Back to Top
የሰላት ብያኔ እነማን ላይ ግዴታ እንደሚሆን አውቀናል፤ ሰላት የተወ ሰው ደግሞ በሸሪዓው ሁክሙ ምንድ ነው?

ጥያቄ(87): የሰላት ብያኔ እነማን ላይ ግዴታ እንደሚሆን አውቀናል፤ ሰላት የተወ ሰው ደግሞ በሸሪዓው ሁክሙ ምንድ ነው?
መልስ:

በቁርኣን፣ በሱና፣ በሰሓቦች ስምምነት፤ትክክለኛው እይታ እና ለነዚህ ማስረጃዎች ሲባል ሰላት የተወ ሰው በሸሪዓው የሚሰጠው ፍርድ ወይም ብያኔ ከኢስላም መንገድ የሚወጣ ካፊር የሚል ሁክም ይሰጠዋል።

ከቁርኣን ማስረጃዎች መካከል፦

 “አላህ ሙሽሪኮችን አስመልክቶ  ሲናገር እንዲህ ይላል፦”ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም ቢሰግዱ፣ ዘካንም ቢሰጡ የሃይማኖት ወንድሞቻችሁ ናቸው፡፡ ለሚያውቁ ሕዝቦችም አንቀጾችን እናብራራለን፡፡” [አት_ተውባ:11]

ከዚህ የቁርኣን አንቀፅ ሰላት የተወ ሰው ካፊር መሆኑ እንረዳለን። በሙእሚኖችና በሙሽሪኮች መካከል ዲናዊ ወንድማማችነት ይፀድቅ ዘንድ አላህ አዘወጀለ ሦስት መስፈርቶችን አስቀምጧል። እነሱም፦ አንደኛው፤ ከሽርክ ተውበት ማድረግ፣ ሁለተኛው፤ሰላትን መስገድ እና ዘካን መስጠት ናቸው። ከነዚህ መስፈርቶች መካከል አንዱ ከተጓደለ ለአማኞች የዲን ወንድሞች አይሆኑም። እንደሚታወቀው ግልፅ በሆነ እና ከኢስላም በሚያወጣ የኩፍር ዓይነት ቢሆን እንጂ ዲናዊ ወንድማማችነት አይፈርስም። ሀጢዓቶች የቱንም ያህል ቢገዝፉም ኩፍር ደረጃ ካልደረሱ ከኢስላም አያስወጡም። “ቂሳስ” መካካስ አስመልክቶ  አላህ አዘወጀለ ያለውን አትመለከትምን?! ሙስሊም ወንድሙን በማወቅና ሆን ብሎ የገደለን ሰው አስመልክቶ አላህ  (አዘወጀለ) እንዲህ ይላል፦

“ከምዕምናንም የኾኑ ሁለት ጭፍሮች ቢጋደሉ በመካከላቸው አስታርቁ፡፡ ከሁለቱ አንደኛይቱም በሌላይቱ ላይ ወሰን ብታልፍ ያችን ወሰን የምታልፈውን ወደ አላህ ትዕዛዝ እስከምትመለስ ድረስ ተጋደሉ፡፡ ብትመለስም በመካከላቸው በትክክል አስታርቁ፡፡ በነገሩ ሁሉ አስተካክሉም፡፡ አላህ አስተካካዮችን ይወዳልና፡፡ ምእመናኖች ወንድማመቾች ናቸው፡፡ በሁለት ወንድሞቻችሁም መካከል አስታርቁ፡፡ ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ፡፡” [አል ሒጅራት፡ 9 _10]

