Back to Top

1/የሰው ልጆች በሙሉ የተፈጠሩበት ዓላማና ግብ ምንድ ነው?

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩኅ በጣም አዛኝ በኾነው። ምስጋና ለአላህ ይገባው። ሰላትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ፤ በቤተሰቦቻቸው እና በሁሉም ባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን ዘንድ ጌታዬን እማፀነዋለሁ። በመቀጠልም ይህን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት አላህ ስለሚፈጥረውና ስለሚደነገግው ጉዳይ አስመልክቶ አጠቃላይ መርሆዎችን ማስታወስ እወዳለሁ። ይኸውም ከአላህ ቃል የተወሰደ መርሆ ነው።
አላህ እንዲህ ይላል፦   
 “እርሱም ዐዋቂው ጥበበኛው ነው፡፡” [አት ተሕሪም :2]  
እንዲህም ይላል፦
“አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡” [አል አሕዛብ:1]  
አላህ የሚፈጥረውና የሚደነግገው ለታላቅ ዓላማና ጥበብ መሆኑን የሚያመላክቱ እጅግ በርካታ የቁርኣን አንቀፆች ይገኛሉ። (በሸሪዓዊና በይሁንታዊው ድንጋጌዎቹ) ማንኛውም አላህ በሚፈጥረውና በሚያስገኘው ነገር ላይ ጥበብ ቢኖረው እንጂ አይፈጥርም።  እንዳይገኝ በሚያደርገው ነገርም ላይ እንዲሁ። ማንኛውም አላህ የሚደነግጋቸው ህግጋት ጥበብ ያዘሉ ቢሆኑ እንጂ አንድን ነገር አይደነግግም። ዋጂብ አሊያም ሐራም እና ሐላል በሚያደርጋቸው ነገሮች በሙሉ አላህ የተሟላ ጥበብ አለው።
ነገር ግን ሸሪዓዊም ሆነ ከውኒያው (ይሁንታዊ) ድንጋጌዎች በውስጣቸው የሚያካትቷቸው ጥበቦች ለኛ የሚታወቁ አሊያም ከእኛ የተሰወሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ጥበቦች ለሰዎች አላህ በሚያድላቸው የእውቀትና የግንዛቤ መጠን የተነሳ ከፊል ሰዎች ሊያውቁት ከፊሎቹ ደግሞ ላያውቁት ይችላሉ። ይህ ከተረጋገጠ ዘንድ አላህ የሰው ልጅንም ሆነ ጂኖችን የፈጠረው ለትልቅ አላማ እና ምስጉን ለሆነ ግብ ሲሆን እሱም እርሱን በብቸኝነት ለማምለክ ነው እንላለን። አላህ እንዳለው፦
“ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡” [ዛሪያት:56]

 እንዲህም ይላል፦

«የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?” [አል ሙእሚኑን :115]

እንዲህም ይላል፦

”ሰው ልቅ ኾኖ መትተውን ይጠረጥራልን?” [አልቂያማ:36]  
አላህ የሰው ልጅንም ሆነ ጂኖች እጅግ ለላቀ ጥበብ ነው የፈጠራቸው። እርሱም እርሱን በብቸኝነት ማምለክ መሆኑን የሚያመላክቱ ሌሎችም በርካታ አንቀፆች አሉ። (ዒባዳ)አምልኮት ማለት ሸሪዓዎቹ ላይ በመጣው መሰረት አላህን ከመውደድና ትዕዛዙን በማላቅ ክልከላውን በመራቅ ለአላህ እራስን ዝቅ ማድረግ ማለት ነው።
አላህ እንዲህ ይላል፦
“አላህን ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ አጥሪዎች ኾነው ሊግገዙት እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ ...” [አልበዪናህ:5]
የሰው ልጆችም ሆነ ጂኖች የተፈጠሩት ለነዚህ ጥበቦች ሲባል ነው። ከዚህም በመነሳት ከጌታው ያፈነገጠ እና እርሱን ከማምለክ የተኩራራ ባሮች የተፈጠሩበት አላማ የሆነው ነገር አሽቀንጥሮ እንደወረወረ ይቆጠራል። በዚህም ተግባሩ በአፉ አውጥቶ ባይናገርም እንኳ አላህ ፍጥረታቱን ለጨዋታና ለከንቱ እንደፈጠረ በተዘዋዋሪ እንደመሰከር ይቆጠርበታል። ነገርግን ከጌታው ትዕዛዝ በማፈንገጡና በመኩራቱ የተነሳ በተዘዋዋሪ ይህን መልዕክት ያስፈርዳል።
 
