ጥያቄ(88): ሰላትን መተው ተከትሎ የሚመጡ ህግጋት ምንድን ናቸው?
መልስ:
ሰላትን መተው ከኢስላም በማውጣት ወደ ኩፍር ደረጃ የሚያደርስ ከሆነ ይህን ተከትሎ ዱንያዊና አኼራዊ ህግጋቶች አሉ። ዱንያዊ ከሆኑ ህግጋቶች መካከል ሙስሊም ሴትን ለርሱ መዳር አይፈቀድም። ምክንያቱም አላህ አዘወጀል እንዲህ ብሏልና፦
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ምእምናት ስደተኞች ኾነው በመጧችሁ ጊዜ (ለሃይማኖት መሰደዳቸውን) ፈትኑዋቸው፡፡ አላህ በእምነታቸው ይበልጥ ዐዋቂ ነው፡፡ አማኞችም መኾናቸውን ብታውቁ ወደ ከሓዲዎቹ አትመልሱዋቸው፡፡ እነርሱ (ሴቶቹ) ለእነርሱ የተፈቀዱ አይደሉምና፡፡ እነርሱም (ወንዶቹ) ለእነርሱ አይፈቀዱምና፡፡” [አልሙምተሂና:10]
እንዲህም ይላል ፦
“(በአላህ) አጋሪ የሆኑ ሴቶች እስከሚያምኑ ድረስ አታግቡዋቸው፡፡” [አልበቀራ:221]
አንድ ሰው ሰላት ለማይሰግድ ሰው ልጁን የዳረ ከሆነ ኒካሁ ባጢል(ውድቅ) ነው። ሴቷም ለርሱ ሀላል አትሆንለትም። አንድ ባል ከሚስቱ የሚፈቀድለት ነገሮች በሙሉ ለርሱ (ካፊር በመሆኑ) አይፈቀድለትም። ምክንያቱም እርሷ በርሱ ላይ እርም ናትና። አላህ አዘወጀለ ብሎለት ተውበት ካደረገ ኒካሁ በአዲስ መልኩ ሊታሰር ይገባል።
ሁለተኛው ብይን ደግሞ ፤ ሙስሊም በሆኑ ልጆቹ እና ቅርብ ዘመዶቹ ላይ ምንም ዓይነት የወሊይነት (የሀላፊነት) መብቶችን ይነፈጋል። አንዳቸውንም ቢሆን የመዳር መብት የለውም። ምክንያቱም ካፊር ሙስሊም ላይ የበላይ ሀላፊ መሆን አይችልምና።
ሦስተኛው ብይን፤ ሙስሊም ልጆቹን የማሳደግና የመንከባከብ መብት ይነጠቃል። ምክንያቱም ካፊር ሙስሊምን የማሳደግ መብቱ የተጠበቀ አይደለም። አላህም አዘወጀለ ለከሓዲዎች በምእምናን ላይ መንገድን በፍጹም አያደርግምና፡፡
አራተኛው ብይን፤ ከብቶችን ቢያርድ ስጋው አይበላም። እርሱ የሚፈፅመው እርድ መብላቱ ሐራም ነው። ምክንያቱም ከሸሪዓው እርድ መስፈርቶች መካከል እርዱን የሚፈፅመው አካል ሙስሊም ወይም የመፅሀፍቱ ባለቤት (የሁዳ እና ነሳራ) ሊሆን ይገባል። ሙርተድ (እምነቱን በመተው ወደ ኩፍር የገባ) ከነዚህ ውስጥ አይደልምና ያረደው መብላት ሐራም ነው።
አምስተኛው ብይን፤ መካና የተቀደሱ ቦታዎች ወሰኖችን እና ክልሎችን መግባት አይፈቀድለትም። ምክንያቱም አላህ አዘወጀለ እንዲህ ብሏልና፦
“ እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህም ዓመታቸው በኋላ የተከበረውን መስጊድ አይቅረቡ፡፡” [አት ተውባ :28]
ስለዚህም በዚህ አንቀፅ መሰረት ሰላት የማይሰግድን ሰው መካ እንዲገባ ማንም ሊያመቻች አይገባም።
አኼራዊ ከሆኑ ብያኔዎች መካከል ደግሞ፤ ከሞተ ጀናዛው መታጠብ፣መከፈን፣ሰላት ጀናዛ መሰገድ እና ሙስሊሞች መቃብር ውስጥ መቀበር የለበትም። ምክንያቱም ሙስሊም አይደለምና። የአስክሬኑ ጠረኑን ሰዎችን እንዳያስቸግርና ቤተሰቦቹ እሱን እያዩ እንዳይሰቃዩ ሲባል ከመኖሪያ ስፍራ ወጣ ያለ ሜዳ ተወስዶ ጉድጓድ ተቆፍሮ እንደንሰሳ መቀበር ይኖርበታል። እንዲሁም ማንኛውም ቅርብ ዘመድ ዘመዱ ሰላት ሳይሰግድ መሞቱ እያወቀ አላህ አዘወጀለ እንዲያዝንለት ዱዓ ማድረግ አይፈቀለትም። አላህ አዘወጀለ እንዲህ ይላልና፦
