Back to Top
ጠሃራ ላይ ያለ ጥርጣሬ ሲባል ምን ለማለት ነው?

ጥያቄ(79): ጠሃራ ላይ ያለ ጥርጣሬ ሲባል ምን ለማለት ነው?
መልስ:

ጠሃራን አስመልክቶ ጥርጣሬው ለሁለት ይከፈላል።

አንደኛው፡ ውዱእ ካጠፉ በኋላ ጠሃራ አለኝ ወይስ የለኝም ብሎ መጠራጠር።

ሁለተኛው፡ ውዱእ መኖሩ ላይ እርግጠኛ ከሆኑ በኋላ ውዱእ አለኝ ብሎ መጠራጠር።

የመጀመሪያው ማለትም ውዱእ ካጠፉ በኋላ ጠሃራ አለኝ ወይስ የለኝም ብሎ መጠራጠር፤በዚህን ግዜ ማድረግ የሚጠበቅበት መጀመሪያ ላይ በነበርክበት ሁኔታ ላይ መሰረትህን ገንባ እንለዋለን።እርሱም ውዱእ የለህምና ውዱእ ማድረግ ይኖርብሃል እንለዋለን።

ምሳሌ፦ አንድ ሰው አዱሃ ሰላት ከሰገደ በኋላ ውዱእ አጥፍቶ ነበር፤ ለዙህር አዛን ሲል  ውዱእ አለኝ ወይስ የለኝም ብሎ ተጠራጠረ፤ማለትም ለምሳሌ አራት ሰዓት ሲሆን ውዱእን አጥፍቶ ዙህር አዛን ሲባል ውዱእ አድርጌያለሁ ወይስ አላደረግኩም ብሎ ተጠራጠረ።በዚህን ግዜ መጀመሪያ ላይ በነበርክበት እርሱም ውዱእ አለነበረክምና በሱ ላይ እርግጠኝነትን መስርተህ ውዱእ ማድረግ ይጠበቅብሃል እንለዋለን።

ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ ውዱእ ነበረው ውዱእ ጠፍቷል ወይስ አልጠፋም ብሎ ተጠራጠረ፤ በዚህ ግዜ መጀመሪያ ላይ በነበርክበት እርሱም ውዱእ ነበረክና በሱ ላይ እርግጠኝነትን መስርተህ ውዱእ ማድረግ አይጠበቅብህ እንለዋለን።

ምሳሌ፦ አንድ ሰው ከቀኑ አራት ሰዓት ላይ ውዱእ አደረገ፤የዙህር ሰላት ወቅት ሲደርስ ውዱ አጥፍቻለሁን ወይስ አላጠፋሁም ብሎ ቢጠራጠር፤ውዱእ ላይ ነህና ዳግም ውዱእ ማድረግ አይጠብቅምህ እንለዋለን። ምክንያቱም አንድ ነገር የሚቀይረው ነገር ካልመጣ መሰረቱ ባለበት ሳይቀየር መቆየቱ ነው። ለዚህም መርሆ  ማስረጃችን የመልዕክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) ንግግር ነው። ከሰውነቱ ንፋስ(ፈስ) የወጣ የሚመስለው ሰውዬን አስመልክቶ ፦ “ የፈስ ሽታ ወይም ድምፁ ካልሰማ ከመስጂድ ወይም ከሰላት አይውጣ።” ብለዋል።

ተግባር ላይ ቢጠራጠር ወይንም ከሰውነት አንዱን ክፍል አጥቤያለሁ ወይስ አላጠብኩም ብሎ  ከተጠራጠረ፤ ምሳሌ ውዱእ እያደረገ ሳለ ፊቴን አጥቤያለሁን ወይስ አላጠብኩም ብሎ  ከተጠራጠረ፣ ወይንም እጄን አጥቤያለሁን ወይስ አላጠብኩም ብሎ  ከተጠራጠረ። ይህን ሰው አስመልክቶ ከአራት ሁኔታዎች የወጣ አይደለም።

