ጥያቄ(92): ውዱእ ያለው ሰው ተየሙም አድርጎ የሚሰግድን ሰው ተከትሎ መስገድ ይቻላልን?
መልስ:
አዎን። ተየሙም ያደረገ ውዱእ ያደረገ ሰውን ኢማም ሆኖ ማሰገድ ይችላል እንላለን። ምክንያቱም ሁለቱም በተፈቀደ የጠሃራ ዓይነት ሰግደዋልና።
ሁለተኛው የጠሃራ አይነት፦ ከነጃሳ ንፁህ መሆን ሲሆን ቦታዎቹም ሦስት ናቸው። እነሱም፦ ከሰውነት ፣ ከልብስና ከመስገጃ ስፍራ ላይ ያለን ነጃሳ ማፅዳት ነው። ማስረጃውም ደግሞ የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሁለት መቃብሮች መካከል ሲያልፉ ፦
“እነዚህ መቃብሮች ውስጥ ያሉ ሰዎች እየተቀጡ ነው። የሚቀጡበትም በከባድ ወንጀል የተነሳ አይደለም፤አንደኛቸው ሽንቱ እንዳይነካው አይሸሸግም(ጥንቃቄ) አያደርግም ነበር።”
እንደዚሁም የአላህ መልክተኛ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ደሙ ልብሷን ከነካ እንድታጥበው እና ከዚያም እንድትሰግድበት አዘዋል። ከዚህ ሐዲስ የምንረዳው ነጃሳ የነካው ልብስ ጠሃራ መደረግ አለበት። መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘንድ አንድ ከወተት ውጭ ምግብ ያልተመገበ ህፃን ልጅ መጥቶ ታፋቸው ላይ እንዳስቀመጡት ላያቸው ላይ ሸና። ውሃ እንዲመጣላቸው ካዘዙ በኋላ ሽንቱ ላይ ውሃውን አስከትለው አፈሰሱት።
መስገጃ ስፍራ ደግሞ ጠሃራ መደረግ እንዳለበት የሚያሳየው መረጃ ደግሞ አነስ ኢብኑ ማሊክ ባስተላለፉት ሐዲስ አንድ ገጠሬ የሆነ ሰው መስጂድ መጥቶ ጫፍ ላይ ሸና። መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በባልዲ ውሃ እንዲመጣ፣ ካዘዙ በኋላ ቦታው ላይ ውሃ እንዲፈስ አደረጉ።
ስለዚህም የሰው ልጅ ከሰውነቱ፣ከልብሱና ከመስገጃው ስፍራ ነጃሳን መራቅና መጠንቀቅ ይኖርበታል።
ሰውነቱ ላይ ነጃሳ ኖሮበት ቢሰግድ፤ ማለትም አካሉ ላይ ወይም ልብሱ ላይ ወይም መስገጃው ላይ ነጃሳ መኖሩን ሳያውቅ ወይም መኖሩን አውቆ ግን ረስቶት ሳያጥበው ሰላቱን ሰግዶ ቢያጠናቅቅ ሰላቱ ተቀባይነት ያገኛል። ዳግም መስገድም አይጠበበትም። ለዚህም ማስረጃው መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከእለታት አንድ ቀን ሰሓቦችን እያሰገዱ ሳለ ጫማቸውን አውልቀው ጣሉ፤ሰሓቦችም ጫማቸውን አውልቀው ጣሉ። መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰላታቸውን እንደጨረሱ ሰሃቦቹ ጫማቸውን ያወለቁበትን ምክንያት ጠየቋቸው። እነሱም፦ “እርሶ ሲያወልቁ ተመለከትን እኛም አወልቅን” በማለት መለሱላቸው። መልክተኛውም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ፦”ጂብሪል መጥቶ ጫማዬ ላይ ነጃሳ እንዳለ ነገረኝ (ስለዚህም አወለቅኩ)።” በማለት ነገሯቸው።
አንድ ሰው ሳያውቅ ነጃሳን ይዞ መስገድ ሰላትን የሚያበላሽ ቢሆን ኖሮ ዳግም ሰላታቸውን በሰገዱ ነበር። አንድ ሰው እየሰገ ሳለ ውዱእ እንደሌለው ካስታወሰ ወዲያውኑ ከሰላት በመውጣት ውዱእ ማድረግ ይኖርበታል። ስለዚህም ከሰውነት ከልብስና ከመስገጃ ስፍራ ነጃሳን ማስወገድ የሰላት መስፈርት ነው ማለት ነው። ሆኖም ከመስገዱ በፊት ነጃሳ መኖሩን አውቆ ከዚያም ማጠቡ ረስቶ ቢሰግድ ወይም ሰላቱን ካጠናቀቀ በኋላ ነጃሳ መኖሩን ቢያውቅም ሳያውቅ ወይም ረስቶ ቢሰግድ ሰላቱ ተቀባይነት አለው።
