ጥያቄ(19): ኢማን የሚለው መልክት ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቢያደርጉልን? በተጨማሪም ማእዘኖችንም በዝርዝር እንዲያብራሩልን እንሻለን።
መልስ:
ኢማን ማለት በሸሪዓ ያለውን ትርጓሜና መልዕክተኛው የጂብሪል ሐዲሱ ላይ ኢማንን አስመልክቶ የመለሱትን ከላይ ተነጋግረናል። የጠቀስነው የኢማን ትርጓሜ ዲንን ሙሉ ለሙሉ ያካተተ ትርጉሜ ነው። እርሱም ኢማን ማለት በውስጡ የሚጠቁማቸውን መልክቶች መቀበልና መፈፀም የሚለው ትርጓሜ ነው። ይህ ትርጓሜ ኡለማዎች በ ”ኡሱል ሱናህ” እና “ዓቂዳ ኩቱቦች” ላይ የሚናገሩት ይህን መልክት ያዘለ ነው።ጅብሪል ሐዲስ ላይ ተጠቅሶ የመጣው የኢማን ማብራሪያ ፍፁም ለየት ያለ የኢማንን ፅንሰ ሀሳብ ነው። ምክንያቱ ጂብሪል ስለ ኢስላም ጠይቋቸው የውጫዊ ተግባሮችን ከጠቀሱለት በኋላ ስለ ኢማን ሲጠይቃቸው ደግሞ የውስጣዊ (የቀልብ ተግባሮችን) ጠቀሱለት።
የኢስላም ፅንሰ ሀሳቡ ውጫዊ ተግባራትን የሚወክል ቢሆንም በእርግጠኝነትና ያለምንም ጥርጥር አንድ ሰው ላኢላሀ ኢለሏህ ብሎ በአንደበት ሲመሰክር በልቡም ማመን ይጠበቅበታል። ነገር ግን ላኢላሀ ኢለሏህ በዐንደበት የሚመሰከር ስለሆነ ዐንደበታዊና ውጫዊ ተግባሮች ውስጥ ይመደባል። ማለትም ሰላት መስገድ ዘካ መስጠት ፆም መፆምና ሐጅ ማድረግ ውጫዊ ተግባራት ውስጥ ይመደባሉ። መልዕክተኛው የጠቀሷቸው የእምነት ማዕዘናት እንደሚታወቁት ስድስት ናቸው። ነብዩ “በአላህ በመላእክቶቹ፣ በመጻህፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን እንዲሁም ጥሩም ይሁን መጥፎ በአላህ ውሳኔና ፍቃድ (ቀደር) እንደሚከሰት ማመን ነው’ በማለት ለጅብሪል ነገሩት። እነዚህ የእምነት ማእዘናት እጅግ አሳሳቢ በመሆናቸው በዝርዝር ማውራት ይኖርብናል።
በአላህ ማመን ማለት በውስጡ አራት ነገሮችን አቅፎ ይይዛል። እነሱም በአላህ መኖር ማመን በጌትነቱ ፤ብቸኛ ተመላኪ መሆኑን ማመን በመልካም ስሞቹና በላቁ ባህሪያቱ ማመን ናቸው።
በአላህ መኖር ማመን ማለት: አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መኖሩን በሙሉ ልቦና ማረጋገጥ ማለት ነው።በኩራት መንፈስ ካልሆነ በስተቀር አላህ መኖሩን ያስተባበለ የለም። ይህ ፍጥረተ ዓለም በድንገት ተገኘ ወይም ተፈጠረ የሚለውን ጤናማ አዕምሮ ያለው በሙሉ አይቀበለውም። አላህ መኖሩን የሚጠቁሙ አራት መረጃዎች አሉ። አዕምሯዊ መረጃዎች፤ተፈጥሯዊ መረጃዎች በተጨባጭ የምናስተውላቸው መረጃዎች እና ሸሪዓዊ መረጃዎች ናቸው። እነዚህ አራት ነገሮች በሙሉ አላህን መኖሩን የሚጠቁሙ መረጃዎች ናቸው።
