ጥያቄ(93): ከሰላት መስፈርቶች መካከል ጊዜ(መግባት) ፣ ሀፍረትን መሸፈን፣ ጠሃራ እና ወደ ቂብላ መዞርን ጠቅሰውልናል። የተቀሩትን የሰላት መስፈርቶችን እንዲጨርሱልን እንሻለን።
መልስ:
ወደ ቂብላ መዞር የሰላት መስፈርት መሆኑን ከላይ አሳልፈናል። ቂብላ መሳት የሚቻልባቸው አራቱ ሁኔታዎችና ክስተቶች እንዳሉ ተነጋግረናል። ከነዚህ አራት ክስተቶች አራተኛው ሁኔታ ቂብላው ወደየት አቅጣጫ ይሁን አለማወቁ ሲሆን ይህ ጉዳይ ደግሞ ለውይይት ሊቀርብ ይችላል። ያም ሆነ ይህ! ይህ ጉዳይ ከሌሎች ተለይቶ ይወጣል ብንልም ባንልም የሰው ልጅ እንደ አቅሙ አላህን መፍራት ይኖርበታል። ትክክለኛውን አፈፃፀም ተጠባብቆ መተግበር ይጠበቅበታል። እዚህ ጋ አንድ ቁም ነገር አለ። እርሱም ወደ ቂብላ ዞሮ መስገድ ሲባል አንድ ሰው ከዕባ አጠገብ እና ከዕባን መመልከት የሚችል ከሆነ ወደ ከዕባ ፊቱን ማዞር በርሱ ላይ ግዴታ ነው። ምክንያቱም የቂብላ መሰረቱ ከዕባ ነውና። ሆኖም አንድ ሰው ከከዕባ በመራቁ የተነሳ እሱን መመልከት የማይችል ከሆነ የከዕባን አቅጣጫ መዞር ይኖርበታል። ሰውዬው ከመካ በራቀ ቁጥር የቂብላው አቅጣጫ እየሰፋ ይሄዳል።
ለዚህም ሲባል መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፦
“በምስራቅና በምዕራብ ያለው አቅጣጫ ቂብላ ነው።” ያሉት። ይህ የመዲና ሰዎችን አስመልክቶ የተናገሩት ነው። የእውቀት ባለቤቶች ከቂብላ ትንሽ መዛነፍ ችግር አይኖረውም ብለዋል። ሁላችንም እንደምናውቀው አቅጣጫዎች አራት ሲሆኑ ሰሜን፣ደቡብ፣ ምስራቅና ምዕራብ ናቸው። በመሆኑም አንድ ሰው ከከዕባ ወደ ምስራቅ ወይም ምዕራብ አቅጣጫ ከሆነ እሱን አስመልክቶ በሰሜንና በደቡብ መካከል ያለው አቅጣጫ የርሱ ቂብላ ይሆናል። ከከዕባ በስተሰሜን ወይም በስተደቡብ የሚገኝ ከሆነ እሱን አስመልክቶ በምስራቅና በምዕራብ መካከል ያለው አቅጣጫ የርሱ ቂብላ ይሆናል። ምክንያቱም ፊትን ወደ ከዕባ አቅጣጫ ማዞር ግዴታነውና።
እንበልና አንድ ሰው ከመካ በስተምስራቅ ሆኖ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ቢዞር ይህ ትክክል አይሆንም። ምክንያቱም የመካ አቅጣጫን በግራው በኩል ነውና። እንዲሁም ወደ ደቡብ ፊቱን ቢያዞር ይህም ተግባር ትክክል አይደለም። ምክንያቱም መካን በስተቀኙ አድርጓልና። እንደዚሁም የሰሜን ሰው ቢሆን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ቢዞር ሰላቱ ተቀባይነት አያገኝም። ምክንያቱም ቂብላን በግራው በኩል አድርጓልና። ወደ ምስራቅም ቢዞር እንዲሁ ሰላቱ ተቀባይነት የለውም። ቂብላን በቀኙ በኩል አድርጓልና።
አላህ አዘወጀለ ለባሮቹ በዘመናችን ቂብላን በረቀቀ መልኩ የሚጠቁም መሳሪያ እንዲያስገኙ አግርቶላቸዋል። በተደጋጋሚም ተመኩሮ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል። ስለሆነም የሰው ልጅ ጉዞ ሲያስብ አቅጣጫ የሚጠቁም መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ምክንያቱም ሰውዬው የቂብላ አቅጣጫን በትክክል ለማወቅ የሚያዳግተው ከሆነ መሳሪያው የቂብላን ቦታ ይጠቁመዋል። እንደዚሁም መስገጃውን ወደ ቂብላ መገንባት የፈለገ ሰው በትክክል እንደሚሰራ በተደጋጋሚ የተሞከረ እና ትክክለኛ አቅጣጫን የሚጠቁም መሳሪያ ስለሆነ የሚጠቁመውን አቅጣጫ ተከትሎ የመስጂዱን ሚህራብ ሊገነባ ይገባል።
