Back to Top
የእምነት መሰረቶችን መግለፅና ማብራራት ይቀረናል (እና ቢያብራሩልን)።

ጥያቄ(21): የእምነት መሰረቶችን መግለፅና ማብራራት ይቀረናል (እና ቢያብራሩልን)።
መልስ:

ኢማን ማለት መልክተኛው እንዳብራሩት ፦ “በአላህ ማመን በመላኢካ ማመን … “

 በአላህ ማመን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከላይ አሳልፈናል። በመላኢካ ማመን ሲባል ደግሞ ፦

መላኢካዎች ከሰውልጅ እይታ የራቁ (የማይታዩ) እና ከብርሃን የተፈጠሩ ናቸው።ትዕዛዙን ፈፃሚ አድርጎ ፈጥሯቸዋል። “በሌሊትና በቀንም ያጠሩታል፤ አያርፉም፡፡” [አል አንቢያ:20]

 

“አላህን ያዘዛቸውን ነገር (በመጣስ) አያምጹም፡፡ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ፡፡” (አትተሕሪም:6]

በተግባራቸው፤ በስራ ዘርፋቸውና በደረጃቸው እጅግ በጣም በርካቶች ናቸው። ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም የስራ ድርሻው ወህይን ማመላለስ ነው። ማለትም ወህይን ከአላህ በመያዝ ወደ መልክተኞች ያደርሳል። አላህ እንዳለው፦

“እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው፤ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)፡፡ ግልጽ በኾነ ዐረብኛ ቋንቋ፡፡” (አሹዐራእ:193_195] እንዲህም ይላል፦”(ቁርኣንን) ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲኾን ከጌታህ አወረደው በላቸው፡፡” [አነሕል:102]

መልዕክተኛው ጂብሪልን አላህ በፈጠረው ይዘት ሁለት ጊዜ ተመልክተውታል። አንዴ ስድስት መቶ ክንፎች ያሉት ሲሆን ከግዝፈቱ የተነሳ አድማሱን በሙሉ ሸፍኖ ተመልክተውታል።

ሌላኛው ግዙፍ ከሆኑ መላኢካዎች መካከል ሚካኤል የሚባለው መላኢካ ነው። ዝናብን በማዝነብና እፅዋትን በማብቀል የስራ ድርሻ የተሰጠው መላክት ነው። ኢስራፊል ደግሞ (የቂያም ቀን ሲቀርብ) በቀንዱ እንዲነፋ የስራ ድርሻ የተሰጠው እጅግ ግዙፍ ፍጡር ነው።በተጨማሪም ታላቅ እና ግዙፍ ፍጡር የሆነው ዐርሽን ተሸካሚ ከሆኑ መላክት አንዱ ነው።

እነዚህ ሦስት መላክቶችን በመጥቀስ መልክተኛው የለሊት ሰላታቸው ይከፍቱ ነበር። መልክተኛው በለኤት ሰላትና ዱዓቸው እንዲህ ይሉ ነበር፦ ”ጌታዬ ሆይ! የጂብሪል የሚካኤልና የኢስራፌል ጌታ ሆይ! ሰማይና ምድርን ፈጣሪ የቅርብና የሩቅ አዋቂ፤ሰዎች በሚወዛገቡበት ነገር ፈራጁአንተ ነህና በፍቃድህ ሰዎች የተወዛገቡበትን ሐቅ ምራኝ! አንተ የሻኸውን ወደ ቀጥተኛው መንገድ ትመራለህ።”

እነዚህ ሦስት መላኢካዎች በአንድ ላይ የተወሱበት ምክንያት እያንዳንዱ የስራ ድርሻው በውስጡ ሕይወት መዝራት ጋር ተያያዥነት ስላለው ነው የሚል ከኡለማዎች ገለፃ ተሰጥቶበታል። መረጃዎችን ስንመለከት እነዚህ መላክት ከሁሉም መላዕክት በላጭ እንደሆኑ እንረዳለን። መለከል መውት በመባል የተሰየመ ሩሆችን በመግደል የተመደበ መላኢካ አለ። የሰዎችን የስራ መዝገብ በመጠበቅ ስራ ሀላፊነት የተሰጣቸው መላክት አሉ። እነሱም በቀኝና በግራ የተቀመጡ መላዕክት ናቸው። የኢልም መድረክን እየተከታተሉ የሚያንዣብቡ መላክት አሉ። ከዚህ በላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሻ ካለ በዚህ ላይ ኡለማዎች የፃፉትን ያንብብ።




Share

ወቅታዊ