 

10/እያንዳንዱ የተውሒድ ክፍል አስመልክቶ በእኛ ላይ ግዴታ የሚሆነው ነገር ምንድ ነው?

እያንዳንዱ የተውሒድ ክፍል በውስጡ የሚዘውን መልክት ተረድተን ልናምንበት ይገባል። ያ የተውሒድ ክፍል በሚያመላክተው መልክት መሰረት አላህን ነጥለን በብቸኝነት ልናመልከው ይገባል።

 

36/ነገር ግን በኮከብ ቆጠራ እና በጥንቁልና መካከል ቁርኝት አለን?

አዎን፤ በሁለቱ መካከል ያለው ተያያዥነት ሁለቱም መሠረተ ቢስ ምናብ እና ቅጥፈት ላይ የተመሰረቱ ነገሮች በመሆናቸው አንድ ያደርጋቸዋል። እንዲሁም የሰዎችን ገንዘብ በባጢል መብላት፤ ሰዎችን ጭንቀትና ትካዜ ላይ መጣል እና የመሳሰሉት ነገሮች ሁለቱንም አንድ ያደርጓቸዋል።

ከሁለቱ የትኛው የባሳ አደጋ አለው?

14/በልብ ማመንና በዐንደበት መመስከር ልዩነቱ ምንድ ነው? ሁለቱን በአንድ ላይ ማስገኘት ግዴታ ነውን?

አዎን።በልብ ማመንና በዐንደበት መመስከር ልዩነቱ ግልፅ ነው።አንዳንድ ሰው በዐንደበቱ ብቻ ቢመሰክርም በቀልቡ አያምንም ለምሳሌ ሙናፊቆች። ሙናፊቆችን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ይላል፦

“መናፍቃን በመጡህ ጊዜ «አንተ የአላህ መልክተኛ መኾንህን በእርግጥ (ምለን) እንመሰክራለን» ይላሉ፡፡[አልሙናፊቁን:1]”

አላህ ግ እንዲህ ይላል፦

“አላህም አንተ በእርግጥ መልክተኛው መኾንህን ያውቃል፡፡ አላህም መናፍቃን (ከልብ እንመሰክራለን በማለታቸው) ውሸታሞች መኾናቸውን አላህ ይመሰክራል፡፡” [አልሙናፊቁን:1]

እነዚህ መናፍቃን በልባቸው ሳይሆን በዐንደበታቸው መልክተኛው መልክተኛ መሆኑን መስክረዋል። ምናልባትም አንድ ሰው በቀልቡ አምኖ በዐንደበቱ መመስከር የሚከብደው ይኖራል። በምናየው ውጫዊ ተግባር ተነስተን ፍርድ እንሰጣለን እንጂ ውስጣዊ እምነቱ እኛ ዘንድ ምንም አይፈይደውም። ሆኖም በርሱና በአላህ መካከል ያለውን ጉዳይ አስመልክቶ እኛ የምናውቀው ነገር የለንም። ወይም ደግሞ ሊባል የሚችለው ፍርዱን ወደ አላህ እንተወዋለን። ነገር ግን ዱንያ ላይ ምንም አይጠቅመውም። በዐንደቱ እስካልመሰከረ ድረስ ሙስሊም የሚለው ብያኔ አይሰጠውም። ምናልባት መናገር የሚሳነው ከሆነና ምላሱ ላይ ችግር ኖሮ አሊያም እንዳይናገር የሚከለክለው ነገር ካለ እንደሁነታው ፍርድ ይሰጠዋል። ያም ሆነ ይህ በቀልብም ይሁን በአንደበት መመስከር ግዴታ ነው።

56/የተከበሩ ሸይኽ! ትክክለኛው እና ተቀባይነት የሌለው የተወሱል አይነት ምንና ምን ናቸው?

