ጥያቄ(81): ከወር አበባ እና ከወሊድ ደም ጋር የተያያዙ ህግጋት ምንድን ናቸው?
መልስ:
ኡለማዎች ሐይድ (የወር አበባ ደምን) አስመልክቶ እንዲህ ብለዋል፦ ሐይድ ማለት ተፈጥሯዊ እና ጤነኛ የደም ዓይነት ሲሆን አንዲት ሴት ለማርገዝ ብቁ በሆነችበት የእድሜ ክልልእና በታወቁ ጊዜያት የሚፈስ የደም ዓይነት ነው። በእናቱ ማህፀን ውስጥ ላለው ፅንስ ቀለብ ይሆን ዘንድ አላህ (ሱብሃነሁ ወተዐላ) አስገኝቶታል። ለዚህም ሲባል አብዛኛውን ግዜ ሴቷ ስታረግዝ የወር አበባ ደሙ ይቋረጣል። ከዚህ በመቀጠል ሴቷ ሐይድ ላይ በምትሆንበት ጊዜ ተያይዘው የሚመጡ ህግጋቶች አሉ። ከነዚያም መካከል ፤ ሰላት እና ፆም ክልክል ይሆንባታል። መልክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋልና፦ “አንዲት ሴት የወር አበባ ላይ ስትሆን ስግደትና ፆም ታቆም አይደለምን?!” ስለዚህም አንዲት ሴት ሀይድ ላይ ስትሆን መጾምም ሆነ መስገድ ለርሷ አይፈቀድላትም። ይህን ብታደርግ ወንጀለኛ ትሆናለች። ጾሟም ሆነ ሰላቷ በሷ ላይ ተመላሽ ነው።
ሁለተኛ፤ሐይድ ላይ ሆና በከዕባ ዙርያ ጠዋፍ ማድረግ አይፈቀድላትም። ምክንያቱም የአላህ መልክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) ዓኢሻ ሐይድ በሆነችበት ጊዜ እንዲህ ብለዋታል፦ “ጠዋፍ ማድረግ ሲቀር አንድ ሐጅ ስነስርዓት ላይ ያለ ሰው የሚሰራውን ተግባር በሙሉ ፈጽሚ።” ሠፍያ ቢንቱ ሑየይ ሐይድ ላይ መሆኗ ለመልዕክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሲነገራቸው “እርሷ ናት ከሀጅ እንዳንወጣ ያገተችን?” “እርሷ ጠዋፍ ኢፋዳን አድርጋለች” ብለው ሲነግሯቸው “እንግዲያውስ ከሀረም ክልል ውጡ።” አሏቸው። ከዚህ ሐዲስ የምንረዳው አንዲት ሴት ጠዋፉል ኢፋዳ ካደረገች በኋላ ሐይድ ቢመጣባት የሐጅ ስራዋን እንዳከናወነች ይቆጠርላታል። ሰዕይ ሳታደርግ እንኳ ቢመጣትም። ምክንያቱም ሐይድ ላይ ያለች ሴት በሰፋና መርዋ መሃከል መሮጥ ይበቃላታል።
በተጨማሪም ከሐዲሱ የምንረዳው አንዲት ሴት ሐይድ ከሆነችየመሰናበቻው ጠዋፍ ከርሷ ዋጅብነቱ ይነሳላታል። ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ ግልፅ በሆነ ዘገባ በመጣው መሰረት እንዲህ ብለዋል(ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ ) “የመጨረቸው የሐጅ ተግባር ከዕባን የመሰናበቻ ጠዋፍ ማድረግ ላይ እንዲሆን መልክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) ሰዎችን አዘዋል። ሆኖም ሐይድ ላይ ላለች ሴት ግን ተቀንሶላታል።”