 አማኝን እያወቁ መግደል እጅግ የከበደ ወንጀል ከመሆኑ ጋር ሦስተኞቹ አስታራቂ የምእመናን ጭፍሮችን እርሰበርስ ለሚገዳደሉት ወንድሞች አላህ አዘወጀለ ወንድማማች አድርጓቸዋል። ከዚህም የምንረዳው ወንጀል ኩፍር ደረጃ ካልደረሰ ዲናዊ ወንድማማችነት በኃጢዓት የተነሳ በጭራሽ ሊወገድ አይችልም። የሚለውን ሀሳብ ይሆናል። ከላይ የተጠቀሰውን አንቀፅ ማብራሪያ፤ በሽርካቸው ላይ ከቀጠሉ ካፊር መሆናቸው ለማንኛችንም  ግልፅ ነው። ካመኑም በኋላ ሰላት ካልሰገዱም እንዲሁ ካፊር መሆናቸው ግልፅ ነው። “ሶላትንም ቢሰግዱ፣ ዘካንም ቢሰጡ…” መስፈርታዊ ከሆነው ከዚህ አ/ነገር የምንረዳው  ከሽርክ ተውበት ካደረጉ ፣ሰላትን ከሰገዱ፣ ዘካ ከሰጡ አማኝ ወይም ሙስሊም ይሆናሉ የሚለውን ነው። ሆኖም ዘካ መስጠትን አስመልክቶ ዛካ ያልሰጠ ይከፍራል አይከፍርም በሚል በዑለማዎች መካከል ኺላፍ አለ። ይህንንም አስመልክቶ ከኢማሙ አሕመድ ረሂመሁላህ ሁለት ዘገባዎች አሉ።

ሆኖም የሐዲስ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ዘካን መስጠት የተወ (ግዴታ መሆኑን ከማመኑ ጋር) አይከፍርም። ለዚህም አቡሁረይራ ያስተላለፉት ሐዲስ ማስረጃ ነው።

መልዕክተኛው ሰለሏሁ አለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ፦

“የወርቅ እና  የብር ባለቤት የዘካ ሀቃቸውን ያላወጣ የቂያማ ቀን የእሳት መተኮሻ ተደርገው ጀርባውን እና ግንባሩን በጀሀነም እሳት ይተኮሳል። (የአኼራ )ቀኑ አምሳ ሺህ አመት ያህል መጠን ሲሆን በባሮቹ መካከል እስኪፈረድ ሰውነቱ ከቅጣቱ በበረደ ጊዜም ተመልሶ ይቀጠላል። ከዚያም የጀነት ወይም የእሳት መቀመጫውን ይመለከታል።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

 ከዚህ ሐዲስ ዘካን የሚከለክል ሰው ካፊር እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ካፊር ቢሆን ኖሮ ወደ ጀነት መቀመጫውን ባልተመለከተ ነበር። ከሐዲሱ መረጃ በመነሳት ዘካ ከሰላት እና ከሽርክ ህግጋት የወጣ ይሆናል ማለት ነው።

ሰላትን የተወ ሰው ካፊር ለመሆኑ ከሐዲስ መረጃው እነሆ ፦ ሙስሊም ጃቢርን ጠቅሰው በዘገቡት ሐዲስ የአላህ መልዕክተኛ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም፦

“በአንድ ግለሰብ  እና  በኩፍር ወይም በሙስሊም መካከል ያለው ልዩነት ሰላት መተው ነው” ብለዋል።  

 ሰላትን የተወ  ሰው ካፊር መሆኑን እና ፤ በእምነት እና በክህደት መካከል ያለው መለያ ሰላት መሆኑን ሀዲሱ ይጠቁማል። በተጨማሪም ሰላት የማይሰግድ ሰው እምነት እንደሌለው ከሐዲሱ መልዕክት ግልፅ ነው። ምክንያቱም የኩፍር ገደብ የሚያስፈርደው ይህን ነውና።

 "بين الرجل وبين الشرك والكفر"
ማለትና
بين الرجل وبين كفر

በመሀከላቸው ሰፊ ልዩነት አለ። ምክንያቱም " كفرየሚለው የአረብኛ ቃል "أل" ሲገባበት ሀቂቃ የሆነውና ከኢስላም የሚያወጣው የኩፍር  አይነት መሆኑን ያሳያል። "أل" ሳይገባት ግን በተቃራኒው ከኢስላም የማያወጣው ኩፍርን ይጠቁማል። ለምሳሌ ፦

قوله صلى الله عليه وسلم : "اثنتان في الناس هما بهم كفر: الطعن في النسب ، والنياحة على الميت"

