላት የለውም።” ፋቲሓን የማያውቅ ከሆነ መማር ግዴታ አለበት። ይህን መማር ካልቻለ ፋቲሃን የሚተካ ሌላ ቁርኣን አንቀፅ ማንበብ ይችላል። ይህንም ካልቻለ ሱብሓነላህ ወልሀምዱሊላህ፣ወላሁ አክበር፣ላኢላሀ ኢለሏህ ይላል።

አራተኛው ማዕዘን፦ ሩኩዕ ማድረግ አላህ አዘወጀለ እንዲህ ብሏልና ፦

“እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! (በስግደታችሁ) አጎንብሱ፣ በግንባራችሁም ተደፉ፣” [አልሐጅ:77]

መልክተኛውም  ሰላቱን አስተካክሎ ላልሰገደው ሰው እንዲህ ብለውታል፦

 “ከዚያም ተረጋግተህ ሩኩዕን አድርግ።”

አምስተኛው ማዕዘን፦ ከሩኩዕ መነሳት ነው። ምክንያቱም የአላህ መልክተኛ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም  ሰላቱን አስተካክሎ ላልሰገደው ሰው እንዲህ ብለውታል፦

“ከዚያም ተረጋግተህ ጎንበስ ካልክበት ተነስ።”

ስድስተኛው ማዕዘን፦ ሱጁድ ማድረግ ሲሆን ይህን በማስመልከት አላህ አዘወጀለ እንዲህ ብሏል፦ ““እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! (በስግደታችሁ) አጎንብሱ፣ በግንባራችሁም ተደፉ፣” [አልሐጅ:77]

መልክተኛውም ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰላቱን አስተካክሎ ላልሰገደው እንዲህ ብለውታል፦

“ተረጋግተህ ሱጁድ አድርግ።”

ሰባተኛው ማዕዘን፡- በሁለቱ ሱጁድ መካከል መቀመጥ ሲሆን ማስረጃውም መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ከዚያም የተቀመጥክ ሆነህ እስክትረጋጋ ድረስ ከሱጁድ ተነስተህ ቁጭ በል።”

ስምንተኛው ማዕዘን፦ ሁለተኛው ሱጁድ ማድረግ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በየረከዐው ሁለት ሱጁድ ማድረግ ግዴታ ስለሆነ። መልክተኛውም ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰላቱን ሳያስተካክል ለሰገደው እንዲህ ብለውታል፦ “ከዚያም የተቀመጥክ ሆነህ እስክትረጋጋ ድረስ ከሱጁድ ተነስተህ ቁጭ በል።” ካሉት በኋላ በድጋሚ “ሱጁድ ያደረግክ ሆነህ እስክትረጋጋ ድረስ ሱጁድ አድርግ።” ብለውታል።

ዘጠነኛው ማዕዘን፦ የመጨረሻው ተሸሁድ ነው። ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ብለዋልና፦

“ተሸሁድ በእኛ ላይ ግዴታ ከመሆኑ በፊት እንቆም ነበር።” የሚለው አባባል ተሸሁድ ግዴታ መደረጉን ያሳያል።

አስረኛው ማዕዘን፦ መጨረሻው ተሸሁድ ላይ “ሰላት አለ ነቢይ” ማለት ሲሆን ይህ ኢማሙ አሕመድ ረሂመሁላህ ዘንድ በሰፊው የሚታወቀው አቋም ነው።

በመቀጠልም ፈጅርና ባለ ሁለት ረከዓ ሰላት ከሆነ ተሸሁድ ጨርሶ ያንባል። በመቀጠልም እንዲህ ይላል፦ “አላሁመ ሰሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ አሊ ሙሐመዲን ከማ ሰለይተ ዐላ ኢብራሂም ወዐላ አሊኢብራሂም ኢነከ ሐሚዱን መጂድ አላሁመ ባሪክ አላ ሙሐመዲን ወዐላ አሊ ሙሐመዲን ከማ ባረከትዐላ ኢብራሂም ወዐላ አሊሙሐመዲን ኢነከ ሀሚዱን መጂድ። አዑዙቢላሂ ሚን ዐዛቢጀሀነም ወሚን ዐዛቢአልቀብር ወሚንፊትነቲል መህያ ወልመማት ወሚንፊትነቲል መሲሂ ደጃል።” ይላል ከዚያም ዱዓ መጨመር ከፈለገ ይጨምርና ከዚያም በስተቀኙ “አሰላሙ ዐይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካትሁ” ከዚያም በግራው ይህንኑ ይደግማል።

አስራ አንደኛው የሰላት ማዕዘን፦ በሰላት ማዕዘናት መካከል ያለውን ቅደም ተከተል መጠበቅ። እንደሚከተለው ፦ ለሰላት መቆም(ቂያም)ከዚያም ሩኩዕ ማድረግ፣ ቀጥሎ ከሩኩዕ መነሳት፣ከዚያም ሱጁድ ማድረግ፤ከዚያም በሁለት ሱጁዶች መካከል መቀመጥ። ሩኩዕ ከማድረጉ በፊት ሱጁድ ቢያደርግ ሰላቱ ተቀባይነት የለውም፤ ምክንያቱም የሰላት ቅደም ተከተሉን አልጠበቀምና።

አስራ ሁለተኛው ማዕዘን፦ በሁሉም የሰላት ማዕዘናት ላይ መረጋጋት  መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰላት ሳያስተካክል ለሰግደው ፦ “ተረጋግተህ ሩኩዕን አድርግ። ከዚያም ተረጋግተህ ቆም በል። ከዚያም ተረጋግተህ ሱጁድ አድርግ።”ብለውታል።

በሰላት ላይ መረጋጋት ማለት ሰጋጁ ሰላት ውስጥ እንቅስቃሴ በማድረጉ የተንቀሳቀሱት የሰውነት ክፍሎች ወደነበሩበት መመለሳቸው ነው። ዑለማዎች “በትንሹም እንኳ ቢሆን መረጋጋት እና መስከን “ጠምኣኒናህ” ይባላል።” ይላሉ። ስክነት ሳይኖረው ሰላቱን ሰግዶ ያጠናቀቀ አንድ ሺ ግዜ እንኳ ቢሰግድ ሰላቱ ተቀባይነት የለውም።

ከዚህም በመነሳት ዛሬ ላይ እንደምናስተውለው ሰላታቸው ላይ እርጋታ (ስክነት) ባለማድረጋቸው የተነሳ በርካታ ሰጋጆች ስህተት ላይ መሁናቸውን እንገነዘባለን። በተለይም ከሩኩዕ ብድግ ሲሉ እና በሁለቱ ሱጁዶች መካከል የሚገኘው መቀመጥ ላይ ተስተካክለው ቆም ወይም ቁጭ ከማለታቸው በፊት ወዲያውኑ ፈጥነው ሱጁድ ሲወርዱ ትመለከታለህ። ይህ ድርጊት ደግሞ እጅግ ከባድ ስህተት ነው። በዚህ መልኩ አንድ ሰው አንድ ሺህ ሰላት ቢሰግድ ሰላቱ ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም አንድ ግለሰብ እርጋታ በሌለው መልኩ ሰላቱን በማገባደድ ወደ አላህ መልክተኛ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም መጥቶ ሰላም ሲላቸው፦ “ተመለስ ስገድ አልሰገድክምና።” ብለውታል። ከዚህ የምንረዳው ሰላት ውስጥ ዋጂባትን አሊያም አርካን በማጓደል የሰገደ ሰላቱ ተቀባይነት እንደሌለው ነው። እንዲያውም አርካኖችን አለማወቁ ዑዝር አይሆንለትምና ሰላቱ ተቀባይነት የለውም።

አስራ አራተኛው ማዕዘን፦ (የመጨረሻው የሰላት ማዕዘን)  በማሰላመት ከሰላት መውጣት ነው። ይኸውም ሰላቱን ሲያገባድድ “አሰላሙ ዐለይኩም ወራህመቱላህ” በቀኝና በግራው ማሰላመት ሲሆን ሁለቱም ማሰላመቶች ከሰላት “ሩክን” የሚመደቡ ነው የሚለው አቋም ትክክለኛ ነው። ከሰላት ፈርድም ይሁን ሱና  አንዱንም ቢሆን ማጓደል አይፈቀድም። ከፊል ዑለማዎች አንደኛው ማሰላመት ብቻ ነው ፈርዱ ወይም ግዴታው ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ የመጀመሪያው ማሰላመት ሱና ላይ ብቻ እንጂ ፈርድ ሰላት ላይ ግዴታ አይደለም ይላሉ። ስለዚህም ሁለቱም ተስሊማዎች የግዴታ መኖር አለባቸው። በሱና እና በፈርድ ሰላቶች ላይ ሁለት ተስሊማዎችን ማድረጉ ከተጠያቂነት የሚያድን ተግባር ነው። ማዕዘናት አስመልክቶ የሚባለው ይህ ነው።
Share

ወቅታዊ