ሐይድ ላያ ያለች ሴት ከባሏ ጋር ግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ አይፈቀድላትም። ባልም እንዲሁ ሚስቱን ሐይድ ሳለች መገናኘት አይፈቀድለትም። ምክንያቱም አላህ (ሱብሃነሁ ወተዐላ) እንዲህ ይላልና፦ “ከወር አበባም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስጠያፊ ነው፡፡ ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፡፡ ንጹሕ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው፡፡” [አልበቀራ: 222]
ሴት ልጅ ሐይድ በሆነችበት ሰዓት መገናኘት ክልክል መሆኑን የተከበረው አንቀፅ ያስረዳል። በጠራችም ሰዓት ሳትታጠብ ሊገናኛት አይገባም። ምክንያቱም “ንጹሕ በኾኑም ጊዜ” የሚለው መልዕክት ትጥበትን ነው የሚጠቁመው። መንጻት ማለት እዚህ ቦታ መታጠብ ነው የሚፈለግበት። ምክንያቱም በሌላ ቦታ ላይ አላህ (ሱብሃነሁ ወተዐላ) እንዲህ ይላልና “ «ጀናባ») ብትኾኑ (ገላችሁን) ታጠቡ፡፡” [አል ማኢዳ:6]
ሆኖም አንድ ባል ሚስቱ ሐይድ ላይ ሳለች ወሲብ ከማድረግ ውጭ ሌላ አካሏን መነካካትና መዳሰሥ ይፈቀድለታል። ይህ ማድረጉ ምናልባት የሐይድ ወቅት በሙሉ ከወሲብ መታገስ ለማይችል ሰው ስሜቱን በተወሰነ ደረጃ ይቀንስለታል። ሀይድ ላይ ሆነችም አልሆነች በየትኛውም ጊዜ ከኋላ በኩል(በፊንጢጣ) መገናኘት ሐራም ነው።
ከሐይድ ጋር ከሚያያዙ ህግጋቶች መካከል አንዲት ሴት በሰላት ወቅት ከሐይዷ ከጠራች ወቅቱ ሳይወጣ ትሰግድ ዘንድ ወድያውኑ በፍጥነት መታጠብ ይኖርባታል። እንበልና ለምሳሌ ፈጅር ላይ ፀሐይ ከመውጣቱ በፊት ብትጠራ፤ ፈጅርን በሰዓት ትሰግድ ዘንድ መታጠብ በርሷ ላይ ግዴታ ይሆንባታል። አንዳንድ ሴቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ሲዘናጉ ትመለከታለህ። በሰላት ወቅት ከሀይዷ ትጠራና በኋላ እታጠባለሁ ብላ ትጥበቱን ታዘገያለች፤ በተለይም በብርድ ወቅት።በኋላ እሰግዳለሁ እያለች ተዘናግታ የሰላቱ ወቅት ያልፍባታል። ይህ ተግባር ሐራም ነው። እንዲያውም መታጠብ በርሷ ላይ ግዴታ ነው።
ለተራ ሰዎች ሳይቀር የሰላት ወቅቶች የታውቁ ናችው ፈጅር ሰላት ጎህ ከቀደደበት ሰዓት አንስቶ ፀሐይ እስኪወጣ ድረስ ሲሆን የዙህር ወቅት ደግሞ ፀሐይ ከአናት ወደ መጥለቂያዋ ዞር ካለችበት አንስቶ የሁሉም ነገር ጥላ እስከ መሰሉ እስኪሆን ድረስ ነው። የዐስር ወቅት ደግሞ ከዚህ ሰዓት አንስቶ ጸሐይ ዳልቻ ወይም ቢጫ እስክትሆን ያለው ወቅት ነው። ይህ የምርጫ ወቅት ሲሆን ፀሐይ እስክትጠልቅ ያለው ሰዓት ደግሞ የደሩራ ሰዓት ነው።የመግሪብ ወቅት ደግሞ ፀሐይ ከጠለቀችበት አንስቶ ቀዩ አድማስ እስኪጠልቅ ያለው ሰዓት ነው። የኢሻ ወቅቱ ደግሞ ቀዩ አድማስ ከጠለቀበት ሰዓት አንስቶ እስከ ግማሽ ለሊት ድረስ ይቆያል። ግማሽ ለሊት ከሆነበት ሰዓት አንስቶ ኢሻ መስገድ አይቻልም ምክንያቱ የኢሻ ወቅት ወጥቷልና። ምናልባት አንድ ሰው ተኝቶ አሊያም ረስቶ ያሳለፈ ከሆነ በዚህ ወቅት መስገድ ይችላል። የአላህ መልክተኛው(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፦ “ሰላት የረሳ ወይንም ሳይሰግድ በእንቅልፍ ያሳለፈ ሲያስታውስ ወይንም ሲነቃ ይስገድ።”