ተወሱል ማለት “ተወሰለ” “የተወሰሉ” ማለትም ተዳረሰ መዳረስ ከሚለው የዓረብኛ ስረወ ቃል የመነጨ ነው። ወደ ሚያልመው አላማ እና ግብ ሊያዳርሰው የሚችል መዳረሻ ሰበብ ሲይዝ “ተወሰለ”ተዳረሰ መዳረስን ይባላል። የዚህ ቃል መነሻው ወደሚፈለግ ግብ ለመድረስ መፈለግ ወይም መከጀል የሚል ነው። ተወሱል ሲባል ለሁለትም ይከፈላል።

አንደኛው ትክክለኛው የተወሱል ክፍል: ወደሚፈለገው ግብ በትክክለኛ መዳረሻ መዳረስ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ: ወደ ተፈላጊው ግብ የማያዳርስ የመዳረሻ አይነት ነው።

የመጀመሪያው የተወሱል አይነት ማለትም ፡ ወደ ሚፈለገው ግብ በትክክለኛ መዳረሻ መዳረስ የሚለው፦

ብዙ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከእነሱም ውስጥ በአላህ መልካም ስሞቹ እና ባህሪያቶቹ ተወሱል ማድረግ ሲሆን በጥቅሉ ወይም በተለየ መልኩም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፦ በጥቅሉ በአላህ መልካም ስሞቹ እና ባህሪያቶቹ ተወሱል ማድረግ ለሚለው፦ ከዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ ተዘግቦ እንደመጣው ፦ “አላህ ሆይ! እኔ ባሪያህ፣የወንድ ባሪያህም፣የሴት ባሪያህም ልጅ ነኝ። ሁለ ነገሬ በእጅህ ነው። ውሳኔህ በኔ ላይ ተፈፃሚ ብይንህ ፍትሓዊ ነው።ቁርኣንን ለኔ ቀልብ ማርጠቢያ ታደርግልኝ ዘንድ በስሞችህ ሁሉ እማፀንሃለሁ። አንተ ራስህን በጠራህባቸው ወይም ቁርኣንህ ውስጥ ባሰፈርካቸው፣ከፍጡራንህ ለአንዱ ባስተማርካቸው ወይምለማንም ሳትገልፅ አንተ ዘንድ ባስቀረከውም ስሞችህ እማጸነሃለው።” (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ) ”በስሞችህ ሁሉ እማፀንሃለሁ።” ከሚለው አ/ነገር በመነሳት እዚህ ቦታ ላይ  በአላህ ስሞችና ባህሪያቶች ተወሱል  በጥቅሉ ነው የተጠቀሰው።

በተለየ መልኩ የሚለው ደግሞ (ከሐጃው) ከጉዳዩ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችልን ከአላህ ስሞች መካከል አንዱን ለይቶ በመጥራት አላህን መማፀን ነው። ለምሳሌ፦ ከአቡበከር ተዘግቦ በመጣው ሐዲስ ላይ መልዕክተኛውን ሰላት ላይ ሲሆኑ የሚያደርጉትን ዱዓ በጠየቋቸው ጊዜ እንዲህ ብለዋቸዋል፦