ያለ ውዱእ ረስቶ ወይም ሳያውቅ የሰገደ ዳግም ውዱዕ ማድረግ አለበት። ሆኖም "ነጃሳ መኖሩን ሳያውቅ አሊያም ረስቶ የሰገደ ደግሞ መስገድ አለበት"። ስንል ውዱእ ማድረጉን ሳያውቅ የሰገደ እና ነጃሳ መኖሩን ሳያውቅ የሰገደ ልዩነት ምንድ ነው ብለህ ብትጠይቀኝ፤ ለዚህ ምላሻችን ውዱእና ትጥበት ትእዛዛትን ከመፈፀም ውስጥ የሚካተት ነው፤የታዘዘን ትዕዛዝ ሳያውቅ ወይም ረስቶ ቢተው ምንም ዑዝር የለውም። የተከለከለ ነገር ግን በተቃራኒው ነው።
ከሰላት መስፈርቶች መካከል፦ ወደ ቂብላ ዞሮ መስገድ ይገኝበታል። አላህ እንዲህ ይላልና ፦
“የፊትህን ወደ ሰማይ መገላበጥ በእርግጥ እናያለን፡፡ ወደምትወዳትም ቂብላ እናዞርሃለን፡፡ ስለዚህ ፊትህን ወደ ተከበረው መስጊድ (ወደ ካዕባ) አቅጣጫ አዙር፡፡ የትም ስፍራ ብትኾኑም (ስትሰግዱ) ፊቶቻችሁን ወደርሱ አቅጣጫ አዙሩ፡፡” [አልበቀራ:144]
ስለዚህም ወደ ቂብላ (ከዕባ) መቅጣጨት ከሰላት መስፈርቶች አንዱ ሲሆን ያለ ቂብላ የሰገደ ሰላቱ ተቀባይነት የለውም። ምናልባት አራት ሁኔታዎች ላይ ሲቀር ሰላቱንም እንደሰገደ አይቆጠረም።
አንደኛው ሁኔታ፦ ወደ ቂብላ ዞሮ መስገድ አለመቻል። ምሳሌው፦ አንድ ህመምተኛ ፊቱ ከቂብላ ውጭ ዞሮ በህመሙ ምክንያት ወደ ቂብላ መዞር ሳይችል ቀርቶ ያለ ቂብላ ቢሰግድ ሰላቱ ተቀባይነት አለው። ምክንያቱም አላህ አዘወጀለ እንዲህ ብሏልና፦
“የአቅማችሁን ያህል አላህን ፍሩ።” [አተጋቡን:16]
ይህ ሰው ደግሞ በራሱም ሆነ በሌሎችም ድጋፍ ወደ ቂብላ መዞር አይችልም።
ሁለተኛው ደግሞ ፦ ከጠላት ፈርቶ እየሸሸ ባለበት ወቅት ከቂብላው ውጭ ቢሰግድ በመሰረቱ እዚህ ቦታ ላይ ወደ ቂብላ መዞር ግዴታነቱ ለርሱ ይነሳለታል። አላህ አዘወጀለ እንዲህ ይላል፦
“ብትፈሩም እግረኞች ወይም ጋላቢዎች ኾናችሁ (ስገዱ)፡፡” [አልበቀራ፡139]
እንደሚታወቀ ከጠላት የሰጋ ሰው ፊቱ ወደ ቂብላ ወይም ከቂብላ ውጭ ነው የሚሆነው፤ እየሮጠም እየጋለበም መስገድ ከተፈቀደለት ከዚህ የምንረዳው ለነፍሱ በመስጋቱ የተነሳ ፊቱ ከቂብላ ውጭ ሆኖ መስገድ ይችላል ማለትን ነው።
ሦስተኛው ሁኔታ፤ ጎዞ ላይ ሳለ ሱና ሰላትን መጓጓዣው ላይ መስገድ ቢፈልግ መጓጓዣው በዞረበት ዞሮ መስገድ ይፈቀድለታል። መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጎዞ ላይ ሳሉ ግመላቸው ላይ ሆነው ግመሏ በዞረችበት ይሰግዱ እንደነበር፤ የሚጠቁም ሐዲስ ፀድቆ መጥቷል። ሆኖም ፈርድ ሰላትን በዚህ መልኩ ይሰግዱ አልነበረም። ሱና ሰላት ከሆኖ ተጓዥ መጓጓዛው ላይ ሆኖ በየትኛውም ስፍራ ፊቱን አዙሮ መስገድ ይችላል። ፈርድ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው መንገደኛው ወደ ቂብላ ዞሮ ካልሆነ መስገድ አይፈቀደለትም።
አራተኛው ሁኔታ ደግሞ ፦ የቂብላ ትክክለኛው አቅጣጫ ሳያውቅ ቢቀር በዚህን ጊዜ ጥረት እና ግምቱ ወደሚያመዝንበት ስፍራ ዞሮ መስገድ ይኖርበታል። ሰላቱ ሰግዶ ካጠናቀቀ በኋላ ቂብላው በተቃራኒ ሆኖ ቢገኝ ሰላቱን መድገም አይጠበቅበትም። ይሀኛው ሁኔታ ከሌሎች ተለይቶ መታየት የለበትም ሊባል ይችል ይሆናል። በዚህ ግዜ ግምቱ የሚያደላበትን ቦታ ዞሮ እንዲሰግድ እንስገድደዋለን። ከቂብላ ውጭ ሰግዶ ቢገኝ ይህ እርሱን አይጎዳውም። ምክንያቱም የመጨረሻ ችሎታና አቅም ይህ ነው።
አላህ እንዲህ ይላል፦
“አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም፡፡” [አልበቀራ፡286] እንዲህም ይላል፦ “የአቅማችሁን ያህል አላህን ፍሩ።” አተጋቡን፡16]