Back to Top
ዲነል ኢስላም ማለት ምን ማለት ነው?
   ዐቂዳ (እምነት ነክ ጉዳዮች)

የእስልምና ሐይማኖት ምንነት


ጥያቄ(48): ዲነል ኢስላም ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ:

ኢስላም ማለት ጥቅላዊ ትርጓሜው፦ አላህ ባሮቹን በአምልኮት እንዲገዙት ካዘዘበት ሰዓት አንስቶ እስከ ቂያም ድረስ የደነገጋቸውን አምልኮቶች መተግበርና መልዕክተኞች ይዘዉት በመጡት ነገር በሙሉ አምልኮ መፈፀም እስልምና ይባላል። ስለዚህም ኑሕ ዐለይሂሰላም ይዘውት የመጡት ቅን መንገድና ሐቅ፤ ኢማሙ ሑነፋእ ኢብራሂም ይዘውት የመጡት፤ሙሳና ኢሳ ይዘውት የመጡት በሙሉ ጥቅላዊ እስልምና ውስጥ ይካተታል። ወይም ደግሞ አላህ ይህን በማስመልከት በበርካታ አንቀፆች ላይ እንደገለፀው ከዚህ በፊት የነበሩ ድንጋጌዎችና ህግጋቶች በሙሉ ኢስላም(ለአላህ እጅ መስጠት) ውስጥ ይገባሉ። ነገር ግን ኢስላም ለየት ባለው ትርጓሜው፦ ነቢያችን ሙሐመድ የተላኩበት መልዕክት ብቻ እስልምና ይባላል። ምክንያቱም መልዕክተኛው ሙሐመድ የተላኩበት መልዕክት ከዚህ በፊት የነበሩ ሐይማኖትን በሙሉ የሚሽር ነው። እሳቸውን የተከተለ ሙስሊም ሲባል ያልተቀበላቸው ደግሞ ሙስሊም አይባልም። ምክንያቱም ለአላህ ሳይሆን ለዝንባሌው ነው እጅ የሰጠው። በሙሳ ዘመን የነበሩ የሁዳዎች ሙስሊም ነበሩ፤ በኢሳ ዐለይሂ ሰላም ዘመን የነበሩ ነሳራዎች ሙስሊም ነበሩ። ነቢዩ ሙሐመድ (صلى الله عليه وسلم ) ከተላኩ በኋላ ግን ሁላቸውም በመካዳቸው ሙስሊም አይባሉም። ስለዚህም ዛሬ ላይ የሁዳዎችም ይሁን ነሳራዎች ዲን አድርገው የያዙት ሐይማኖት ትክክል ነው አሊያም ከእስልምና ጋር እኩል ነው ብሎ ማመን ለአንድ ሙስሊም አይፈቀድለትም። እንዲያውም ይህ አይነት አመለካከት ያለው ግለሰብ ከእስልምና ይወጣል፤ ካፊር ይሆናል።ምክንያቱም አላህ እንዲህ ብሏልና፦

“አላህ ዘንድ (የተወደደ) ሃይማኖት ኢስላም ብቻ ነው፡፡” [አልዒምራን፡19]
 
እንዲህም ይላል፦ “ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይነት የለውም፡፡” [አልዒምራን፡89]

ይህ በቁርኣኑ የጠቆመው እስልምና ለመልክተኛውና ለህዝባቸው ስለመረጠላቸው ታላቅ ውለታ እንደሆነ በቁርኣኑ እንዲ ሲል ገልፆታል፦ 

“ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ፡፡ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፡፡ ለእናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፡፡ “ [አልማኢዳ ፡3]

ከመልክተኛው (صلى الله عليه وسلم ) ተከታይ ውጭ ያሉ ሰዎች በሙሉ እስልምና ላይ እንዳልሆኑ ይህ አንቀጽ በግልፅ ያሳያናል። ስለዚህም እንደ ሐይማኖት አድርገው የያዙት በሙሉ ተቀባይነት የለውም። የቂያማ እለትም አይጠቅማቸውም። ሐይማኖታቸውን ትክክለኛ እና ቀጥተኛ ሐይማኖት ብለን ልንቆጥርው አይገባም። ስለዚህም የሁዳና ክርስቲያን ወንድሞቻችን ናቸው ወይም ዲናቸው ቀጥተኛ ሐይማኖት ነው የሚል ግልፅ የሆነ ስሕተት ላይ ወድቋል። ላሳለፍነው ምክንያት ሲባል።

