Back to Top
ጣኦት ማለት ምን ማለት ነው ስያሜውስ ከየት የመጣ ነው?

ጥያቄ(50): ጣኦት ማለት ምን ማለት ነው ስያሜውስ ከየት የመጣ ነው?
መልስ:

ጣኦት(ጣጉት) የሚለው ጡግያን (ወሰን ማለፍ) ከሚለው ስረወ ቃል የተወሰደ ነው። ይህን ትርጉም ከሚሰጡን የቁርኣን አንቀጾች መካከል ፦

“እኛ ውሃው ወሰኑ ባለፈ ጊዜ በምትሄደው መርከብ ውስጥ ጫንናችሁ፡፡” [አልሓቃህ፡11]
ጣጉትን አስመልክቶ ከተሰጡ ጥሩ ትርጓሜዎች መካከል ኢብኑል ቀይም የጠቀሱት ይገኝበታል። እርሱም፦ ጣዖት ማለት ከሚመለክ ወይም ከሚከተሉት ወይም ከሚታዘዙት ሁሉ ባሪያው ወሰን ያለፈበት ነገር በሙሉ ጣዖት ይባላል።” [አዕላሙል ሙወቂዒን፡1/64]

ከአላህ ውጭ(ፈቅደው) የሚመለኩ ነገሮች ጣዖቶች ይባላሉ። ወደ ጥመት የሚጣሩ መጥፎ ዑለማዎች ጣዖት ይባላሉ።ማለትም ወደ ቢድዓ ፤አላህ ሐራም ያደረገውን ሐላል ወደ ማድረግ ወይም ሐላሉን ሐራም ወደ ማድረግ የሚጣሩ ወይም ከሸሪዓ እንዲወጡ የኢስላም ስርዓትና ደንብን የሚጥሱ ህግጋትን ከኩፍር ሀገር በማምጣት በርሱ መፍረድን ለመሪዎች አሳምረው የሚያቀርቡ እነዚህ ሰዎች ወሰናቸውን አልፈዋልና ጣዖታት ይባላሉ። ምክንያቱም የአንድ ዓሊም ወሰኑ መልዕክተኛው ይዘውት የመጡትን መከተል ነው። በእውነታው የተመለከትን ከሆነ ዑለማዎች ማለት የነቢያት ወራሾች ናቸው። ከነቢያት ህዝብ መካከል ዑለማዎች የነቢያትን እውቀታቸውን፣ ተግባራቸውን፣አኽላቃቸውን፣ ደዕዋቸውን ይወርሳሉ። ይህን ወሰናቸውን ከተላለፉና ለመሪዎች ከሸሪዓው ማፈንገጥን የሚያስውቡ ከሆነ ጣዖት ይባላሉ። ምክንያቱም ሸሪዓውን መከተል ሲኖርባቸው በመጣሳቸው ጣዖት ይሰኛሉ።

 ”ወይም ከሚታዘዙት”  የሚለው የኢብኑል ቀይም አባባል የሚታዘዙት ሲሉ የሚፈልጉበት፦ በሸሪዓው ወይም በቀደር ሰዎች የሚታዘዙቸውን መሪዎችን ለማለት ፈልገውበት ነው። በቁርዓንና በሐዲስ የሚያስተዳድሩ ከሆነ በቀደር ሰዎች እንደሚታዘዟቸው ሁሉ በሸሪዓውም እንታዘቸዋለን። ስለዚህም መሪዎች ህዝቦ ቻቸውን ሸሪዓን በማይጥስ ነገር ሲያዟቸው መስማትና መታዘዝ ይኖርባቸዋል። በዚህም ባለነው ሁኔታ እና ገደብ መሰረት መሪዎችን መታዘዝ አላህን እንደመታዘዝ ነው የሚቆጠረው። ስለዚህም የአንድ ሀገር መሪ ያዘዘውን ስንተገብር ወደ አላህ መቃረቢያ የሆነ ኢባዳን የፈፀምን ያህል ሊሰማን ይገባል። ይህ እንደ ዒባዳ ይቆጠርልን ዘንድ ማስተዋል ያስፈልገናል። ምክንያቱም አላህ እንዲህ ይላልና ፦

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፡፡ መልክተኛውንና ከእናንተም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፡፡” [አኒሳእ፡59]

በአቅም ያህል እነሱን  እነሱን መታዘዝ ሲባል ባለስልጣኖች በስልጣናቸው ሀይለኛ ሲሆኑ ሰዎች ሳይወዱ በግዳቸው ሳያምኑበትም ይታዘዟቸዋል። መሪዎችን መታዘዝ ከእምነት የመነጨ (ኢባዳ መሆኑ በመቁጠር) ሊሆን ይችላል። ይህኛው ቢሆን ነው ለመሪዎችም ሆነ ለህዝባቸው የሚጠቅማቸው። ምናልባትም መሪያቸው ጉልበት እና ጥንካሬ ስላለው የሚጥሰውን አካል ሊቀጣ ስለሚችል ሰዎች ሊፈሩትና ሊብረከረኩ ይችላሉ። ስለዚህም ሰዎች መሪዎችን መታዘዝ አስመልክቶ ለብዙ ይከፈላሉ።

