ጥያቄ(85): በሸሪዓ ሰላት ሁክሙ ምንድ ነው? አሳሳቢነቱስ?
መልስ:
ሰላት ማለት ከኢስላም ማዕዘናት መካከል እጅግ ጠንካራው ማዕዘን እንዲያውም ከሸሃደተይን(ከሁለቱ ምስክሮች) ማለትም አሽሀዱ አን ላኢላሃ ኢለለሁ ወአሽሀዱ አነ ሙሐመድ ረሱሉላህ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ የኢስላም ማዕዘን ነው። እንዲሁም በአካል ከሚፈፀሙ ተግባሮች እጅጉ የጠነከረ ተግባር ነው። ከመልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ፀድቆ በመጣው ሐዲስ መሰረት ሰላት የኢስላም ምሶሶ ነው። መልዕክተኛው (ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) ፦“የኢስላም ምሦሶው ሰላት ነው።” ብለዋል። በመልክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ላይ ሰላት ግዴታ የተደረገው የሰው ልጅ ሊደርስበት ከማይችልበት ከላቀው ስፍራ ላይ ሆነው ሳለ ነበር። ማንም ጣልቃ ሳይገባ በተከበረው ስፍራ በተከበረው ለሌት መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ ሰላት ግዴታ ሆነ። መጀመሪያ ሀምሳ ግዜ እንዲሰግዱ ግዴታ ነበር። ነገር ግን አላህ አዘወጀለ ለባሮቹ በማቅለል በተግባር አምስት ቢሆንም ሚዛን ላይ ደግሞ ሀምሳ ሰላት ሆነ። ይህ ሰላት በጣም አሳሳቢ እና አላህ አዘወጀለ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ተግባር መሆኑን ያሳያል። የሰው ልጅ አብዛኛውን ወቅቱን ሰላት ላይ ሊያሳልፍ ይገባል። ለዚህም መሰረት ቁርኣን ሐዲስ እና የሙስሊሞች (ሊቃውንት) ስምምነት ሰላት ግዴታ መሆኑን ይጠቁማል። ቁርኣን ላይ አላህ አዘወጀለ እንዲህ ይላል፦
መልዕክተኛው (ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሙዐዝ ኢብኑ ጀበልን ረዲየላሁ ዐንሁ ወደ የመን በላኩት ጊዜ፦ “በቀንና በለሊት ውስጥ አምስት ሰላቶችን አላህ ግዴታ እንዳደረገባቸው አሳውቃቸው(አስተምራቸው)።” ብለውታል።
ሙስሊሞች ሰላት ግዴታ መሆኑን በአንድ ድምፅ ተስማምቷል። ለዚህም ሲባል ዑለማዎች የአምስት ጊዜያት ሰላቶች ወይም አንዱን ሰላት ግዴታነት ካስተባበል ካፊር ሙርተድ ይሆናል ብለዋል። ምናልባት አዲስ ሰለምቴ ካልሆነ ተውበት እስካላደረገ ደሙም ንብረቱም ሀላል ይሆናል። ሰለምቴ ከሆነ ባለማወቁ የተነሳ ዑዝር ሊሰጠው ይችላል። ሆኖም የሰላትን ሑክም ያውቅ ዘንድ እናስተምረዋለን ከዚያም የሰላት ግዴታነት በማስተባበል ላይ ከቀጠለ ካፊር ይሆናል። ስለዚህም ሰላት ግዴታ ከሆኑ አምልኮቶች እጅግ ከባድ የሆነው ግዴታ ነው።