እስልምና ማለት፦ አላህ በደነገገው አምልኮ መገዛት ማለት ከሆነ በውስጥም ሆነ በውጫዊ ለአላህ እጅ መስጠት እስልምና ይባላል።

ስለዚህም ዲን ሲባል ዐቂዳ ተግባርና ዐንደበታዊ ስራዎችን በሙሉ ያካትታል። ኢስላም ከኢማን ጋር ተቆራኝቶ ሲመጣ ለውጫዊ ተግባራት ማለትም በአንደበት የሚነገሩ ተግባሮችና ለአካላዊ ስራዎች ኢስላም የሚል ትርጉም ሲሰጠው ኢማን ደግሞ ውስጣዊ ለሆኑ ተግባራት ማለትም ዓቂዳና የቀልብ ተግባሮች ኢማን የሚል ትርጉም ይሰጠዋል። ቀጣዩ የቁርኣን አንቀጽ በሁለቱ መካከል ልዩነት እንዳለ ይጠቁማል።

“የዐረብ ዘላኖች «አምነናል» አሉ፡፡ «አላመናችሁም፤ ግን ሰልመናል በሉ፡፡ «እምነቱም በልቦቻችሁ ውስጥ ገና (ጠልቆ) አልገባም፡፡” [አልሑጅራት:14]

 ስለ ነቢዩላህ ሉጥ ዐለይ ሂሰላም ሲናገር አላህ እንዲህ ይላል፦

“ከምእመናንም፤ በእርሷ (በከተማቸው) ውስጥ የነበሩትን አወጣን፡፡ በውስጧም ከሙስሊሞች ከአንድ ቤት (ቤተሰቦች) በስተቀር አላገኘንም፡፡” [አዛሪያት 35-36]

ስለዚህም በሙእሚን እና በሙስሊም መካከል ልዩነት አለ። ምክንያቱም ከአንቀጹ ግልፅ የሚሆንልን በመንደሪቷ ይኖሩ ከነበሩት ውስጥ የሙስሊሞች ቤት ነበር። ሉጥ ላይ ሸፍጥ የሰራችውንም የሉጥን ሚስት ያካትታል።  ከመንደሪቷ የወጡና ከቅጣቱ ሰላም ሆነው የዳኑት በትክክል ከልባቸው ያመኑት ብቻ ናቸው። ኢስላምና ኢማን አንድ ላይ ሲመጡ የተለያየ መልክት እንዳላቸው ዑመር ኢብኑ አልኸጣብ ያስተላለፉት ሐዲስ ማስረጃ ነው። ‘የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እስኪ ስለኢስላም ይንገሩኝ?’’ አለ። ከዚያም ነብዩ (صلى الله عليه وسلم )  ‘ኢስላም ማለት፤ ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ እንደሌለ እና ሙሀመድም የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር፤ ሶላትን በተሟላ ሁኔታ መስገድ፣ ዘካን መስጠት፣ የረመዷንን ወር መጾም፣ አቅምህ ከፈቀደ ሀጅ መሄድ ነው’ ኣሉት።  ‘ኢማን   አስመልክቶ  ግን እንዲህ አሉት፦ ‘በአላህ በመላእክቶቹ፣ በመጻህፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን እንዲሁም ጥሩም ይሁን መጥፎ በአላህ ውሳኔና ፍቃድ (ቀደር) እንደሚከሰት ማመን ነው’  ያም ሆነ ይህ ኢስላም  የሚለው ትርጓሜ በልቁ ማለትም ከኢማን ጋር ሳይያያዝ ከመጣ ዲን በሙሉ ያካትታል። ኢማንም በውስጡ ይካተታል። ከኢማን ጋር ተያይዞ ሲመጣ ደግሞ ለውጫዊ ተግባራት ማለትም በአንደበት የሚነገሩ ተግባሮችና ለአካላዊ ስራዎች ኢስላም የሚል ትርጉም ሲሰጠው ኢማን ደግሞ ውስጣዊ ለሆኑ ተግባራት ማለትም ዓቂዳና የቀልብ ተግባሮች ኢማን ተብሎ ማብራሪያ ይሰጠዋል።
Share

ወቅታዊ