አዕምሯዊ መረጃዎችን በተመለከት ሰዎች ሊያስገኙት የማይችሏቸው ነገሮች ሲከሰቱ እዚህ ፍጥረተ ዓለም ላይ እንመለከታለን። ይህ ዩንቨርስ፤ ሰማይና ምድር እንዲሁም ውስጣቸው ያሉ ነገሩች በሙሉ ከዋክብት ተራሮች፤ወንዞች ዛፎች ተናጋሪና ተናጋሪ ያልሆኑ እንሰሳቶች እና ሌሎችም ፍጥረታት ከየት ተገኙ? እንዳው ዝም ብለው በድንገት የተከሰቱ ናቸውን? ወይስ ፍጥረተ ዓለሙ እራሱን በራሱ አስገኘ? እነዚህ ሦስት ግምቶች የሰው ልጅ አዕምሮ አንዱንም አይቀበላቸውም። ምናልባት አራተኛው ግምት ሲቀር። እርሱም አላህ አስገኛቸው ወይም ፈጠራቸው የሚለው ግምትና እምነት ሐቅ ነው።ፍጥረተ ዓለሙ በድንገት ያለምንም ነገር ተገኘ የሚለው አመለካከት አዕምሮም ሆነ ተጨባጫችን ያስተባብለዋል። ምክንያቱም እነዚህ በአይናችን የምንመለከታቸው ግዙፍ ፍጥረታት በድንገት ሊፈጠሩ አይችሉምና። ማንኛውም ተጽእኖ የሆነ ነገር ተፅእኖውን አሳራፊ እንዳለው አመላካች ነው። እነዚህ በአይናችን የምንመለከታቸው ግዙፍ ፍጥረታት እርሰ በርሱ ሳይላተምና ሳይጋጭ በዚህ ድንቅ ስርዐትና የተሰካካ ውህደት በድንገት ሊሆን ይችላል ተብሎ ፈፅሞ አይታለምም። ምክንያቱም በድንገት የተከሰቱ ነገሮች ብዙን ግዜ ክስተቶቹ የተዛቡና ስርዐት የሌላቸው ናቸው።
ያላስገኝ ተገኘ የሚለው አባባል ማለትም በድንገት ተገኘ ብለን የገለፅነው አባባል ይህ ፍፁም ሊሆን የማይችልና (ዘበት) ነው። ስለዚህም ፍጥረተ ዓለሙ በአስገኚ አካል ተገኘ ብለን መናገር ይጠበቅብናል። አላህ እንዳለው፦
ይህ! ፍጥረተ ዓለም ፈጣሪ መኖሩን ለአዕምሯችን በቂ ማስረጃ ነው። ተፈጥሯዊ ማስረጃዎች ደግሞ አላህን መኖሩን የሚጠቁሙት በጣም ግልፅ ከመሆናቸው የተነሳ ምንም ማስረጃ አይሹም። ምክንያቱም የሰውልጅ በተፈጥሮው ጌታ መኖሩን ያምናል። የአላህ መልክተኛ እንዲህ ብለዋል፦ “ማንኛውም ህጻን ልጅ ሲወለድ በትክክለኛ ተፈጥሮ (ኢስላም) ላይ ይወለዳል። እናትና አባቱ የሁዳ አሊያም ክርስቲያን አሊያም መጁሳ (እሳት አምላኪ) ያደርጉታል።” ለዚህም ሲባል ዱንያ ላይ አንድ ሰው ሳያስበው በድንገት ከባድ አደጋ ቢደርስበት በዐንደበቱ “ያ አላህ!” ወይም “ያ ረብ!” እና የመሳሰሉትን ቃላት ሳያስበው ከዐንደበቱ ሲያወጣ ይሰማል። ይህም የሰውልጅ ውስጣዊ ተፈጥሮና ስሜቱ ለዚህ እምነት (አላህ መኖር” ሳይወድ በግዱ የተፈጠረ መሆኑን አመልካች ነው።