“አላህ ሆይ! እኔ ነፍሴን በርካታ በደሎችን በድያለሁ። ወንጀልን ከአንተ ውጭ የሚሸፍን(የሚምር) የለም። ከአንተ  የሆነን ምህረት ለግሰኝ። እዘንልኝም። አንተ መሓሪና አዛኝ ነህና።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
በነዚህ ሁለት ስሞች(አል ገፉር እና አር ረሒም) አላህን ምህረትና እዝነት መጠየቅ ከጉዳዩ ጋር አብሮ የሚገጥሙ ስያሜዎች ናቸው። ይህ አይነቱ የተወሱል አይነት ቀጣዩ የቁርኣን ትዕዛዝ ውስጥ የሚካተት ነው።”
ለአላህም መልካም ስሞች አሉት፡፡ (ዱዓ ስታደርጉ) በእርሷም ጥሩት፡፡” [አል አዕራፍ ፡180]

   እዚህ ቦታ ላይ ዱዓ(ጥሪ) ሲባል ዱዓኡ መስኣላና ዱዓኡ ዒባዳ ይካተታሉ። በባህሪያቶቹ ተወሱል ማድረግ የሚለው ደግሞ ልክ እንደ ስሞቹ ጥቅልና ለየት ያሉ የተወሱል አይነት አላቸው። ጥቅል በሆኑ በአላህ መገለጫ ባህሪያቶች ተወሱል ማድረግ ለሚለው ፦ አላህ ሆይ! መልካምና ውብ በሆኑ ስሞችህ እና ከፍና ላቅ ባሉ ስሞችህ እማፀንሃለሁ። የሚለው በምሳሌነት ተጠቃሽ ነው። ለየት ባሉ በአላህ መገለጫ ባህሪያቶች ተወሱል ማድረግ ለሚለው ደግሞ ፦ ሐዲስ ላይ እንደመጣው ፦ “አላህ ሆይ! በሩቅ ሚስጥር እውቀትህና በፍጡራን ላይ ባለህ ችሎታ እማፀንሃለሁ። መኖሬ ለኔ መልካም መሆኑን ካወቅክ በህይወት አቆየኝ።ሞት ለኔ መልካም እንደሆነ ካወቅክ ደግሞ ለህልፈት አብቃኝ።” “በሩቅ ሚስጥር እውቀትህና በፍጡራን ላይ ባለህ ችሎታ እማፀንሃለሁ።” እዚህ  ላይ ደግሞ ዒልም (ዕውቀት) እና ቁድራ (ችሎታ) በሚባሉት መገለጫ ባህሪያቶች ወደ አላህ ተወሱል ተደርጓል። ይህ አንደኛው የተወሱል አይነት ነው።

ሁለተኛው የተወሱል አይነት ደግሞ፦ አንድ ሰው በአላህ ማመን እና በመልክተኛው መልዕክተኝነት ማመን በሚባለው መልካም ስራ ወደ አላህ ተወሱል ማድረጉ ሲሆን ለምሳሌ ፦ “አላህ ሆይ በአንተ አምላክነት በመልዕክተኛው መልክተኝነት አምኛለሁና ወንጀሌን ማረኝ፣ለመልካሙ ሁሉ ግጠመኝ።”ሊል ይችላል። ወይም አላህ ሆይ! በአንተ በማመኔ መልክተኛውን በመቀበሌ እንዲህ እንዲህ  ያሉ ነገሮችን …  እጠይቅሃለሁ።” ሊል ይችላል።ከዚህም የተወሱል አይነት ከሚካተተው የሚከተለው የቁርኣን መልክት ይገኝበታል፦ “ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር ሌሊትና ቀንንም በመተካካት ለባለ አእምሮዎች በእርግጥ ምልክቶች አሉ፡፡ (እነርሱም) እነዚያ ቆመው፣ ተቀምጠውም፣ በጎኖቻቸው ተጋድመውም አላህን የሚያወሱ በሰማያትና በምድር አፈጣጠርም የሚያስተነትኑ፡-