ከሰላት መስፈርቶች መካከል “ኒያ” ይገኝበታል። የኒያ ቦታው ቀልብ ነው። ኒያ የሰላት ሸርጥ መሆኑ እዚህ ቦታ ሲጠቀስ አንድን ሰላት ነጥሎ ወይም ለይቶ ለመስገድ መነየትን ማለታችን እንጂ በልቁ ስናስተውል አንድ ጤናማ አዕምሮ ያለው እና ነገሮችን ሳይገደድ በምርጫው የሚሰራ ሰው ተነስቶ ውዱእን አድርጎ ወደ መስጂድ ሄዶ ከሰገደ በኋላ ያለ ኒያ ሰግዷል ማለት ፈፅሞ የማይታሰብ ጉዳይ ነው። ሆኖም ኒያን አስመልክቶ ስንናገር ሰላትን ከሰላት መለየት የሚለውን ኒያን ነው የምንፈልግበት። ዙህር ሰላትን ዙህር ብሎ፣ዐስር ሰላትን ዐስር ብሎ፣ መግሪብ ሰላትን መግሪብ ብሎ፣ኢሻ ሰላትን ኢሻ ሰላት ብሎ፣ፈጅር ሰላትን ፈጅር ብሎ መነየት ግዴታ ነው። ሰላትን ከየትኛውም የሰላት ዓይነት ሳያቆራኙ እንዲሁ በልቁ ብቻ አስቦ መስገድ በቂ አይደለም። ምክንያቱም ከየትኛውም የሰላት ዓይነት ሳይቆራኙ በልቁ የሚሰገዱ ሰላቶች በሀሳብ ተነጥለው ከሚሰገዱ ሰላቶች ይበልጥ ጠቅለል ያሉ ሀሳቦችን የያዙ ናቸው። እንደ መርሆ ስንመለከተው ደግሞ ጠቅለል ያለ ሀሳቦችን የያዙ ደግሞ ለየት ያሉ ሀሳቦችን የያዙ ነገሮችን አያስተናግዱም። ማለትም በጥቅሉ ሰላትን ያሰበ ለየት ያለ ሰላትን አስቦ ሰግዷል አይባልም። ሆኖም ለየት ያለ ሰላት አስቦ የሰገደ ግን በውስጡ ስለሚካተቱ ጥቅል የሆኑ ሰላቶችንም ሰግዷል ይባላል።
በመሆኑም አንድ ሰው ጥቅል ከሆኑ ሰላቶች ለየት ወዳሉ ወይም ለየት ካሉ ሰላቶች ወደ ጥቅል ሰላቶች መሸጋገር አይፈቀድም እንላለን። ጥቅል ከሆኑ ሰላቶች ለየት ወዳሉ ሰላቶች ከተሸጋገረ ልቅ አድርጎ የነየተው ሰላት ይበላሽበታል። ለየት ካሉ ሰላቶች ወደ ሌላ ለየት ያሉ ሰላቶች ከተሸጋገረ የመጀመሪያው ሁለተኛው ሰላት ይበላሽበታል። ይህ ጥቅላዊ አባባል ግልፅ ይሆን ዘንድ በምሳሌ እንደሚከተለው አብራራዋለሁ።
አንድ ሰው በጊዜ ያልተገደበ እና ልቅ የሆነ ሱና ሰላት መስገድ ጀምሮ ከዚያም በጊዜ ወደ ተገደበ የሱና ሰላት መሸጋገር ቢፈልግ፤ ማለትም በጊዜ ያልተገደበ እና ልቅ የሆነ ሱና ሰላትን ወደ ራቲባ (ፈርድ ሰላት ተከትለው የሚመጡ ሱና ሰላቶች) ለመቀየር ቢነይት፤እዚህ ጋ ይህ ተግባር አይፈይደውም እንላለን።ምክንያቱም ራቲባ ሱናዎች ከተክቢረተል ኢህራም በፊት መነየት ይኖርባቸዋልና። ይህ ካልሆነ ግን ሰላቱ ራቲባ አይባልም። ምክንያቱ የሰላቱ ጅምሬ ላይ ሰላተል ራቲባ ስላልነየተ። ሆኖም ራቲባ ሰላትን እየሰገደ በጊዜ ያልተገደበ እና ልቅ ወደ ሆነ ሱና ኒያውን ቢቀይር ሰላቱ ትክክል ነው። ምክንያቱም ለየት ያለ ኒያ ያለው ሰላት ልቅ የሆኑ ሰላቶችንና ለየት ያሉ ሰላቶችን በውስጡ ይዟልና። ለየት ያለው ሰላት ለመስገድ ያሰበውን ሲተው ልቅ የሆነው የሰላት ኒያ ባለበት ይቀራል።