“ሒሳዊ” ማለትም ከምናየውና ከምንሰማው ተጨባጫችን በመነሳት አላህ መኖሩን የምናቅበት ዘዴ ብዙ ነገሮች አሉ። ሰዎች ጌታቸውን ለምነውት የልመናቸው መልስ አገኙ የሚለውን ስንትና ስንት ዜናዎችን ሰምተናል! እንዲያውም እራሳችን ላይ የምናስተውለውም ነገር አለ ይኸው ለምነነው ምላሽ ሰጥቶን ያቃል። ስንትና ስንቶቹ ናቸው ያ ረብ! ብለው ጌታቸውን ለምነው ወዲያውኑ ምላሹን በተጨባጭ በአይናቸው የተመለከቱት?! ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ቁርኣን ውስጥ ብቻ እጅግ በርካታ ምሳሌዎች እናገኛለን። ለምሳሌ አላህ እንዲህ ይላል ፦
ሐዲስ ውስጥ ደግሞ እጅግ ብዙ ምሳሌዎችን እናገኛለን። ከነዚይም ሐዲሶች መካከል ቡኻሪና ሙስሊም ከአነስ ኢብኑ ማሊክ እንደዘገቡት “አንድሰ ሰው በጁምዓ ዕለት ነቢዩ ኹጥባ እያደረጉ ባሉበት ሰዓት ከፊት ለፊታቸው በኩል ባለው በር ገብቶ በመቆም እንዲህ አላቸው፦
“አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከብቶች አለቁ መንገዱም ተቋረጠ ጌታችን ዝናብ በማዝነብ ከጭንቅ እንዲያወጣን ለምኑልን? ነቢዩም(ሰ.ዐ.ወ) እጃቸውን ከፍ አድርገው “ጌታችንሆይ! አዝንብልን ጌታችን ሆይ! አዝንብልን ጌታችን ሆይ! አዝንብልን በማለት ተማፀኑ። ”ሰማይ ላይ ጉም አልነበረም። መልክተኛው ከሚንበራቸው ሳይወርዱ ዝናብ ዘንቦ በፂማቸው መካከል ተንጠባጠበ። ለሳምንት ያህልም ሳያቋርጥ ዘነበ። በሳምንቱ ጁምዓ አንድ ሰው በዚያው በር በመግባት ፊት ለፊታቸው በመቆም ቤቶች ፈረሱ ንብረታችን በጎርፍ ተጥለቀለቀ። አላህ ዝናቡን እንዲይዝልን ለምኑልን።” አላቸው መልክተኛውም እጃቸውን ከፍ አድርገው “ጌታችን ሆይ! እኛ ላይ ሳይሆን በዙሪያችን ባሉ ቦታዎች ላይ አድርገው። ብለው እጃቸው የጠቆሙበት ቦታ ላይ በአላህ ፍቃድ ደመናው ተገለጠ። ሰዎች እየተራመዱ በፀሐይ ወጥተው ሄዱ። በርካታ ሰዎች ዱዓ አድርገው ምላሹን በፍጥነት አግኝተዋል። ይህ አላህ መኖሩን የሚጠቁም “ሒሳዊ” መረጃ ነው።
ሸሪዓዊ መረጃ ደግሞ ፦ መረጃዎቹ እጅግ በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ ቆጥረን አንጨርሳቸውም። ሁሉም የቁርኣንና የሐዲስ መረጃዎች በሙሉ አላህ መኖሩን ይጠቁማሉ። አላህ በታላቁ ቁርኣን እንዳለው።
የስካሁኑ በአላህ ማመን ውስጥ አንዱን ክፍል እያብራራን ሲሆን እርሱም በአላህ መኖር ማመን የሚለው ነው።
በሩቡቢያን ኡሉሂያ አስማኡ ወሲፋት አስመልክቶ የተውሒድ ክፍሎችን ስናብራራ ሰፋ ያለ ገለፃ ከላይ አሳልፈናል።