Back to Top
ለሟች ሩሕ ተብሎ ቁርኣን መቅራት ሸሪኣዊ ብይኑ ምንድን ነው?

ጥያቄ(62): ለሟች ሩሕ ተብሎ ቁርኣን መቅራት ሸሪኣዊ ብይኑ ምንድን ነው?
መልስ:

ለሟች ሩሕ ቁርኣን መቅራት ማለትም አንድ ቁርኣን የሚቀራ ሰው ከሙስሊሞች ሟች መካከል አንዱን አስቦ መልካም ምንዳ እንዲደርሰው መቅራት ሲሆን ይህን ርዕስ አስመልክቶ ዑለማዎች የተለያየ አቋም አላቸው። ከእነሱም መካከል አይቻልም የሚል አቋም ያላቸው አሉ።በዚህ መልኩ ለሟች ቁርኣን መቅራት ሟችን አይጠቅምም ይላሉ።ሌሎቹ ደግሞ በዚህ መልኩ መቅራት ለሟች ይጠቅመዋል የሚል አቋም አላቸው። አንድ ሰው ከሙስሊሞች ሟች መካከል ቅርብ ዘመድም ይሁን ሩቅ ዘመድ እገሌን ወይም እገሊትን በማሰብ ሰዋቡ(መልካም ምንዳ) እንዲደርሰላቸው አቅዶ መቅራት ይቻላል ይላሉ። ይህ ከሁለቱ አቋሞች  መካከል ሚዛን የሚደፋው አቋም ይኸኛው ነው። ምክንያቱም መሰል የሆኑ የዒባዳ አይነቶች ለሟች ሩሕ መልካም ምንዳ እንዲደርስ ብሎ መስራት እንደሚቻል የሚጠቁሙ ሐዲሶች አሉና። ሰዕድ ኢብኑ ዑባዳ ረዲየላሁ ዐንሁ ለሟች እናቱ የአትክልት ስፍራ ሰደቃ እንዳወጣ የሚጠቁም ሐዲስ፣እንዲሁም ያ ሰውዬ ለመልዕክተኛው እናቱ ነፍሷ አምልጣት ሳትናገር ሞተች፤መናገር ብትችል ሰደቃ ታወጣ ነበርና እኔ ለርሷ ሰደቃ ላውጣላትን? ብሎ ሲጠይቃቸው እሳቸው”አዎን” በማለት መለሱለት።

እነዚህ ጉዳዮችና ክስተቶች ዒባዳን ሙስሊም ለሆኑ ሟቾች ምንዳውን አሳልፎ መስጠት እንደሚቻል ይጠቁማሉ።ቁርኣን መቅራትም እንዲሁ ከኢባዳዎች የሚመደብ ነው። ሆኖም ይህን ከማድረግ ለሟች ዱዓ ፣መልካም ተግባሮችን ደግሞ ለራስ ማድረግ  ይበልጥ የሚሻል ተግባር ነው። ምክንያቱም የአላህ መልክተኛ እንዲህ ብለዋልና«የአደም ልጅ (አንድ ሰው) ሲሞት ከሶስት ነገሮች በስተቀር መልካም ስራው ሁሉ ይቋረጣል፤ ቀጣይ የሆነ ሰደቃ፣ ጠቃሚ ዕዉቀት እና ለእርሱ ዱዓ የሚያደርግለት ሷሊህ (መልካም) ልጅ።» ቁርኣን የሚቀራለት መልካም ልጅ፣ ሰላት የሚሰግድለት መልካም ልጅ፣ ጾም የሚፆምለት መልካም ልጅ፣ ሰደቃ የሚያወጣለት መልካም ልጅ ወዘተ አላሉም። እንዲያውም ” ዱዓ የሚያደርግለት ሷሊህ (መልካም) ልጅ።» ነው ያሉት። የሐዲሱ አመጣጥ ተግባርን አስመልክቶ  ነውና ስለዚህም በላጩ ተግባር መልካም ስራን ለሟች ማድረግ ሳይሆን ዱዓ ማድረግ ነው የሚገባው። የሰው ልጅ የመልካም ስራው መልካም ምንዳ ጌታው ዘንድ ተከማችቶ መቀመጥ ለርሱ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ሟች ከሞተ በኋላ አንዳንድ ሰዎች ቁርኣን የሚቀራን ሰው በገንዘብ ተከራይተው ለሟች ቁርኣን እንዲቀራማድረግ ይህ ተግባር ቢድዓ  ነው። በዚህ መልኩ ለሟች ቢቀራለትም መልካም ምንዳው አይደርሰውም። ምክንያቱም ይህ ቁርኣን አንባቢ ቁርኣን  የሚያነበው ለአላህ ብሎ  ሳይሆን ለዱንያ ጥቅም ብሎ ነው።ለዱንያ ጥቅም ብሎ አንድ መልካም ስራ የሰራ በአኼራ ምንም የምንዳ ድርሻ የለውም። አላህ በቁርኣኑ እንዳለው ፦

“ ቅርቢቱን ሕይወትና ጌጧን የሚሹ የሆኑትን ሰዎች ሥራዎቻቸውን (ምንዳዋን) በእርሷ ውስጥ ወደነሱ እንሞላላቸዋለን፡፡ እነሱም በርሷ ውስጥ ምንም አይጎድልባቸውም፤ እነዚያ እነርሱ በመጨረሻይቱ ዓለም ለእነርሱ ከእሳት በቀር የሌላቸው ናቸው፡፡ የሠሩትም ሥራ በርሷ ውስጥ ተበላሸ፡፡ (በቅርቢቱ ዓለም) ይሠሩት የነበሩትም በጎ ሥራ ብልሹ ነው፡፡” [አልሑድ 15 _16]

በዚህ አጋጣሚ ይህን ተግባር ያስለመዱ ወንድሞቼን ምክር መለገስ እሻለሁ። ገንዘቦቻቸውን ለራሳቸውም ሆነ ለወራሾች ጠብቀው ማቆየት ይኖርባቸዋል።ይህ ተግባር በራሱ ቢድዓ መሆኑ ሊያውቁ ይገባል። ሟች ሰዋብ (መልካም ምንዳ) አይደርሰውም። ምክንያቱም? ዱንያ ጥቅምን ፈልጎ የሚቀራ ሰው አላህ ዘንድ ምንም ምንዳ የለውም።በዚህን ጊዜ ቁርኣን አንባቢው ገንዘቡን ወሰደ ሟች ግን በቂርኣቱ ተጠቃሚ አይሆንም።




Share

ወቅታዊ