“ለነቢዩና ለነዚያ ላመኑት ለአጋሪዎቹ የዝምድና ባለቤቶች ቢኾኑም እንኳ እነሱ (ከሓዲዎቹ) የእሳት ጓዶች መኾናቸው ከተገለጸላቸው በኋላ ምሕረትን ሊለምኑ የሚገባ አልነበረም፡፡” [አት ተውባ 113]
“ለሙሽሪኮች ምሕረትን ሊለምኑ የሚገባ አልነበረም፡፡” የሚለው አባባል ላይ ሙሽሪኮችን አስመልኮ ነውና ሰላት የተወ ሰው ደግሞ ሙሽሪክ አይደለም ሊባል አይገባም። ምክንያቱም ከላይ ያሳለፍነው የጃቢር ሐዲስ ገሃዳዊ መልክቱ የሚጠቁመው ሰላት የተወ ሰው ሙሽሪክ መሆኑንም ጭምር ነው።
: " بين الرجل وبين الشرك والكفر ترك الصلاة"
“በሰውዬው እና በሽርክ ወይም በኩፍር መካከል ያለው መለያ ሰላትን መተው ነው።”
ሰላትን መተው አንዱ የሽርክ መገለጫ ነው። እንላለን። በመቀጠልም አላህ አዘወጀለ፤እዚህ አንቀጽ ላይ ሙሽሪክ መሆኑ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው “(ከሓዲዎቹ) የእሳት ጓዶች መኾናቸው ከተገለጸላቸው” ሲል ካፊር መሆኑ አረጋግጧል።
በቁርኣን፣በሐዲስ ፣በሰሓቦች ንግግር እና በትክክለኛው ሎጂክ መሰረት ሰላት የተወ ሰው የጀሀነም ጓድ መሆኑ ግልፅ ሆኖልናል።
የጀሀነም ጓድ የሆነበት ምክንያት እርሱ ያው እራሱ ነው። አንድ ብይን በምክንያት ከፀደቀ ያ ምክንያት ተፅእኖ የሚያሳርፍበት ነገር በሙሉ በውስጡ አቅፎ ይይዛል።
አንድ ሰው ሰላትን በመተዉ የተነሳ አኼራ ላይ ተከትለው ከሚመጡ ብያኔዎች መካከል ፤ የቂያማ ቀን ከፊርዓውን፣ሃማን፣ቃሩን፣ኡበይ ኢብኑ ኸለፍ እና ከኩፍር መሪዎች ጋር አብሮ ይቀሰቀሳል። ከነዚህ ጋር አብሮ የሚቀሰቀስ መኖሪያው እሳት ነው። አላህ ይጠብቀንና። ስለዚህም አንድ ሰው ሰላት ላለመተው በጣም ጥንቃቄ ሊያደርግ እና ጌታውን ሊፈራ ይገባል። አላህ አዘወጀለ በነፍሱ ላይ የጫነበትን ግዴታ ሊወጣ ይገባል። ምክንያቱም አላህ አዘወጀለ በሰውዬው ነፍስ ላይ መብት አለውና።
ምናልባትም ሰላት የማይሰግድ ሰው ኩፍሩ ከእስልምና የሚያስወጣው ነው ስትሉ ሌሎች ደግሞ ሰላት የተወ ሰው ካፊር ነው ሲባል ግዴታውን በመካድና በማስተባበል እንጂ በመዘናጋት እና በመሰላቸት የተወን አይመለከትም ኩፍሩ መለስተኛ እና ከእስልምና አያስወጣውም ፤ ብለው ከሚናገሩ ዑለማዎች ጋር ንግግራቹ ይጋጫል ብሎ የሚናገር ሰው ይኖራል።
ለዚህም ምላሻችን የሚሆነው በእርግጥ ይህ ጉዳይ ማለትም ሰላት የተወ ይከፍራል አይከፍርም የሚለው ጉዳይ በዑለማዎች መካከል የኺላፍ ርዕስ ነው። ሆኖም አላህ አዘወጀለ እንዲህ ይለናል፦
“ከምንም ነገር ያ በእርሱ የተለያዩበት ፍርዱ ወደ አላህ ነው፡፡” [አሽ ሹራ ፡10] እንዲህም ይላል፦ “በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፡፡ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው፡፡” [አኒሳእ ፡59]
