ጥያቄ(70): ውዱእን የሚያበላሹ ነገሮች ምንድን ናቸው?
መልስ:
ውዱእን የሚያበላሹ ነገሮች ከመጥቀሳችን በፊት ብዙዎች ዘንድ የሚሰወር ቁም ነገርን ማስታወስ እወዳለሁ እርሱም አንዳንድ ሰዎች ኢስቲንጃእ ወይም ኢስቲጅማር(በድንጋይና በደረቅ ነገሮች ማደራረቅ) ከውዱእ ግዴታዎች ናቸው ብለው ይገምታሉ፤ስለዚህም በተደጋጋሚ ከሚጠይቁት ጥያቄዎች መካከል አንድ ሰው በቀኑ የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ ውዱእን አጥፍቶ ከዚያም ለዙህር አዛን ሲባል ውዱእን አላበላሸም ነበር፤ ከዚያም ውዱእን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያጠፋ ውዱእን አላደረገም፤ ዙህር አዛን ሲባል ብልቴን ዳግም ማጠብ አለብኝ ወይስ የለብኝም? ይላል።በዚህን ግዜ ብልትህን አትጠብ እንላለን።ምክንያቱም ብልትህን ማጠብ የሚኖርብህ በሽንት ወይም በሰገራ የተነሳ ነጃሳውን ለማስወገድ ሲባል ነውና መጀመሪያውን ከነጃሳ ካልተጥራራ ጠሃራ ሆኗል አይባልም። በዚህን ግዜ በኢስቲንጃ እና በውዱእ መካከል ምንም ግንኙነት የለውም። ይህን ቁም ነገር ሰዎች ልብ ይሉት ዘንድ ማስታወስ እወዳለሁ።
ውዱእን የሚያበላሹ ነገሮችን በማስመልከት የሚከተሉት ናቸው፦ ሰጋራ፣ሽንት፣ፈስ፣እንቅልፍ፣የግመል ስጋ መመገብ ናቸው። ሰገራና ሽንት ውዱእን እንደሚያበላሹ ሰፍዋን ኢብኑ ዐሳል ረዲየላሁ ዐንሁ ያስተላለፈው ሐዲስ ማስረጃ ሲሆን እንዲህ ይላል፦ የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) መንገደኛ ከሆን ጀናባ ካልሆን በስተቀር ለሦስት ቀንና ለሦስት ለሌት ኹፋችን እናዳናወልቅ አዘውናል። ነገር ግን ከሰገራ፣ከሽንት እና ከእንቅልፍ ግን (ኹፍ ሳናወልቅ ውዱእ እንድናደርግ አዘውናል)። ይህ ሐዲስ ቁርኣን ላይ በሰገራ ወቅት ውዱእ ማድረግ በማዘዝ የመጣውን መልክት ያጠናክራል። አላህ (ሱብሃነሁ ወተዐላ) እንዲህ ይላል፦
ፈስ ውዱእን እንደሚያበላሽ ደግሞ ዐብዱላህ ኢብኑ ዘይድ እና አቡሁረይራ ያስተላለፉት ሐዲስ ላይ ሰላት ውስጥ ፈስ የወጣ እየመሰለው የሚቸገረውን ሰውዬው ጠቅሰው፤ የአላህ መልክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) እንዲህ ብለዋል፦
ይህ ሐዲስ ፈስ ውዱእን እንደሚያበላሽ ማስረጃ ነው። እነዚህ አራት ነገሮች ማለትም ሽንት፣ሰገራ፣ፈስ እና እንቅልፍ ውዱእን የሚያበላሹ ነገሮች ናቸው።
ነገር ግን እንቅልፍ በጣም የጠለቀ ማለትም ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ካልሆነ ውዱእን አያበላሽም። ከእንቅልፉ የተነሳ ከሰውነቱ የሆነ ነገር ይውጣ አይውጣ የማያውቅበት ደረጃ ሲደርስ ብቻ ነው እንቅልፍ ውዱእን የሚያበላሸው። ምክንያቱም ውዱእን የሚያበላሽ ነገር በእንቅልፍ ሰዓት ይከሰታል የሚል ግምት ስለሚያሳድር እንጂ እንቅልፍ በራሱ ውዱእን አያበላሽም።አንድ ሰው ሰላት ውስጥም ሆነ ከሰላት ውጭ ቢያንገላጅጅና ውዱእን ቢያበላሽ እራሱን የሚያውቅበ ና የሚያስተውልበት ደረጃ ላይ ከሆነ ረጅም ሰዓትም እንኳ ቢያንቀላፋ ውዱኡ አይበላሽም። ተደግፎም ሆነ ተጋድሞ ቢተኛ በየትኛውም አኳሃን ላይ ቢሆን ውዱኡ አይጠፋም፡ውዱኡ የሚበላሸው ማስተዋሉ እና መንቃቱ ላይ እንጂ በአኳሃኑ ወይም በአቀማመጡ ላይ አይደልም። የሚያንቀላፋው ሰው ምናልባት ውዱእ ቢያጠፋ የሚያስተውልበት ደረጃ ላይ ከሆነ ቢደገፍም ቁጢጥ ብሎ ቢቀመጥም ቢንጋለልም በየትኛውም አኳሃን ላይ ቢሆን ውዱኡ አይበላሽም፤ እንዳለ ይቆያል።