«ጌታችን ሆይ! ይኸን በከንቱ አልፈጠርከውም፤ ጥራት ይገባህ፤ ከእሳትም ቅጣት ጠብቀን» የሚሉ ናቸው፡፡” [አልዒምራን:190_ 191] እንዲሁም እስከ [አል ዒምራን 193 ] ያለው
«ጌታችን ሆይ! እኛ በጌታችሁ እመኑ በማለት ወደ እምነት የሚጠራን ጠሪ ሰማን፡፡ አመንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ኃጢአቶቻችንንም ለኛ ማር፡፡ ክፉ ሥራዎቻችንንም ከኛ አብስ፡፡ ከንጹሖቹም ሰዎች ጋር ግደለን፤»

ስለሆነም በነዚህ አንቀፆች መሰረት አማኞች በአላህ በማመናቸው ወንጀላቸውን እንዲምርላቸው ሐጢያቶቻቸውንም እንዲያብስላቸውና ከአብራሮች (መልካም ሰሪዎች) ጋር እንዲገድላቸው ወደእሱ ተወሱል አድርገዋል።

ሦስተኛው የተወሱል ዓይነት፦ በመልካምና በሰናይ ምግባራት ተወሱል ማድረግ ሲሆን ከዚህ የተወሱል ዓይነት ማስረጃ (ምሳሌ) ሆኖ የሚቀርበው ሦስቱ በጉዞ ላይ ሳሉ ዝናብ ገጥሟቸው በመሸሽ ወደ ዋሻ የተጠለሉት ሰዎች ታሪክ ነው። እርሱም(ታሪካቸውም)፦ ዋሻው ውስጥ ሲጠለሉ ማንቀሳቀስ የማይችሉት ትልቅ ቋጥኝ ተንከባሎ የዋሻውን በር ዘጋባቸው። ሦስታቸውም ለአላህ ሲሉ በሰሯቸው መልካም ስራ ተወሱል አደረጉ።ከእነሱ ውስጥ አንዱ ለእናቱ መልካም በመዋሉ፣ሁለተኛው ደግሞ በተሟላው ጥብቅነቱ ሦስተኛው ደግሞ ለቅጥረኛው አማናውን ጠብቆለት ተገቢውን ደሞዝ ሳይቀንስ በመስጠቱ ተወሱል አደረጉ። ሁላቸውም ፦ “አላህ ሆይ! ይህንን ስራ ለአንተ ስንል ካደረግነው አሁን ካለንበት ጭንቀት ገላግለን።” በማለት አላህን ተማፀኑት። ቋጥኙም ተንከባሎ በሩን ክፍት አደረገላቸው።” ይህ በመልካም ስራ ወደ አላህ ተወሱል ማድረግ ውስጥ የሚካተት  ነው።

አራተኛው የተወሱል ዓይነት፦ ተወሱል የሚያደርገው ግለሰብ እርሱ ያለበት ሁኔታ እና የአላህ እገዛ ለሱ በጣም እንደሚያስፈልገው በማስተዛዘን ተወሱል(ዱዓ) ማድረግ ነው።

ከዚህ የተወሱል ዓይነት የሚጠቀሰው ሙሳ ዓለይሂ ሰላም ያደረገው ዱዓ ነው፦

«ጌታዬ ሆይ! እኔ ከመልካም ነገር ወደኔ ለምታወርደው ፈላጊ(ከጃይ) ነኝ» አለ፡፡” [አልቀሰስ:24]

ሙሳ ይህን በሚልበት ግዜ የአላህ መልካም ነገር ለርሱ ወሳኝ እና አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ ተወሱል አድርጓል።

ከዚሁ የተወሱል አይነት የሚመደበው ዘከሪያ (ዓለይሂ ሰላም) ያደረገው ተወሱል(ዱዓ) ይገኝበታል።

«ጌታዬ ሆይ! እኔ አጥንቴ ደከመ፤ ራሴም በሺበት ተንቀለቀለ፤ አንተም በመለመኔ ጌታዬ ሆይ! (ምንጊዜም) ዕድለ ቢስ አልሆንኩም፡፡” [መርየም:4]

እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው የተወሱል ዓይነቶች ሁሉም ይፈቀዳሉ፤ ምክንያቱም በነሱ ተወሱል በማድረግ የሚፈለገውን ዓላማ ለማግኘት ትክክለኛ ሰበቦች እና ጥረቶች ናቸው።


 

86/ሰላት ግዴታ የሚሆነው በማን ላይ ነው?