ይህን የልዩነት አጀንዳ ወደ ቁርኣንና ሐዲስ ስንመልሰው ሸሪዓዊ ብያኔ የሚሽከረከረው ሰላትን በመተው ላይ እንጂ የሰላትን ግዴታነትን በማስተባበል አይደልም። ይህን ጉዳይ ያለፈው ጥያቄ መልስ ላይ በማብራራት ጠቅሰነዋል።
በመቀጠልም ስለ የአላህ አዘወጀለ ህግጋትን አስመልክቶ ከረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም የበለጠ አውቃለሁ ብሎ የሚሞግት አካል ይኖራልን? ስንል እንጠይቃለን ለፍጥረታቱ ከረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም የበለጠ መካሪ ነኝ ብሎ የሚሞግት አካል ይኖራልን? ለማስተላፍ የሚፈልጉትን መልክት ከርሳቸው ማለትም ከረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም የበለጠ መግለፅ እችላለሁ ብሎ የሚሞግት አለን? እነዚህ አራት መገለጫዎችን አንድም አካል አዎን እችላለሁ ብሎ የሚሞግታቸው ነገሮች አይደሉም።
ከመልዕክተኛው ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም በላይ አዋቂ ከሌለ ፣ለፍጥረታቱ ከርሳቸው ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም በላይ መካሪ ከሌለ ፣ለማስተላፍ የሚፈልጉትን መልክት ከርሳቸው ማለትም ከረሱል ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም የበለጠ መግለፅ የማይችል አካል ከሌለ፤እሳቸው ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦
“በእኛ(ሙስሊሞች)ና በከሃዲዎች መካከል ያለው ቃል ኪዳን ሰላት ነው እርሷን የተወ በእርግጥ ከፍሯል”
እንዲህም ብለዋል፦
“በሰውዬው እና በሽርክ ወይም በኩፍር መካል ያለው መለያ ሰላትን መተው ነው”
ከዚህ በላይ ካፊር የሚለው ሁክም የተሰጠበት ምክንያት መተው መሆኑን የሚገልፅ ፍንትው ያለ ገለፃ ምን ሊኖር ይችላል!
በተጨማሪም "ሰላት ግዴታነቱ ያስተባበልን ነው" ብሎ የሚገልፅ ሰውን የመልክተኛውን ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ንግግር በሁለት መልኩ አዛብተሃል እንለዋለን።
አንደኛው፤ካፊር የሚለውን ባህሪ ያሰጠው ሁክም ከስራ ውጭ አድርገሃል።
ሁለተኛው ደግሞ ፤ከሁክሙ ጋር ተያያዥ አድርገህ ያስቀመጥከው መገለጫ ሀዲሱ ላይ የተገለፀው (ማስተባበል የሚለው)ቃል በጭራሽ እሱን አይጠቁመውም።
" فمن تركها فقد كفر"؟
“ሰላትን የተወ በርግጥ ከፍሯል።” የሚለው የመልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ንግግር ላይ "ያስተባበለ" ብሎ መተርጎም ቃላትን ከማዛበት ውስጥ ይካተታል። በተጨማሪም ሰውዬው የሰላት ግዴታነትን ካስተባበል ቢሰግድም ካፊር ነው እንላለን። ግዴታ መሆኑን ካስተባበለ በኋላ ቢሰግድ አይከፍርም ትላለህን? ብለን በምንጠይቅበት ሰዓት “አይ! ግዴታ መሆኑን ካስተባበለማ ቢሰግድም ካፊር ነው።” በማለት ይመልስልናል። እንግዲያውስ የሀዲሱን ፅንሰ ሀሳብ ጥሰሃል እንለዋለን። ምክንያቱም ሐዲሱ ላይ የሚለው ፦ “ሰላትን የተወ ….” ነው። አንተ ግን የሐዲሱ ፅንሰ ሀሳብ "ሰላት ግዴታ መሆኑን ያስተባበለ" በሚል ተርጉመሃል ስለዚህም በአንተ ሙግት መሰረት በተዘዋዋሪ ሰውዬው ካፊር የሚለው ሁክም ይሰጠው ዘንድ ሰላት ግዴታ መሆኑን በማስተባበል የተወ በመሆኑ እንጂ ሰላት ሳይተው ግዴታነቱን ያስተባበለን ነው የሚመለከተው እያልከን ነው። ይህን ደግሞ በቀጥታ አትናገረውም። በዚህ ንግግር መሰረት ደግሞ ሰላት መሰገድ ሳያቆም የሰላትን ግዴታነትን ያስተባበለ ሙስሊም ነው እንደማለት ይቆጠርብሃል። ስለዚህ ከዚህ ማብራሪያ ግልፅና ፍንትው ያለልን ነገር ቢኖር ሰላትን በመሰላቸት ወይም በስንፍና የተወ ካፊር ይሆናል። የሚለው አቋም ትክክለኛ ነው። ምክንያቱም ሰላት ግዴታ አይደለም ብሎ ያስተባበለ ሰገደም አልሰገደም እርሱ ካፊር ነውና።
ይህ ሙግት ማለትም "ሰላትን የተወ ሰው ካፊር የሚሆነው ግዴታ መሆኑን ያስተባበለ ነው" የሚለው ሙግት፤ ቀጣዩን አንቀፅ በማስመልከት ከኢማሙ አህመድ ረሂመሁላህ የተዘገበው አባባል ጋር እጅግ ተመሳሳይነት አለው። እርሱም፦ አላህ እንዲህ ይላል፦
“ምእመንንም አስቦ የሚገድል ሰው ቅጣቱ በውስጧ ዘውታሪ ሲኾን ገሀነም ናት፡፡ አላህም በርሱ ላይ ተቆጣ፡፡ ረገመውም፡፡ ለእርሱም ከባድ ቅጣትን አዘጋጀ፡፡” [አኒሳእ:93]
ከፊል ሰዎች ይህን አንቀፅ አስመልክቶ ሙእሚን መግደል የጀሀነም የሚዳርገው ሙስሊም መግደል ሐላል ነው በሚል እምነት የገደለ እንጂ አማኝን በመግደል ብቻ አይደለም የሚሉ ሰዎች ንግግራቸው ኢማሙ አሕመድ ዘንድ ሲደርስ ኢማሙ አሕመድ ረሂመሁላህ በንግግራቸው ተገርመው እንዲህ አሉ “ሙስሊም መግደል ይቻላል የሚል እምነት ካለውማ ቢገድልም ባይገድልም ካፊር ይሆናል። ጀሀነም የሚዘወትርበት ምክንያት አንቀፁ ሲገልፅ መግደል የሚለው ላይ ሁክሙ አንጠልጥሎ እንጂ በሌላ አይደልምና።”
ይህ (የኢማሙ አህመድ) አባባል ሰላት እዚህ ቦታ ላይም ሊባል ይገባል። እኛ ሰላት የተወ ሰው ይከፍራል ብለን ስንናገር የአላህ አዘወጀለ እና የመልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ሰላም ቃል የማይጠቁመውን ከመናገር ከዚህ ተግባር የጠራን ለሞሆኑ ወደ አላህ ንፁህነታችን እናስጠጋለን። ሰላትን መተው ኩፍር ነው ስንል ሐላል ነው ሐራም ነው ብሎ ፈትዋ እንደመስጠትም እንቆጥረዋለን። ስለሆነም ይህን ከሸሪዓው መረጃ ሳይኖር ፍርድ መስጠት እንደማይቻል እምነታችን ነው። ሰዎችን ለማክፈር መዳፈር አላህ አዘወጀለ ግዴታ ያላደረገውን ግዴታ ወይንም ሐራም ያላደረገውን ሐራም እንደማድረግ ይቆጠራል። ምክንያቱም ሁሉም ህግጋት ተመላሽነታቸው ወደ አላህ አዘወጀለ ነውና። ሀላልን ሀላል ማድረግ፣ሀራምን ሐራም ማድረግ፣ ዋጂብን ግዴታ ማድረግም አለማድረግ፣ማክፈርም ሆነ አለማክፈር ሁሉም ነገር የአላህ አዘወጀለ መብቶች ናቸው። ስለዚህም አንድ ሰው የአላህ አዘወጀለ እና የመልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ንግግር የሚያስከትለውን መናገር ይኖርበታል እንጂ ይህን ለሚፃረር ነገር ምንም ግምት ሊሰጥ አይገባም።