Back to Top
ሙስሊሞ የመርየም ልጅ የሆነውን ዒሳን አስመልክቶ ያላቸው ዐቂዳ (እምነት) ምንድነው? ተገድሏል ተሰቅሏል ማለትስ በሸሪዓው ያለው ብይን ምንድነው?
       ሺርክ (በአምልኮ ማጋራት) እና አይነቶቹ

ሙስሊሞች ኢሳን አስመልክቶ ያላቸው እምነት


ጥያቄ(51): ሙስሊሞ የመርየም ልጅ የሆነውን ዒሳን አስመልክቶ ያላቸው ዐቂዳ (እምነት) ምንድነው? ተገድሏል ተሰቅሏል ማለትስ በሸሪዓው ያለው ብይን ምንድነው?
መልስ:

ሙስሊሞች የመርየም ልጅ የሆነውን ዒሳን አስመልክቶ ያላቸው እምነት፤ ባለሟል ከሆኑ መልክተኞች አንዱ ነው እንዲያውም ኡሉል ዐዝም (መካራን እና ችግርን በትግስት ተወጡ) ከሚባሉት አምስት ምርጥ ነብያት መካከል አንዱ ነው። አላህ በቁርኣኑ ሁለት ቦታዎች ላይ ጠቅሷቸዋል። ሱረቱ አሕዛብ ላይ እንዲህ ይላል፦

“ከነቢዮችም የጠበቀ ኪዳናቸውን ከአንተም፣ ከኑሕም፣ ከኢብራሒምም፣ ከሙሳም ከመርየም ልጅ ዒሳም በያዝን ጊዜ (አስታወስ)፡፡ ከእነርሱም የከበደን ቃል ኪዳን ያዝን፡፡” [አል አሕዛብ:7]

ሱረቱ አሹራ ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል። 

“ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፡፡ ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)፡፡” [አሹራ፡13]

ዒሳ ያለ አባት ከእናት ብቻ የተፈጠረ የአደም ልጅ እና ሰብዓዊ ፍጡር ነው። እርሱም የአላህ ባሪያና መልክተኛ ነው። የማይመለክ ባሪያ ሲሆን ሊያስተባብሉት የማይገባ ነብይ ነው። የፈጣሪነትና የጌትነት መለያ አንዱም የለውም። እንዲያውም እርሱ አላህ እንዳለው ነው፦

“እርሱ(ኢሳ) በርሱ ላይ የለገስንለት ለእስራኤለም ልጆች ተዓምር ያደረግነው የኾነ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡” [አዙኽሩፍ፡59]

 እርሱንም ሆነ እናቱን ከአላህ ውጭ ያሉ አምላኮች አድርገው እንዲይዙ ህዝቦቹን አላዘዘም። አላህ ያወደረለትን ብቻ ነው ያዘዛቸው።

«በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ ማለትን እንጂ ለነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡” አልማኢዳ፡117]

ዒሳ የተፈጠረው ሁን በሚለው የአላህ ቃል ትዕዛዝ ነው። አላህ እንዳለው፦

“አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አዳም ብጤ ነው፡፡ ከዐፈር ፈጠረው፡፡ ከዚያም ለርሱ (ሰው) «ኹን» አለው፤ ኾነም፡፡” [አልዒምራን፡59]

በኢሳና በመልክተኛው ሙሐመድ (صلى الله عليه وسلم ) መካከል የተላከ መልክተኛ የለም። አላህ እንዳለው ፦

“የመርየም ልጅ ዒሳም፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደእናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ» ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ በግልጽ ተዓምራቶች በመጣቸውም ጊዜ «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ፡፡” [አሰፍ፡6]

