ጥያቄ(15): ይህን ጥያቄ እንድናነሳ ያነሳሳን ነገር ቢኖር አንዳንድ ሰዎች ዒባዳ እንዲሰሩ ጥሪ ሲደረግላቸው አላህ ቀልብን ነው የሚያየው በማለት ስራን እርግፍ አድርገው የሚተዉ አሉ። በዚህ አባባል (አመለካከት) ላይ ሐሳብ ቢሰጡበት እንወዳለን።
መልስ:
አዎን። አላህ ቀልብን ብቻ ሳይሆን የቀልብንም የአንደበትንም ስራ የሚመለከትና የሚሰማ ጌታ ነው እንላለን። ቀልብ ሲስተካከል ውጫዊ አካልም ይስተካከላል። ምክንያቱም የአላህ መልክተኛ እንዲህ ብለዋልና፦ “እነሆ! አካል ውስጥ አንዲት ቁራጭ ስጋ አለች እርሷ ስትስተካከል ሌላውም አካል ይስተካከላል። እርሷ ስትበላሽ ሌላውም አካል ይበላሻል። እርሷም ቀልብ ናት።” አንዳንድ ሰዎች ወንጀል ፈፅመው ስታገኛቸውና ስትመክራቸው “ተቅዋ ልብ ውስጥ ናት! ።” በማለት ወደ ደረታቸው እየጠቆሙ የሚሞግቱ ሰዎች ይህ ሐዲስ ሙገታቸውን በሙሉ ውድቅ እንደሆነ ያሳያል። ምናልባት ቃሉ እንደጥቅል ስናየው ትክክክል ቢሆንም ተናጋሪው ግን ባጢል መልዕክትን ነው የሚፈልግበት። አላህ ያለውን እስኪ ተመልከት ፦ “እነዚያ ያጋሩት «አላህ በሻ ኖሮ እኛም አባቶቻቸንም ባላገራን ነበር፡፡ አንዳችንም ነገር እርም ባላደረግን ነበር ይላሉ፡፡” [አልአንዐም:148]
እነዚህ ሙሽሪኮች አላህ ባይሻ ኖሮ ባላጋራን አሉ። አዎን! እውነት ተናገሩ። ነገር ግን ይህን ሲሉ ሐቅ የሆነ መልክትን አስበውበት ሳይሆን ሽርክ ላይ መቆየታቸውን እና ድክመታቸውን ለመሸፋፈንና ቅጣት እንዲነሳላቸው ብለው እንጂ ለሌላ አይደልም። ለዚህም ነው አላህ እንዲህ ሲል መለሰላቸው ፦
“እንደዚሁ (እነዚህን እንደዋሹ) እነዚያ ከበፊታቸው የነበሩት ብርቱ ቅጣታችንን እስከቀመሱ ድረስ አስተባባሉ፡፡” [አልአንዐም:148]
ስለዚህም በሽርክ ላይ ለመቀጠል፤ ወቀሳና ቅጣት እንዲነሳላቸው ቀደርን ምክንያት ማድረጋቸው አልጠቀማቸውም።
እውነታው ግን አላህ ባይሻ ኖሮ ባላጋራን እንዳሉት ነው። አላህ ለመልክተኛው እንዲህ ይላቸዋል፦
“ከጌታህ ወደ አንተ የተወረደውን ተከተል፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ አጋሪዎችንም ተዋቸው፡፡አላህም በሻ ኖሮ ባላጋሩ ነበር፡፡ በእነሱም ላይ ጠባቂ አላደረግንህም፡፡ አንተም በእነሱ ላይ ኃላፊ አይደለህም፡፡” [አልአንዐም:106_107]
ነገርግን በሁለቱ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ለመልክተኛው አላህ እንዲህ አላቸዋል። “አላህም በሻ ኖሮ ባላጋሩ ነበር፡፡” ይህም ያለበት ምክንያት ሽርካቸው በርሱ ፍላጎት የተከሰተ መሆኑን ለመጠቆም ሲባል ነው። እነርሱ ሽርክ ላይ መውደቃቸው የራሱ የሆነ ጥበብ አለው። በተጨማሪም ይህ ድርጊታቸው በአላህ መሻት የተከሰተ በመሆኑ ሊያጽናናቸው ሲል ነው ይህን የተናገረው። ያም ሆነ ይህ! ምክር ሲለገስ “ተቅዋ ልብ ውስጥ ነው።” በማለት ነውሩ የሚሸፍንና ምክርን የማይቀበል ቃሉ ሐቅ ቢሆንም የሚፈልግበት መልዕክት ግን ውድቅ ነው። “ተቅዋ ልብ ውስጥ ነው።” ያሉት መልክተኛ እሳቸው ናቸው ደግመው፦ “እነሆ! አካል ውስጥ አንዲት ቁራጭ ስጋ አለች እርሷ ስትስተካከል ሌላውም አካል ይስተካከላል።እርሷ ስትበላሽ ሌላውም አካል ይበላሻል። እርሷም ቀልብ ናት።” ያሉት። በቀልብ ውስጥ ተቅዋ ካለ ውጫዊ አካልም ላይ ተቅዋ መታየቱ የግድ ነው። ውጫዊ ተግባር የውስጣዊ ተግባርን ጠቋሚ ነውና።