ጥያቄ(91): ኢማም ካሰገደ በኋላ ያለውዱእ እንዳሰገደ ቢያውቅ ኢማሙ እና ተከታዮቹም ዳግም ሰላታቸውን መስገድ ይኖርባቸዋልን?
መልስ:
የዚህ ሑክም እንደሚከተለው ይሆናል፤ ኢማሙ ዳግም ውዱእ አድርጎ መስገድ ይኖርበታል ተከታዮች ግን ዳግም መስገድ አይኖርባቸውም። በጀማዓ ሰግደዋልና የጀማእን ምንዳ አግኝተዋል። አጅር ይፃፍላቸዋል። በተጨማሪም ዑዝር ስላለው ማለትም ውሃን መጠቀም ስለማይችል ወይም ውሃ በማጣቱ የተነሳ ያለ ውዱእ ወይም ጀናባውን ሳይታጠብ በውሃ ፈንታ በአፈር ተየሙም አድርጎ መስገድ ይበቃለታል። ውሃ ሳላላገኘ ወይም በበሽታ የተነሳ ውዱእን ማድረግ ባለመቻሉ በተየሙም ለብዙ ወራት ያህል እንኳ ቢሰግድ ሰላቱ ተቀባይነት አለው። ምክንያቱም ተየሙም የውሃ ቦታን ይተካልና። በውሃ መጠቀም ሳይቻል ቀርቶ ተየሙም ቢያደርግ ውዱእን እስካላጠፋ ድረስ ዳግም ተየሙም ማድረግ አይጠበቅበትም። ምክንያቱም ተየሙም የውዱእን ቦታ ይተካል። አላህ በሱረቱ አልማኢዳ እንዳለው። ተየሙም ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል፦
“አላህ በእናንተ ላይ ምንም ችግር ሊያደርግ አይሻም፡፡ ግን ታመሰግኑ ዘንድ ሊያጠራችሁና ጸጋውን በእናንተ ላይ ሊሞላ ይሻል፡፡” [አልማኢዳ፡6]
መልክተኛውም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፦
“ምድር ለኔ መስገጃ እና መጥራሪያ(ጠሃራ ማስገኛ) ተደርጎልኛል።”