ጥያቄ(61): ጉልህ የሆኑ ቁርኣን ንበብ ደንቦችና ስርኣቶች ምንድን ናቸው?
መልስ:
ቁርኣንን የሚያነብ ሰው ከትልቁ(ጀናባ)እና ከትንሹ(ውዱን የሚያበላሹ) ሐደስ ጠሃራ ሊሆን ይገባል።ጀናባ ላይ ሆኖ አንድ ሰው ቁርኣንን ማንበብ አይፈቀድለትም።በሐዲስ ላይ እንደመጣው ጁኑብ ላይ የሆነ ሰው እስኪታጠብ ቁርኣንን ማንበብ ይከለከላል። የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ቁርኣንን ማንበብ ትችላለችን? የሚለውን ርእስ አስመልክቶ የእውቀት ባለቤቶች የተለያየ አቋም አላቸው።
ሁለት የተለያየ አቋም ያሏቸው ሲሆን ከእነሱም መካከል ቁርኣን መቅራት ትችላለች ያሉ አሉ። ምክንያቱም ቁርኣን መቅራቷን የሚከለክል ግልፅ የሆነ የሐዲስ ማስረጃ የለምና። በሸሪዓችን ደግሞ አንድ ሰው ከጅማሬው ጫንቃው ከግዴታ የጠራ ነው፤አለማስገደድ፤ ከእንደገናም ባንድ ነገር ላይ አለመከልከል ነው መሰረቱ።አንዳንድ ዑለማዎች ደግሞ ሐይድ ላይ ሆኗ ቁርኣንን መቅራት አትችልም የሚል አመለካከት አላቸው። ምክንያቱም እንደ ጀናባ ትጥበት ይኖርበታል። እንዲሁም ሐይድ ላይ ያለችን ሴት ቁርኣንን መቅራት የሚከለክሉ ከመልዕክተኛው(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) ሐዲስ ተዘግበዋል።እኔ በዚህ ላይ ያለኝ አቋም መቅራት ብቻ ከሆነ አላማዋ ባትቀራ ይሻላል ባይ ነኝ።ነገር ግን ቁርኣን ካልቀራሁ እረሰዋለሁ የሚል ስጋት ካላት አሊያም አስተማሪ በመሆኗ ቁርኣን ተማሪዎቿና ልጆቿን ለማስቀራት፣ወይም ተማሪ በመሆኗ ቁርኣን ማሰማት ካለባት እና ለመሳሰሉት ጉዳዮች መቅራቷ ችግር የለውም። በተጨማሪም እለታዊ አዝካር ውስጥ ለምሳሌ አያቱል ኩርሲይ ብትቀራ ችግር የለውም። ይህ አቋም ለሐቅ የቀረበ ነው የሚል እምነት አለኝ። በጥቅሉ ሐይድ ላይ ያለችን ሴት አስመልክቶ ቁርኣን መቅራቷ ወሳኝ ከሆነ መቅራት ይፈቀድላታል።ሆኖም መቅራቷ ወሳኝና አስፈላጊ ካልሆነ መቅራት የለባትም።
እንደዚሁም አንድ ቁርኣን የሚቀራ ሰው ቁርኣንን በሚያነብበት ጊዜ የሚያነበውን የቁርኣን የላቀ መልዕክት ይረዳ ዘንድ ልቡን ጥዶ ማንበብ ይጠበቅበታል። አንቀፆቹ በውስጣቸው የያዙዋቸውን መልዕክቶች ታሪክ፣ዜና እና ህግጋትን ሁሉንም በእኩል ማስተንተን ይኖርበታል። ምክንያቱም ቁርኣን የወረደው ለዚህ ጥበብ ነውና።
የሰው ልጅ ልቡ ዝንጉ ሆኖና ልቡ ተጥዶ (እያስተነተነ) ቁርኣንን ሲያነብ በሁለቱ መሃል ከፍተኛ ልዩነት ያስተውላል።ቁርኣንን በማስተንተንና በማስተዋል ሲቀራ ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል። በዚህ መልኩ ቁርኣን ማንበብ ልቡ ውስጥ ጠንካራ ኢማን እና እርግጠኝነት፣የአላህ መፅሐፍ በውስጡ የሚያካትታቸውን ህግጋቶች መፈፀምና መታዘዝ ላይ ጠንካራ ተፅእኖ ያሳድራል።
ቁርኣን ሲነበብ ሊጠበቁ ከሚገቡ ስርኣቶች መካከል፦ ሲነበብ በርጋታ ሊሆን ይገባል፣አንዳንድ ፊደላት እስኪሳቱ ወይም ቃላቶች እስኪሰወሩ ድረስ በፍጥነት መቀራት አይኖርበትም። እንዲያውም በዝግታና በእርጋታ መቀራት አለበት ነገርግን ፊደላት ሳይጣሉ፣ኢድጋም መደረግ የሌለበትን ኢድጋም ሳይደረጉ እና የመሳሰሉት ህግጋት ሳይጣሱ አንዳንዴ መፍጠን ችግር የለውም።