አንዳንዴ ፦ ኢማናዊ እና ስልጣናዊ ጉልበት ሊጠነክር ይችላል። ይህ ከሁሉም በላይ በላጭ ነው።

አንዳንዴ ደግሞ፦ ኢማናዊ እና ስልጣናዊ ጉልበት ሊዳከም ይችላል። ይህ ለመሪውም ሆነ ለህዝቡ እጅግ አደገኛ እና ዝቅተኛው ደረጃ ነው። ምክንያቱም ኢማናዊ እና ስልጣናዊ ጉልበት ሲዳከም የአስተሳሰብ፣ የአኽላቅና የተግባር ስርዓት የለሽነት ይነግሳል።  ሦስተኛው ደረጃ ደግሞ ኢማናዊ ጉልበት ሲጠናከር ስልጣናዊ ጉልበት ሲዳከም ነው። ይህ መካከለኛው ደረጃ ሲሆን የኢማን ወይንስ የስልጣን ጉልበት ቢጎለብት ይሻላል የሚለው ጉዳይን አስመልክቶ   እንደ ውጫዊ ገፅታ ከተመለከትን የስልጣን ሀይል ሲጎለብት ለህዝቡ ህልውና የሚሻለው ይህ ነው። ነገር ግን ስልጣኑ ከመዳከሙ የተነሳ የስልጣኑ ጉልበት የማይታይ የሆነ እንደሆን ስለዚያ ህዝብ እጣፈንታ አጠይቅ! ምክንያቱም የህዝቡ ኢማን መዳከም ሲደመርበት እጅግ መጥፎ ተግባራት ላይ ይወድቃሉ። የህዝቡ ኢማን ተጣናክሮ የስልጣን አቅም የሚዳከም ከሆነ ገፅታው ከላይኛው ዝቅ ያለ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በህዝቦች እና በአላህ መካከል ያለውን አስመልክቶ ከሆነ የምናወራው የስልጣን ከልካይ ሲጠፋ ለህዝቡ የሚበጀው ይህ ይሆናል።

ለማንኛውም አራቱ ደረጃዎች እነዚህን ይመስላሉ።  ዋናው ቁም ነገር ግን መሪዎች ሸሪዓን ሳይጥሱ የሚያዙን ትዕዛዝ ስንፈፅም ወደ አላህ የሚያቃርበን ተግባር መሆኑ ልናምንበት ይገባል። ኢብኑል ቀይም፦

“ጣዖት ማለት ከሚመለክ ወይም ከሚከተሉት ወይም ከሚታዘዙት ሁሉ ባሪያ ወሰን ያለፈበት ነገር በሙሉ ጣዖት ይባላል።” ያሉት ባለስልጣን ወይም መሪዎች የሚያዙት ነገር ከአላህና ከመልክተኛው ትዕዛዝ ሊቃረን ስለሚችል ነው። ስለዚህም ከአላህና ከመልክተኛው ትዕዛዝ የሚቃረን ትዕዛዝ ሲያዘን አንሰማውም አንታዘዘውም። አላህን በማመፅ ላይም ፍፁም ልንታዘው አይገባም። ምክንያቱም እነሱን መታዘዝ የአላህንና የመልክተኛውን ትዕዛዝ ተከትሎ ሲመጣ ነው የምንታዘዛቸው። ከአንቀፁ እንደምንረዳው፦ “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፡፡ መልክተኛውንና ከእናንተም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፡፡” [አኒሳእ፡59]

የስልጣን ባለቤቶችን በልቁ ታዘዙ አላለም። ስለዚህም እነሱ መታዘዝ ለብቻው ያለገደብ አይደልም የሚለውን አንቀጹ የሚጠቁመው። እንዲያውም የአላህንና የመልክተኛውን ትዕዛዝ ተከትሎ ሲመጣ ነው እነሱን የምንታዘዘው።  መታዘዝ የሚገባው በመልካም ነገር (ሸሪዓው መልካምነቱን ባረጋገጠው ነገር) ላይ ብቻ ነው የሚል መልክት ከመልክተኛው ፀድቆ መጥቷል። ሸሪዓው መጥፎ ያለው ነገር ላይ ማንኛውም ፍጡር ሊታዘዙት አይገባም። ወላጆችህ እንኳ ቢሆኑ አላህ በማመፅ ላይ ካዘዙህ ልትታዘዛቸው አይገባም። ምክንያቱም የአላህ ትዕዛዝ ከማንኛውም ትእዛዛት ተቀዳሚ ነውና። አንድ ሰው አላህን በማመፅ ጉዳይ ላይ ባለስልጣን ወይም መሪውን ከታዘዘ በዚህ ድርጊቱ ወሰኑን አልፏል።
Share

ወቅታዊ