Back to Top
ግዴታ የሆኑ ሰላቶች አሰጋገድ እንዴት ነው?

ጥያቄ(94): ግዴታ የሆኑ ሰላቶች አሰጋገድ እንዴት ነው?
መልስ:

የሰላት አፈፃፀምን ማወቅ ከማንኛውንም የዒባዳ አፈፃፀም እጅግ የላቀ ግምትና አሳሳቢነት አለው። ምክንያቱም ማንኛውም ዒባዳ ኢኽላስና የመልክተኛውን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አፈፃፀም ካልተከተለ የተሟላ አይሆንም። አንድ ሰው ረሱልን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም  “ሙታባዓህ” ማድረግ የሚችለው መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አንድን ኢባዳ የፈፀሙበትን መንገድ በዝርዝር ሲያውቅ ብቻ ነው።

 የሰላት አፈፃፀምን ማወቅ እጅግ ወሳኝና አሳሳቢ ነው። መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በፈፀሙት አፈፃፀም ይፈፅሙ ዘንድ እኔንም ሆነ ሙስሊም ወንድሞቼን በሙሉ የሰላት አፈፃፀም ከቁርኣንና ከትክክለኛ የነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሶች እና ግምት ከሚሰጣቸው የሱና ኩቱቦች መውሰድ ይኖርባቸዋል ስል ቅስቀሳ ማድረግ እሻለሁ። ምክንያቱም መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የእኛ አርዓያና ተምሳሌታችን ናቸው። እሳቸውን በኢኽላስ ከሚከተሉ ያደርገን ዘንድ አላህን እንማፀነዋለን። እዚህ ቦታ ላይ የመልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አሰጋገድ በዝርዝር እንጠቅሳቸዋለን። ሀቁንና ትክክለኛውን ይገጥመን ዘንድ አላህን አዘወጀለ እንለምነዋለን።

የሰላት አሰጋገድ ከመጀመራችን በፊት የሰላት መስፈርቶች ማለትም ከሐደስ እና ከነጃሳ ጠሃራ መሆን፣ወደ ቂብላ መቅጣጨትና ሌሎችም የተቀሩት የሰላት መስፈርቶች በቅድሚያ መፈፀማቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ከዚያም ወደ ትከሻ ወይም ጆሮ ትይዩ እጆቹን በማንሳት  “አላሁ አክበር” በማለት ተክቢራ ያደርጋል፣ከዚያም ቀኝ እጁን ግራ ክንዱ ላይ በማድረግ ደረቱ ላይ ያሳርፋል። ከዚያም ከመልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በትክክለኛ ሰነድ ተዘግበው የመጡ የሰላት መክፈቻ ዱዓዎች መካከል አንዱን ያነባል። ሆኖም በየትኛውም የሰላት መክፈቻ ዱዓ ቢጀምር ችግር የለውም። ለምሳሌ፦ ቀጣዩን የመክፈቻ ዱዓ ማድረግ ይችላል፦

 

“አላሁመ  ባዒድ በይኒ ወበይነ ኸጣያየ ከማ ባዐድተ  በይነል መሽሪቅ ወልመግሪብ አሏሁመ ነቂኒ ሚን ኸጣያየ ከማ ዩነቀ ሰውቡል አብየድ ሚነ ደነስ አላሁም ኢግሲልኒ ሚንኸጣያየ ቢልማኢ ወሰልጂ ወል በረድ” የሚለውን ዱዓ ማድረግ ይችላል። አሊያም ደግሞ ፦ “ሱብሓነከ አላሁመ ወቢሀምዲከ ፣ተባረከ ኢስሙክ ወተዓላ ጀዱክ፣ወላኢላሃ ገይሩክ።” ወይም ሌሎች ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ተዘግበው ከመጡ ዱዓዎች መካከል አንዱን መርጦ ማድረግ ይችላል።

ከዚያም ፤ “አዑዙ ቢላሂ ሚነ ሸይጣን ረጂም፣ቢስሚላሂ አረህማኒ አረሂም፤” ካለ በኋላ ፋቲሃን ያነባል። በእያንዳንዱ አንቀፅ ላይ ቆም እያለ ትንፋሽ መውሰድ ይኖርበታል። እንዲህ ይላል፦

الْحَمْدُ لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ ﴿٢﴾ الرَّحْمَٰنِ الرَّحِيمِ ﴿٣﴾ مَالِكِ يَوْمِ الدِّينِ ﴿٤﴾ إِيَّاكَ نَعْبُدُ وَإِيَّاكَ نَسْتَعِينُ ﴿٥﴾ اهْدِنَا الصِّرَاطَ الْمُسْتَقِيمَ ﴿٦﴾ صِرَاطَ الَّذِينَ أَنْعَمْتَ عَلَيْهِمْ غَيْرِ الْمَغْضُوبِ عَلَيْهِمْ وَلَا الضَّالِّينَ ﴿٧﴾