የአላህ መልክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፦

“ሰዎች የማይተዋቸው ሁለት የ(መልስተኛው) ኩፍር ተግባሮች አሉ። እነሱም፦ የሰውን ዘር መተቸትና ሟች ላይ ሙሾ ማውረድ ናቸው።” በዚህ ሐዲስ ላይ የተጠቀሱት ተግባሮች ከኢስላም አያስወጡም።

ሌላኛው ማስረጃ፤ ሰላት የተወ ሰው ካፊር ለመሆኑ ከሰሃቦች ንግግር እነሆ ፦ ዐብደላህ ኢብኑ ሸቂቅ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ብለዋል፦

“የሙሐመድ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ባልደረቦች ከተግባሮች መካከል መተዉ ከሰላት ውጭ ያከፍራል ብለው የሚያምኑበት ነገር አልነበረም።” ሰላት የተወን ሰው ሰሓቦች እንደሚያከፍሩ ኢስሃቅ ኢብኑ ራሆያህ ኢጅማእ (ስምምነት) ዘግበዋል።

ከትክክለኛ እይታ አንፃር ደግሞ የሚከተለውን እንላለን፤ የሰላትን ደረጃ እና ሸሪዓው ለሰላት ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠው እያወቀ  ያለምንም ዑዝር ሰላትን የሚተው ማንኛውም ሰው አላህ አዘወጀለ ዘንድ ምንም ማስረጃ የለውም። በተጨማሪም ሰላት የተወ ልቡ ውስጥ ኢምንት ያህል ኢማን እንዳሌለ አመላካች ነው። ምክንያቱም ልቡ ውስጥ ኢማን ቢኖር  ኖሮ ይህን በኢስላም ትልቅ ቦታ የተሰጠውን ሰላትን ባልተወ ነበር። ነገሮች የሚታወቁት በሚያሳድሩት ተፅእኖ ልክ ነውና። ማለትም በሸሪዓው ሰላት እጅግ አሳሳቢና ከፍተኛ ትኩረት የተቸረው ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ሰላትን መተው ላይ መዘውተሩ ልቡ ውስጥ የስናፍጭ ፍሬ ታክል እንኳ ኢማን እንደሌለው ጠቋሚ ነው።

ከዚህም የቁርኣን የሐዲስ እና የሰሓቦች እንዲሁም ሎጂካዊ መረጃዎች በመነሳት ሰላት የተወ ሰው ከኢስላም ውጭ የሚያወጣ ኩፍር ላይ መሆኑ ነው። በተጨማሪም ዛሬ ላይ ብዙዎቹ የተዘናጉበት የሆነው ሰላት ማስረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት ከሆነ ይህ አይነቱ አስፀያፊ ተግባር ሊርቁትና ሊጠነቀቁት እንደሚገባ ያሳያሉ። ሆኖም ለአላህ አዘወጀለ ምስጋና ይገባውና የተውበት በር ክፍት ነውና ፈጥነው ተውበት ሊያደርጉ ይገባል። አላህ አዘወጀለ እንዲህ ይላል፦

“ከእነሱም በኋላ ሶላትን ያጓደሉ (የተዉ) ፍላጎቶችንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች ተተኩ! የገሀነምንም ሸለቆ በእርግጥ ያገኛሉ፡፡ ግን የተጸጸተና ያመነም በጎንም ሥራ የሠራ ሰው እነዚህ ገነትን ይገባሉ፡፡ አንዳችንም አይበደሉም፡፡ የመኖሪያን ገነቶች ያችን አልረሕማን ለባሮቹ በሩቅ ኾነው ሳሉ ተስፋ ቃል የገባላቸውን (ይገባሉ)፡፡ እርሱ ተስፋው ተፈጻሚ ነውና፤ በእርሷ ሰላምን እንጂ ውድቅን ነገር አይሰሙም፡፡ ለእነሱም በርሷ ውስጥ ጧትም ማታም ሲሳያቸው አላቸው፡፡” [መረየም 59_ 62]

እኛም ሆነ ሙስሊም ወንድሞቻችን አምልኮቱን እሱ በሚወደው እና በሚደሰበት መልኩ ለመፈፀም ይመራን ዘንድ አላህን እንማፀነዋለን።
Share

ወቅታዊ