ሰላት በሙስሊም፣ለአቅመ አዳም በደረሰ፣ጤናማ አእምሮ ያለው ወንድ ይሆን ሴት ላይ በሙሉ ግዴታ ነው። ሙስሊም ስንል ካፊር ያልሆነ ማለት ነው። ካፊር ላይ ሰላት ግዴታ አይደለምና። ማለትም ካፊር ሆኖ ሳለ ሰላትን መስገድ ግዴታ አይሆንበትም ሲሰልምም በኩፍር ዘመኑ ያሳለፈውን ሰላት ቀዳ ማውጣት ግዴታ አይሆንበትም ማለታችን ነው። ሆኖም የቂያማ ቀን ሰላት ባለመስገዱ ይቀጣል። አላህ አዘወጀለ  እንዲህ ይላል፦ 

 

“ የቀኝ ባለቤቶች ብቻ ሲቀሩ፡፡ (እነርሱስ) በገነቶች ውስጥ።  ከአመጸኞቹ ሁኔታ፡፡ (ይጠያየቃሉ፡፡) (ይሏቸዋልም) «በሰቀር ውስጥ ምን አገባችሁ?» (እነርሱም) ይላሉ «ከሰጋጆቹ አልነበርንም፡፡ «ለድኾችም የምናበላ አልነበርንም፡፡ «ከዘባራቂዎቹም ጋር እንዘባርቅ ነበርን፡፡ በፍርዱ ቀንም እናስተባብል ነበርን፡፡ (ይላሉ)” [አልሙደሲር:39_ 46]

 

«ከሰጋጆቹ አልነበርንም፡፡” ማለታቸው ሰላት ባለመስገዳቸው የተነሳ መቀጣታቸውን ያሳያል። ለአቅም አዳም የደረስ ማለት ደግሞ፤ ለአቅም አዳም መድረሱን ከሚጠቁሙ ምልክቶች መካከል አንዱ መከሰት ሲሆን፤ ወንዶችን በማስመልከት ሦስት ምልክቶች ሲኖሩ ሴቶች አስመልክቶ ደግሞ አራት ምልክቶች አሉ። ከነዚህ ምልክቶች መካከል የመጀመሪያው፦ አስራ አምስት አመት መሙላት። ሁለተኛው፤ በህልምም ይሁን በእውን የዘር ፈሳሽን በእርካታ መልኩ መውጣት (መፍሰስ) ሦስተኛው፤ብልት ዙርያ ፀጉር ማብቀል። እነዚህ ሦስት ምልክቶች ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የጋር ምልክቶች ናቸው። ሴት ከወንድ አንድ ምልክትን ትጨምራለች፤ እርሱም የወር አበባ ማየት መጀመሯ ነው። ስለዚህም የወር አበባ (ሐይድ) ለሴቶች ከጉርምሳና ምልክቶች አንዱ ነው።

ጤናማ አዕምሮ፤ ስንል ደግሞ የአዕምሮ በሽተኛ ያልሆነ ማለት ነው። ከዚሁ ጋር የሚካተተው እድሜው የገፋ/ች አዛውንት በእርጅና የተነሳ ነገሮችን መለየት የማይችሉበት ደረጃ ከደረሱ አዕምሯቸው ማስተዋል ስሌለው በነሱ ላይ ሰላት ግዴታ አይሆንም። የወር አበባና የወሊድ ደም ደግሞ ሰላት በነሱ ላይ ግዴታ የማያደርጉ ምክንያቶች ሲሆኑ የወር አበባና የወሊድ ደም ሲከሰቱ ሰላት መስገድ በሴቶች ላይ ዋጂብ አይሆንም።