(አልሐምዱሊላሂ ረቢል ዓለሚን፣አረሕማኒ አረሂም፣ማሊኪ የውሚዲን፣ኢያከ ነዕቡዱ ወኢያከ ነስተዒን፣ ኢህዲነ ሲራጠል ሙስተቂም፣ ሲራጠለዚነ አንዐምተ ዐለይሂም ገይሪል መግዱቢ ዓለይሂም ወለዷሊን።)

ከዚያም ከቁርኣን አንቀፅ የገራለትን ያነባል። ፈጅር ሰላት ረጃጅም እና ሙሉ ሱራዎችን ቢያነብ የተሻለ ነው። መግሪብ ላይ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ አጫጭር ሱራዎች ቢነበቡ ይመረጣል። የተቀሩት ሰላቶች ላይ ደግሞ መካከለኛ በሆኑ ሱራዎች መስገድ የተመረጠ ተግባር ነው።

ከዚያም እጆቹን ወደ ጆሮው ትይዩ በማንሳት “አላሁ አክበር” በማለት ሩኩዕ ያደርጋል። የእጆቹን ጣቶች በመሃላቸው ክፍተት በመፍጠር ጀርባውን በራሱ ትይዩ ያደርጋል ማለትም ራሱን ከፍ አያደርግም፣ ጀርባውን አያጎብጥም፤ ከዚያም “ሱብሓነ ረቢየል ዐዚም” ይላል። የተሟላው ዚክር በትንሹ ሦስቴ በመደጋገም ማለት ሲኖርበት ከዚህም በላይ መጨመር ይችላል።

ከዚያም “ሰሚዐላሁ ሊመንሐሚደህ” በማለት ከተጎነበሰበት ይነሳል። ተክቢረተል ኢህራም ላይና ሩኩዕ ላይ እጆቹን እንዳነሳው እዚህም ጋር ያነሳል። ተስተካክሎና ቀጥ ብሎ ከቆመ በኋላ፤ “ረበና ወለከል ሀምድ፣ሀምደን ከሢይረን ጠይበን፤ ሙባረከን ፊይሂ፣ሚልኡ ሰማዋቲ ወሚኡል አርዲ ወሚልኡ ማበይነሁማ፤ ወሚልኡ ማሺእተ ሚን ሸይኢን በዕዱ።” ካለ በኋላ  “አላሁ አክበር” ብሎ ወደ ሱጁድ ይወርዳል፤ ወደ ሱጁድ ሲወርድ እጆቹን ወደ ጆሮዎቹ ትይዩ ማንሳት የለበትም። ዐብዱላሂ ኢብኑ ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ  መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይህን አይደርጉም ነበር ብለዋል። ማለትም ከሱጁድ ሲነሱ እጃቸውን አያነሱም ነበር። መጀመሪያ ጉልበቶቹን መሬት ላይ በማሳረፍ ቀጥሎ መዳፎቹን ያስቀምጣል። ከዚያም በሰባት የሱጁድ አካላቱ ሱጁድ ያደርጋል። ማለትም ግንባር እና  አፍንጫ፣ እንደ አንድ አካል ነው የሚቆጠሩት። ሁለቱ መዳፎች፣የሁለቱም እግሮች ጣቶች ጫፍ፤ጡንቻዎቹን ከጎድን አጥንቶቹ ማራራቅ ይኖርበታል። ጀርባውን ከፍ ያደርጋል አይለጥጠውም። መዳፎቹን በመካከላቸው ምንም ክፍተት ሳይፈጥር በማገጣጠም  እና በመዘርጋት በፊቱ ወይም ትከሻው ትይዩ ያደርጋል። የጣቶቹ አቅጣጫ ወደ ቂብላ መሆን ይኖርባቸዋል። ከዚያም “ሱብሓነ ረቢየል አዕላ” ይላል።  የተሟላው ዚክር በትንሹ ሦስቴ በመደጋገም ማለት ሲኖርበት ከዚህም በላይ መጨመር ይችላል። ሆኖም ሱጁድ ላይ ዱዓ ማብዛቱ ተመራጭ ነው። ምክንያቱም መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋልና፦ “ሩኩእ ላይ  ስትሆኑ ጌታቹን አልቁ፤ሱጁድ ላይ ደግሞ ዱዓ በማድረግ ጥረት አድርጉ፤(ዱዓችሁ) ተቀባይነት ሊኖረው የተገባ ነውና።”