አንደኛው ሁኔታ፤ ልቡ ላይ መሰረት የሌለው ዝም ብሎ ጥርጣሬ ሊከሰትበት ይችል ይሆናል።እጄን አጥቤያለሁን ወይስ አላጠብኩም ብሎ  ሲጠራጠር ይህን ጥርጣሬ ሚዛን የሚደፋለት ነገር ላይኖረው ይችላል፤ ወይንም ሁለቱንም ማለትም አጥቤያለሁ ወይንስ አላጠብኩም የሚለው ጥርጣሬ እኩል ላይሆን ይችል ይሆናል። ዝም ብሎ ያለ ምንም ምክንያት ዝም ብሎ ጥርጣሬው ልቡ ላይ ሊከሰት ይችላል።በዚህን ግዜ ለጥርጣሬው ቦታ ወይም ግምት ሊሰጠው አይገባም።

ሁለተኛው ሁኔታው ደግሞ፦ ግለሰቡ በባህሪው ሲበዛ ተጠራጣሪ ሊሆን ይችል ይሆናል። ውዱእ ባደረገ ቁጥር ይጠራጠራል። ለምሳሌ እግሩን እያጠበ ሳለ ራሴን አብሻለሁ ወይስ አላበስኩም ብሎ ሊጠራጠር ይችላል። ጆሮቼን አብሻለሁ ወይንስ አላበስኩም ብሎ ይጠራጠር ይሆናል። ብቻ በጣም ሲበዛ ተጠራጣሪ ነው። ይህም ሰው እንዳለፈው ሰው ለጥርጣሬህ ቦታ ወይም ግምት አትስጥ እንለዋለን።

ሦስተኛው ሁኔታ፤ ውዱእን ካጠናቀቀ በኋላ ጥርጣሬ ቢያድርበት ለምሳሌ እጁን ይጠብ ወይም አይጠብ፣ራሱን ያብስ ወይም አያብስ፣ጆሮውን ያብስ ወይንም አያብስ የሚለው ላይ ሊጠራጠር ይችል ይሆናል። ይህንም ግለሰብ እንዳለፈው ሰው ለጥርጣሬህ ቦታ ወይም ግምት አትስጥ እንለዋለን።

እነዚህ ሦስት ሁኔታዎች ለጥርጣሬ ቦታና ግምት የማይሰጥባቸው ሁኔታዎች ናቸው። እነሱም አንደኛው መሰረት የሌለው ጥርጣሬ ሁለተኛው፤በጣም ሲበዛ ተጠራጣሪ መሆን። ሦስተኛው ደግሞ፤ውዱእን ካጠናቀቀ በኋላ ጥርጣሬ መከሰት ናቸው።

አራተኛው ሁኔታ፤ጥርጣሬው የእውነት ጥርጣሬ መሆን ነው። በባህሪው ሲበዛ ተጠራጣሪ መሆን ሳይሆን እና ውዱእን ከማጠናቀቁ በፊት ጥርጣሬው ሲከሰት፤ በዚህን ግዜ በእርግጠኝነት ላይ ሊመሰርት ይገባል ማለትም ውዱእ ላይ ያን አካል እንዳላጠበ ይቆጠራል።ስለሆነም ያን የረሳውን ክፍልን እና ቀጥሎ  ያሉትን የሰውነት አካሎች ማጠብ ይኖርበታል። ምሳሌ፦ ራሱን እያበሰ ባለበት ሰዓት መጉመጥመጡ ወይም በአፍንጫው ውሃ አስገብቶ ማስወጣቱ ላይ እርግጠኛ ባይሆን እና በባህሪው ሲበዛ ተጠራጣሪ ሳይሆን እውነተኛ ጥርጣሬ ቢከሰትበት በዚህ ግዜ ተጉመጥመጥ በአፍንጫህም ውሃ በማስገባት አስወጣ፣እጅህንም እስከ ክርን እጠብ ከዚያም ራስህን አብስ እንለዋለን።እጁን ቢያጥበውም ዳግም እንዲያጥብ ግዴታ ያደረግንበት ምክንያት ቅደም ተከተል መጠበቅ ስላለበት ነው። ምክንያቱም ውዱእ በሚደረግበት ግዜ  የሰውነት ክፍሎች ሲታጠቡ አላህ (ሱብሃነሁ ወተዐላ)  በቁርኣኑ ውስጥ በቅደም ተከተል በጠቀሰው መሰረት ቅደም ተከተልን መጠበቅ ግዴታ ነው። መልክተኛውም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ወደ ሰፋ ኮረብታ ለመሮጥ ፊታቸውን  ሲያዞሩ ፦ “አላህ በጀመረው ጀምሩ።” ብለዋል። ከጠሃራ ጋር ተያይዞ ጥርጣሬ ፍርዱ ይህን ይመስላል።




Share

ወቅታዊ