አምስተኛው ውዱእን የሚያበላሸውን ነገር የግመል ስጋ መመገብ ሲሆን ከመልክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) በትክክለኛ ሐዲስ ተዘግቦ እንደመጣው የግመል ስጋን ከተመገብን በኋላ ውዱእን እናድርግ ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ አዎን በማለት መልሰዋል። የፍየል ስጋን ከተመገብን በኋላስ? ሲባሉ “ከፈለግክ አድርግ።” በማለት መለሱ። የግመል ስጋ አስመልክቶ “አዎን (ውዱእ አድርጉ)” ማለታቸው የፍየል ስጋን አስመልክቶ ደግሞ “ከፈለግክ ውዱእ አድርግ” ማለታቸው የግመል ስጋ ከተመገቡ በኋላ ውዱእ ማድረግ አለማድረግ የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ ያሳየናል። እንዲያውም ግዴታ መሆኑን ያሳያል። ግዴታ ባይሆን ኖሮ ጉዳዩ ወደ ፍላጎት ወይም ወደ ምርጫ ይመለስ ነበር። ከመልክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) በትክክለኛ ሰነድ ተዝገቦ እንደመጣው፦ “መልዕክተኛው ከግመል ስጋ ውዱእን እንዲያደርግ አዘውታል።” ከዚህም በመነሳት የሰው ልጅ የግመል ስጋን ትንሽም ይሁን ብዙ ከተመገበ ውዱኡ ይበላሻል። ጥሬም ይሆን የበሰለ፣ ቀይ ስጋ ይሁን ስብ፣የሆድ እቃውን ቢሆን አንጀቱን፣ጉበትም ሆነ ልብ ወይም የትኛውም የሰውነት ክፍል ከተመገበ ውዱእን ያበላሻል። ምክንያቱም ሐዲሱ ላይ ይኸኛው ከዚህኛው ስጋ ይለያል የሚል መልዕክት የለውምና። የአሳማ ስጋ መብላት ሁሉንም አካሉ የሚመልከት ከሆነ እንዲሁ የግመል ስጋ መብላትም ውዱእን ያበላሻል ሲባል ሁሉንም የሰውነት ክፍሉ ይመለከታል። አላህ እንዲህ ይላል፦
የአሳማ ስጋ መመገብ ክልክልነቱ ሁሉንም የሰውነት አካሉን የሚያካትት ነው። እንደዚሁም ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) የግመል ስጋ ከተመገብን በኋላ ውዱእ እናድርግ ብለው ሲጠይቁ የግመል ሁሉንም የሰውነት ክፍሉን ይመለከታል። በሸሪዓችን አንድ የሰውነት ክፍል ከሌላኛው የሰውነት ክፍል እንደሚለይ የሚያሳይ ማስረጃ የለም። እንዲያውም ሁሉም የሰውነት ክፍል በሑክም ደረጃ ተመሳሳይ ፍርድና ብያኔ ይሰጠዋል። በተለይም የግመል ስጋ መመገብ ውዱእን ለምን እንደሚያበላሽ ጥበቡ ለኛ ግልፅ ነው እንጂ ሚስጢሩና ጥበቡ የማይታወቅ እንዲያው ውዱእ ማድረጉ ለተዐቡድ ብቻ የታዘዘ አይደለም።
ለዚም ሲባል ውዱእ ኖሮት ከግመል የትኛውንም ክፍሉ የተመገበ ውዱእን ማደስ ይጠበቅበታል። በመቀጠልም አንድ ሰው ውዱዕ ኖሮት ውዱእ ይጥፋ አይጥፋ በዚህ ላይ ጥርጣሬ ካለበት ለምሳሌ ሽንት ወይም ፈስ ወጥቶኛል ወይስ አ ልወጣኝም ብሎ ቢጠራጠር አሊያም የተመገበው ስጋ የግመል ይሆን የፍየል ስጋ የሚል ጥርጣሬ ቢያድርበት ውዱእን ማደስ አይጠበቅበትም። ምክንያቱም የአላህ መልክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) አንድ ሰው ሰላቱ ውስጥ ከገባ በኋላ ውዱእን ያጠፋ ይመስለዋል ምን ያድርግ? ተብለው ተጠየቁ። እሳቸውም፦ “ድምፅ ካልሰማ ወይም ሽታ ካላሸተተ ከሰላት አይውጣ ወይም አያቋርጥ።”አሉ። ማለትም እርግጠኛ እስኪሆን ድረስ፣በስሜት ህዋሱ እስኪደርስበት ድረስ ውዱእ አይበላሽም። ምክንያቱም አንድ ነገር በእርግጠኝነት መወገዱ እስካላወቅን ድረስ ባለበት ይዘት ላይ ይቆያል ። ስለዚህም ውዱእ መወገዱ እና መበላሸቱ እስካላረጋገጥን ድረስ ውዱእ መኖሩ እንዳለ ይዘልቃል።