ሌላኛው ምሳሌ፦ አንድ ሰው ዐስርን ለመስገድ ነይቶ ወደ ሰላት ገባ እንበል። መሃል ሰላት ላይ ዙህርን እንዳልሰገደ ትዝ አለው። የዐስር ኒያውን ወደ ዙህር ኒያ ቢቀይር። ዙህሩም ሆነ ዐስር ሰላቱ ተቀባይነት የለውም። "ዐስር ሰላቱ ተቀባይነት የለውም"። ያልንበት ምክንያት ኒያውን ስላቋረጠ ሲሆን ዙሁር ሰላቱ ደግሞ ተቀባይነት የለውም። ያልንበት ምክንያት ደግሞ መጀመሪያው ሰላት ላይ ዙህርን እሰግዳለሁ ብሎ ስላልነየተ ነው። ሆኖም ይህን ሁክም ሳያውቅ ይህን ድርጊት ፈፅሞ ከሆነ ለርሱ ትርፍ ሱና እንደሰገደ ይቆጠርለታል። ምክንያቱም ለየት ያለውን ኒያ ሲተው ልቅ የሆነው ሰላት ባለበት ይዘልቃል።
ባጭሩ፦ ዒባዳ ላይ ልቅ የሆነውን ኒያን ሳያስብ የሚፈፅም ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም አንድ ግለሰብ ሲናገርም ሆነ ሲተገብር አስቦ እንጂ ማንኛውንም ድርጊት አይፈፅምም። ሆኖም ኒያን አስመልክቶ ለይቶ እና ገድቦ መነየት ነው ግዴታ የሚሆነው።
እንደዚሁም ኒያ ላይ ከሚካተቱ ነገሮች መካከል ለብቻው እየሰገደ ሳለ ወደ ኢማምነት ኒያውን ቢቀይር ወይም ለብቻው እየሰገደ ሳለ ሌላን ሰው ተከትሎ ወደ መስገድ ኒያውን ቢቀይር፤ይህን አስመልክቶ በዑለማዎች መካከል ኺላፍ አለ። ሆኖም ትክክለኛው አቋም ችግር የለውም የሚለው ሀሳብ ይሆናል። ብቻውን እየሰገደ ወደ ኢማምነት ኒያውን መቀየር ማለትም አንድ ሰው ብቻውን ሰላት መስገድ ጀምሮ ሳለ ከዚያም ሌላኛው ሰው መጥቶ ጀማዓን አስቦ ተከትሎት ቢሰግድ ይህ ድርጊት ችግር የለውም። ማስረጃችንም መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የለሊት ሰላት እያሰገዱ ሳለ ዐብዱላሂ ኢብኑ ዓባስ ተኝተው ነበርና ከንቅልፋቸው ነቅተው ውዱእ ካደረጉ በኋላ መልክተኛውን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ተከትለው መስገድ ጀመሩ ይህን አይተው መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ድርጊቱ በዝምታ አፀደቁለት። ማስረጃ እስካልመጣ ድረስ እዚህ ቦታ ላይ መሰረታዊ መርሆው ሱና ሰላት ላይ የፀደቀ ፈርድም ሰላት ላይ ይፀድቃል። የሚለው ሀሳብ የፀና ይሆናል።
ብቻውን እየሰገደ ሳለ ሌላው ሰው መጥቶ ኢማም አድርጎት መከተል ቢጀምር ሰላቱ ላይ ችግር የለውም። የመጀመሪያው ሰው ኢማም ቀጥሎ የመጣው ሰው ደግሞ ተከታይ ሆኖ መስገድ ይቻላል። በተቃራኒውም እንዲሁ። ማለትም ብቻውን ሰላት ጀምሮ ሳለ ሌሎች መጥተው ጀመዓ ሆነው ሰላታቸውን ቢጀምሩ እነሱን መቀላቀል ይፈቀድለታል። በዚህም ድርጊቱ ለብቻ መስገዱን ትቶ ወደ ጀመዓ ሰላት ተሸጋገረ ማለት ነው። ይህ ድርጊት ችግር የለውም። ምክንያቱም ይህ ኒያን ማበላሸት ውስጥ አይካተትም። ነገር ግን ሰውየው ያደረገው ነገር ቢኖር ከነጠላ ወደ ህብረት ወደሚለው መገለጫ ነው የተሸጋገረው። ስለዚህም ይህ ድርጊት ችግር የለውም። ይህን መስፈርት አስመልክቶ መናገር እጅግ ወሳኝና አንገብጋቢ ርዕስ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የሰላት መስፈርቶች አሉ ለምሳሌ፦ ኢስላም መሆን፣ጥሩንና መጥፎ የመለየት የዕድሜ ደረጃ ላይ መድረስ፣ እንዲሁም ጤናማ አዕምሮ መኖር የሚሉት ይገኝበታል። ሆኖም እነዚህ መስፈርቶች ሰላትን ብቻ የሚመለከቱ ሳይሆኑ ማንኛውንም የዒባዳ መስፈርቶች ላይ የሚጠቀሱ ናቸው።