ጥያቄ(22): በመላኢካ ማመን የሚለው ርእስ አስመልክቶ የሚጨምሩት ማብራሪያ ይኖራችኋል ወይንስ ወደ ቀጣዩ የእምነት ማእዘን እንሸጋገር።
መልስ:
ሁለተኛው የእምነት ማእዘን ማለትም በመላኢካ ማመን አስመልክቶ የቀረን ነገር ቢኖር በነሱ ማመን ሲባል ጥቅል እና ዝርዝር የእምነት አይነት አለ። ይኸውም መላዕክቱን አስመልክቶ ዝርዝር ገለፃ ከመጣ በዝርዝር ማመን ግዴታ ይሆንብናል። ስለዚህም እንዲህ እንላለን፦ በጂብሪል፤በሚካኤል፤በኢስራፌል፤በመለከል መውት ፤ማሊክ የእሳት ዘበኛ እና የመሳሰሉት በዝርዝር እናምናለን።በስሙ ተጠርቶ ያልመጣውን ደግሞ ስሙን ሳንሰይም በጥቅል እናምናለን። በመላክት በጥቅሉ እናምናለን። መላክት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ሲሆን የቁጥራቸውንም ብዛት ከአላህ በስተቀር የሚያውቀው የለም። መልዕክተኛው እንዲህ ብለዋል፦ “ሰባተኛው ሰማይ ላይ የሚገኘው በይተል መእሙር ላይ በየቀኑ ሰባ ሺ መላክት ይገቡ እና ጠዋፍ ያደርጋሉ ከወጡም በኋላ ዳግም ተራ አይደርሳቸውም።” በሌላ ሐዲስ መልዕክተኛው እንዲህ ሲሉ ብለዋል፦ “በሰማይ ላይ አራት ጣት የሚያሳርፍ ስፍራ እንኳ የለም።ለሰላት የቆመ አሊያም ሩኩዕ ወይም ሱጁድ የሚያደርግ መላኢካ ስፍራው ቢይዝ እንጂ።” በሸሪዓው ስራቸው በዝርዝር የመጣውን ካልሆነ በስተቀር የማንንም ስራ ማወቅ አንችልም። ስራቸው፤ባህሪያቸው የስራ ሐላፊነታቸው በሸሪዓ ማስረጃዎች በዝርዝር ከመጣ ዝርዝር በሆነ መልኩ ማመን ግዴታ ይሆንብናል። በዝርዝር ማስረጃ ያልመጣለትን ደግሞ በጥቅሉ ማመን ግዴታ ይሆንብናል።
እነዚህ መላክት የሰው ልጅ ጋር የሌለው ሐይልና ጉልበት ለነርሱ መኖር ከአላህ ተዓምራቶች አንዱ ነው። ስለዚህም በመላክት ስናምን በአላህ ሀያልነት አመንን ማለት ነው። መላክት ምእመናን ስለሆኑ እና አላህ ያዘዛቸውን በአግባቡ ስለሚፈፅሙ ልንወዳቸው ይገባል። ከመላዕክት አንዱን ጠላት አድርጎ የያዘ ካፊር የሚል ሑክም ይሰጠዋል።
አላህ እንዳለው፦
ያም ሆነ ይህ መላክት ሁሉንም ልንወዳቸው ይገባል። ምክንያቱም ሁሉም የአላህ ባሮች እና ትዕዛዙን የሚፈፅሙ ናቸውና አንዳቸውንም ልንጠላ አይገባም።