ከዚያም ተክቢራ በማድረግ ከሱጁድ ብድግ ይላል። መዳፎቹን በጆሮዎቹ ትይዩ በማድረግ ማንሳት የለበትም። ግራ እግሩን በማንጠፍ ቀኝ እግሩን ደግሞ በመትከል በቂጡ ቁጭ ይላል። መዳፎቹን በታፋው ወይም በጉልበቶቹ ላይ ያሳርፋል። ቀኝ እጆቹ ላይ የሚገኙ ሦስቱ ጣቶች በመሰብሰብ ማለትም ትንሿ ጣት፣ የቀለበት ጣት እና አውራ ጣትን በማሰባሰብ አሊያም አውራ ጣትን ከመሃለኛው ጣት ጋር ክብ አድርጎ በመያዝ አመልካች ጣትን ዝርግ እንደሆነ ወደ ቂብላ በመጠቆም በየዱዓው ማንቀሳቀስ ይቻላል። “ረቢ ኢግፊርሊ ወርሀምኒ ወጅቡርኒ ወዓፊኒ ወርዙቅኒ” ብሎ ዱዓ ያደርጋል። ዱዓ ባደረገ ቁጥር አመልካች ጣትን ወደ ሰማይ በማድረግ ማንቀሳቀስ ይኖርበታል። ይህንንም የሚያደርገው የሚለመነው አካል (አላህ) አዘወጀል የበላይ መሆኑ ለመጠቆም ነው። የግራ እጅን ደግሞ  በግራ ታፋ ወይም በጉልበት ጫፍ ላይ በማድረግ መዳፎች ዝርግ እንደሆኑ ወደ ቂብላ ማቅጣጨት ከዚያም መጀመሪያው ሱጁድ ላይ ሲለው የነበረውን ዱዓ እና ሲሰራው የነበረውን ተግባር በመድገም ሁለተኛውን ሱጁድ ያደርጋል።

  ከዚያም ተክቢራ በማድረግ ከሱጁድ በመነሳት ወደ ቀጣዩ ረከዐ ይሸጋገራል። እዚህም ቦታ መዳፎቹን ወደ ጆሮቹ ትይዩ ማንሳት የለበትም። ምክንያቱም ይህ ድርጊት በትክክለኛው ሐዲስ ከመልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አልተዘገበምና። ከዚያም ፋቲሃ እና ከሱራ የገራለትን ይቀራል። እዚህኛው ረከዐ ላይ ግን እንደመጀመሪያው ረከዓ ሱራውን ማስረዘም የለበትም። መጀመሪያ ረከዓውን እንደሰገደው ይሰግዳል። ከዚያም “አተህያቱን” ለመቅራት ቁጭ ይላል። በሁለቱ ሱጁዶች መካከል እንደተቀመጠው አቀማመጥ ይቀመጣል። ከዚያም ፦

 “አተሕያቱ ሊላህ ወሰላዋቱ ወጠይባቱ፣ አሰላሙ ዐለይከ አዩሃ ነቢዩ፣ወራሕመቱላሂ ወበረካትሁ፣አሰላሙ ዐለይና ወዓላ ዒባዲላሂ ሷሊሂን፣አሽሀዱ አን ላኢላሀ ኢለሏህ ወአሽሀዱ አነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ” በማለት ተሸሁድ ያነባል።

ባለ ሦስት ወይም ባለ አራት ረከዓ ሰላት ከሆነ ሁለተኛው ረከዐ ላይ ተቀምጦ ተሸሁድ ከቀራ በኋላ ሰላዋት ሳይጨምር  ሦስተኛውን ወይም አራተኛውን ረከዓ ለመስገድ ብድግ ይላል ፋቲሃን ብቻ በማንበብ የተቀሩት ረከዓዎችን ይሰግዳል። ከዚያም ከላይ ባሳልፈነው መሰረት ሩኩእና ሱጁድ ያደርጋል። ከዚያም ሁለተኛውን ተሸሁድ ለመቅራት ቁጭ ይላል። ነገር ግን አቀማመጡ ከመጀመሪያው ተሸሁድ አቀማመጥ ይለያል። አቀማመጡም “ተወሩክ” ይባላል።

“ተወሩክ” የሚባለው አቀማመጥ ሦስት አይነት አቀማመጥ አለው። አንደኛው ቀኝ እግሩን በመትከል ግራ እግሩን በቀኙ ባት በኩል ያሳልፍና በቂጡ መሬት ላይ ይቀመጣል። ሁለተኛው ደግሞ፤ ሁለቱንም እግሮች በማንጠፍ ወይንም በቀኝ እግር ባት ስር በማሳለፍ ይቀመጣል። ሶስተኛው፤ ቀኝ እግሩን መሬት ላይ ያነጥፍና ግራ እግሩን በቀኝ ታፋና ባት በኩል በማሳለፍ በቂጡ ቁጭ ይላል። እነዚህ አቀማመጥ በሙሉ ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ተዘግበው መጥተዋል። ከዚያም “ተሸሁዱንና” “ሰለዋት አለ ነቢ” ከጨረሰ በኋላ ከላይ ባሳለፍነው መሰረት በቀኝና በግራ ያሰላምታል።

የነቢዩ ሰለሏሁ አለይሂወሰለም አሰጋገድ ይህን ይመስላል። ስለዚህም አንድ ሰው በተቻለው አቅም አሰጋግዱን ከእርሳቸው ጋር በማመሳሰል ሊሰግድ ይገባል። ይህን ካደረገ የተሟላ ዒባዳ እንደፈፀመ ይቆጠርለታል። እንዲሁም ኢማኑ የተጣናከረና መልክተኛውን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መከተል ላይ ጠንካራ መሆኑንን ያረጋግጣል።
Share

ወቅታዊ