Back to Top
በአላህ ስሞች እና ባህሪያቶች ላይ ኢልሃድ ሲባል ምን ማለት ነው?

ጥያቄ(44): በአላህ ስሞች እና ባህሪያቶች ላይ ኢልሃድ ሲባል ምን ማለት ነው?
መልስ:

ኢልሓድ ማለት በአረብኛ መነሻ ቃሉ መዘንበል ማለት ነው። ይህን ትርጓሜ ከሚያሳዩ የቁርኣን አንቀፆች መካከል፦

“የዚያ ወደርሱ የሚያዘነብሉበት ሰው ቋንቋ ዐጀም(ባዕድ) ነው፡፡ ይህ (ቁርአን) ግን ግልጽ ዐረብኛ ቋንቋ ነው፡፡”[አነሕል:103]

ከዚሁ ትርጉም ጋር የሚሄደውም የቀብር “ለሕድ” ሲሆን ለሕድ የተባለበትም ምክንያት ወደጎን ዘንበል ተደርጎ ስለሚቆፈር ነው። ኢልሃድ የሚለውን ልናውቅ የምንችለው ኢስቲቃማን (ቀጥ ያለውን መልክት) ስናውቅ ብቻ ነው። ምክንያቱም ነገሮች ግልፅ የሚሆኑት ተቃራኒያቸው ሲታወቅ ነው የሚል አባባል አለ ።  ከዚህ በፊት እንዳሳለፍነው   የአላህ ስምና ባህሪያትን አስመልክቶ አህሉ ሱናዎች ቀጥተኛው አካሄድ እነዚህ ስምና ባህሪያትን ያለ ትርጉም ማዛባት፤ያለ ትርጉም አልባ፤ያለ እንዴታ እና ከፍጡራን ጋር ሳያመሳስሉ ለአላህ በተገቢው መልኩ በሐቂቃው ማስኬድ (ማፅደቅ) ነው። በዚህ ርዕስ ላይ ትክክለኛው አካሄድ ግልፅ ከሆነልን የዚህ ተቃራኒው ኢልሃድ ይባላል። ዑለማዎች የአላህ ስምና ባህሪያት ላይ የሚደረጉ ብዙ አይነት የኢልሃድ አይነት ጠቅሰዋል። በጥቅሉ ሲቀመጥ ግን እምነት ተደርጎ ሊያዝ ከሚገባው ነገር መዘንበል ኢልሃድ ተብሎ ይጠራል።

አንደኛው የኢልሃድ አይነት ፦ ስሞቹ ከሚያመላክቱት አንዱን ባህሪ ማስተባበል ነው። ለምሳሌ፦ በጃሂሊያ ዘመን የነበሩ ሰዎች አረሕማን የሚለውን ስም ይክዱና ያስተባብሉ ነበር።

ወይም ደግሞ ከፊል የቢድዓ አንጃዎች እንዳደረጉት፦ ስሞቹ በውስጣቸው የሚይዙትን ባህሪያት ማስተባበል። ለምሳሌ ፦ “አዛኝ ነው ያለ እዝነት፤ ሰሚ ነው ያለመስማት፤ ተመልካች ነው ያለ ዓይን …” ወዘተ

ሁለተኛው የኢልሃድ አይነት፦ አላህ ባልሰየመበት ስም መሰየም። ይህን ድርጊት ኢልሃድ ያልንበት ምክንያት የአላህ ስሞች ተውቂፊያ (በቁርኣንና በሐዲስ የተገደቡ) ስለሆኑ ነው። ስለዚህም አንድም ሰው ለአላህ ስም የመሰየም መብት የለውም። ምክንያቱም ይህ ተግባር በአላህ ላይ የማያቁትን ከመናገር ይቆጠራል። በአላህ ላይ ወሰን ከማለፍም ነው። ፈላስፋዎች አላህን “ዒላህ አልፋዒላ” ብለው እንደሰየሙት ማለት ነው። ክርስቲያኖች ደግሞ “አብ” ብለው አላህን እንደሚጠሩት። ወዘተ….

ሦስተኛው የኢልሓድ አይነት፦ እንዚህ የአላህ ስምች ፍጥረታት እንደሚገለፁበት ባህሪን ይጠቆማሉ ብሎ ማመን። ይህን ድርጊት ኢልሃድ ያልንበት ምክንያት የአላህና የመልክተኛው ንግግር ከፍጥረታት ጋር መመሳሰል ያስጨብጣሉ ወይም በተዘዋዋሪ ንግግራቸው ኩፍርን ይጠቁማሉ እንደማለት ይቆጠራል። ምክንያቱም አላህ ከፍጥረታት ጋር ማመሳሰል ኩፍር ነው።  ቀጣዩ ን የአላህን ቃል እንደማስተባበል ስለሚቆጠር።

“ለርሱ ምንም አምሳያ የለውም፡፡ እርሱም ሰሚውና ተመልካቹ ነው፡፡” [አሽ ሹራ:11]

 

“ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን?” [መርየም:65]

«አላህን ከፍጡራኑ ጋር ያመሳሰለ በእርግጥ ክህደትን ፈፅሟል፤ (አላህ) ራሱን የገለፀበትን ያስተባበለም በእርግጥ ክህደትን ፈፅሟል፤ አላህ ራሱን የገለፀበትም ሆነ መልዕክተኛው (እርሱን የገለፁበትን ማፅደቅ) ማመሳሰል አይደለም!»(“ሸርሁ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ነቲ ወል-ጀማዐህ” ሊ’ል-ላለካኢይ (3/532)

አራተኛው የኢልሃድ አይነት፦ የአላህ ስሞችን በማጣመም ለጣኦታት ስም ማውጣት። ኢላህ ከሚለው ስም “ላት“ ዐዚዝ ከሚለው ስም‹‹ዑዛ›› መናን ከሚለው ስም መናት በማለት ለጣዖታት ስም ማውጣት። ይህን ድርጊት እንደ ኢልሃድ የቆጠርንበት ምክንያት የአላህ ስሞች በእርሱ ብቻ የተነጠሉ በመሆናቸው ነው።ማለትም ለአላህ የማይገባውን ባህሪ ስለሚያሰጥ ስሞቹ የሚጠቁሙትን መልዕክት ለአንዱም ፍጡር ማሸጋገር አይቻልም (ክልክል ነው)። እነዚህ በአላህ ስሞች ላይ የተከሰቱ የኢልሓድ አይነቶች ናቸው።




Share

ወቅታዊ