ሌላው የወር አበባን አስመልክቶ ሊታወቅ የሚገባው የሐይድ ወቅት እስከሆነ ድረስ ከሐይድ ደም የሚያወጣው መሰረት እስካልመጣ ደሙ የሐይድ ደም ሁክም ይይዛል። ከዚህ መሰረት ሊያወጣው የሚችለው ደሙ ከማህፀን ግድግዳ የወጣ መሆኑንና ተፈጥራዊ ደም አለመሆኑ ላይ እርግጠኛ ስንሆን ብቻ ነው ደሙ የወር አበባ ደም አይደልም ልንል የምንችለው። ለምሳሌ ሴቷ ቀዶ ጥገና በማድረጓ አሊያም በድንጋጤ የተነሳ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ከተፈጥሯዊ ደም ውጭ እንዲፈስ የሚያደርጉ ሰበቦች ሲከሰት በዚህን ግዜ ደሙ የሐይድ ደም ተብሎ አይቆጠርም። እንደዚሁም ደሙ በብዛት ሳይቋረጥ ከወር በላይ ከፈሰሳት ደሙ የኢስቲሃዳ(የበሽታ) ደም ሁክም ይይዛል። ይህ የበሽታ ደም ከመከሰቱ በፊት ባላት የሐይድ ልምድ መሰረት መለስ ብላ እራሷን በመቃኘት በሱ ትቆጥራለች። የልምድ ግዜዋ ያህል ከኢባዳ ትታቀብና ታጥባ ሰላቷን ትሰግዳለች።ደሙ ቢፈሳትም እንኳ። ከወር አበባና ከወሊድ ደም ጋር ከሚያያዙ ህግጋቶች መካከል፦ አንድ ባል ሚስቱ ሐይድ ላይ ሳለች ፍችን ማከናወን አይፈቀድለትም። ይህን ካደረግ ወንጀለኛ መሆኑን ሊያውቅና ንፁህ እስክትሆን ጠብቆ ሳይገናኛት መፍታት እስኪችል ድረስ ሊመልሳት ይገባል። በቡኻሪና ሙስሊም በተዘገበው ሐዲስ ላይ ዐብዱላሂ ኢብኑ ዑመር ባለቤቱን ሐይድ ሳለች ፈቷት ነበር፤ይህን ጉዳይ ዑመር ለመልክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሲነግራቸው ፦ “ይመልሳት ዘንድ እዘዘው፤ከዚያም ከወር አበባ ንፁህ ሳለች አሊያም ፀንጻ ይፍታት።” አሉት።
አላህ እኛንም ይሁን እነሱን ይምራንና በዚህ ጉዳይ ላይ ሲቻኮሉ እናስተውላለን። ሚስቱ ሐይድ ላይ ሳለች ወይም ከጠራች በኋላ ተገናኝቷት ፅንስ ይኑር አይኑር ሳያረጋግጥ ይፈታታል። ይህ ተግባር ሐራምመሆ ኑን በማወቅ ማንኛውም ሰው ከዚህ ተግባር ተውበት ማድረግ ይጠበቅበታል።በዚህ መልኩ የፈታትን ሴት ሊመልሳትም ይገባል።
የወር አበባና የወሊድ ደም ጋር ከሚያያዙ ህግጋቶች መካከል፦ አንዲት የወሊድ ደም ያለች ሴት ከአርባ ቀን በፊት ከደሟ ከጠራች ታጥባ ሰላቷንና ጾሟን(ረመዳን ከሆነ) መቀጠል ይጠበቅባታል። በአርባ ቀን ውስጥ ከደሙ ንፁ ህ ከሆነች የጠሃራ ፍርድን ትይዛለችና።ግብረስጋ ግንኝነትን እንኳ አስመልክቶ አርባ ቀን ባይሞላትም ንጽሁ ከሆነች ባሏ እርሷን መገናኘት ይፈቀድለታል። ምክንያቱም ሰላት መስገድ ይፈቀድላታል ካልን ከባሏ መገናኘቷ ደግሞ በይበልጥ ይቻላል እንላለን።
ከወር አበባና ከወሊድ ደም ጋር ከሚያያዙ ህግጋቶች መካከል፦ ከላይ እንዳሳለፍነው የወሊድም ይሁን የወር አበባ ደም ላይ ያለች ሴት ደሙ ሲቋረጥ መታጠብ ይኖርባታል። የወር አበባና የወሊድ ደም ህግጋቶች እጅግ ብዙ ናቸው። እዚሁ ላይ እንገድበዋለን ይህን ያህል ካልንም በቂ ነው።