ዒሳ የአላህ ባሪያና መልዕክተኛው መሆኑ ሳያምን አንድ አማኝ እምነቱ የተሟላ ሊሆን አይችልም።  የሁዳዎች ዒሳን ከገለፁ አስፀያፊ ማንነት የፀዳ ነው። የሁዳዎች፦ እርሱ የዝሙተኛ ልጅ ነው አሉ።አላህ ይጠብቀንና እርሱ ከዝሙት ነው የተገኘው አሉ። አላህ ከዚህ ነጻ መሆኑን መስክሮለታል፤ሙስሊሞች እንዲሁ ክርስቲያኖች ከሚጓጓዙበት መንገድ የጠሩ ናቸው። እርሱና እናቱ ከአላህ ውጭ አምላክ አድርገው ስለያዙት። አንዳንዶቹ ደግሞ ፦ የአላህ ልጅ ነው በማለታቸው፤ ሌሎች ደግሞ የአላህ አንድ ሶስተኛው ነው (ስላሴን በማመናቸው)በማለታቸው ነው። ክርስቲያኖች የመርየም ልጅ የሆነውን ዒሳን ማንነት አስመልክቶ ግንዛቤያቸው የተሳሳተ ነው። ዒሳ ተገድሏል ወይም ተሰቅሏል የሚለውን አስመልክቶ አላህ በቁርኣኑ ይህ እንዳልተከሰተ በግልጽ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፦

«እኛ የአላህን መልዕክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን» በማለታቸውም (ረገምናቸው)፡፡ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም፡፡ ግን ለእነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፡፡ እነዚያም በእርሱ ነገር የተለያዩት ከእርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በእርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ (ኢሳን) ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡ ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት (እዚህ ምድር ሳለ) በእርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም፡፡ በትንሣኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይኾናል፡፡” [አኒሳእ:157-159]

ዒሳ ተገድሏል ወይም ተሰቅሏል የሚል እምነት ያለው ቁርኣንን በርግጥ አስተባብሏል። ቁርኣንን ያስተባበለ ደግሞ ካፊር ነው። ዒሳ አልተገደለም አልተሰቀለም ስንል እናምናለን። ነገርግን የሁዳዎች ተገድሏል ተሰቅሏል የሚለውን ውሸት በማራገባቸው የተነሳ ወንጀሉ እነሱ ተሸክሙት እንላለን። እርሱን ገደልነው ይላሉ እውነታው ግን አልገደሉትም አልሰቀሉትም። ነገርግን አምሳያውን ይዘው ገደሉት።ከነርሱ መካከልም የዒሳን መልክ አለበሰውና እርሱ መስሏቸው ይዘውት ሰቀሉት ገደሉትም። እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን አሉ። ስለዚህም በአንደበታቸውም ሰቅለነዋል ገድለነዋል ብለው በማረጋገጣቸው የተነሳ ወንጀሉን የሁዳዎች ይሸከሟታል። ዒሳ ግን ከተባለው ነገር በሙሉ አላህ ነጻ አድርጎታል ከየሁዳዎች ሴራም ጠብቆ  ወደ ሰማይ አሳርጎታል። የመጨረሻው ቀንም ሲቃረብ ወደ ምድር በመውረድ በነቢዩ ሙሐመድ (صلى الله عليه وسلم ) ሸሪዓ (ህግ) ያስተዳድራል ከዚያም የተወሰነለት ሞት  አይቀርለትምና ይሞታል፤መሬት ውስጥ ይቀበራል። ሌሎች የሰው ልጆች ከቀብራቸው እንደሚቀሰቀሱት እሱም ዳግም ይቀሰቀሳል። አላህ እንዳለው፦

“ከእርሷ (ከምድር) ፈጠርናችሁ፡፡ በእርሷም ውስጥ እንመልሳችኋለን፡፡ ከእርሷም በሌላ ጊዜ እናወጣችኋለን፡፡” [ጧሃ:55]

እንዲህ ብሏል፦

«በእርሷ ላይ ትኖራላችሁ፡፡ በእርሷም ላይ ትሞታላችሁ፡፡ ከእርሷም ውስጥ ትወጣላችሁ» አላቸው፡፡ [አል አዕራፍ፡25]

 




Share

ወቅታዊ