Back to Top
ከነዚህ ማለትም ከጠቀሷቸው አራት የተወሱል አይነት ውጭ ሌላ የተወሱል አይነት ይኖራልን?
   ዐቂዳ (እምነት ነክ ጉዳዮች)        ምልጃ

አምስተኛው የተወሱል ዓይነት


ጥያቄ(57): ከነዚህ ማለትም ከጠቀሷቸው አራት የተወሱል አይነት ውጭ ሌላ የተወሱል አይነት ይኖራልን?
መልስ:

አዎን። ከላይከጠቀስናቸው አራት የተወሱል ዓይነቶች ሌላ ተጨማሪ የተወሱል ዓይነት አለ። እርሱም፦ ዱዓው ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ የሚከጀል ሰው ዱዓ ካደረገ በኋላ በሱ ዱዓ ወደ አላህ ተወሱል ማድረግ ነው። የነቢዩ  ባልደረባዎች ለህዝባቸውም ሆነ ለግላቸው መልክተኛው ዱዓ እንዲያደርጉላቸው ይጠይቋቸው ነበር።

ቡኻሪና ሙስሊም ከአነስ ኢብኑ ማሊክ እንደዘገቡት “አንድሰ ሰው በጁምዓ ዕለት ነቢዩ ኹጥባ እያደረጉ ባሉበት ሰዓት ከፊት ለፊታቸው በኩል ባለው በር ገብቶ በመቆም እንዲህ አላቸው፦

“አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከብቶች አለቁ መንገዱም ተቋረጠ ጌታችን ዝናብ በማዝነብ ከጭንቅ እንዲያወጣን ለምኑልን? ነቢዩም እጃቸውን ከፍ አድርገው “ጌታችን ሆይ! አዝንብልን ጌታችን ሆይ! አዝንብልን ጌታችን ሆይ! አዝንብልን በማለት ተማፀኑ። ”ሰማይ ላይ ጉም አልነበረም። መልዕክተኛው ከሚንበራቸው ሳይወርዱ ዝናብ ዘንቦ በፂማቸው መካከል ተንጠባጠበ።  ለሳምንት ያህልም ሳያቋርጥ ዘነበ። በሳምንቱ ጁምዓ አንድ ሰው በዚያው በር በመግባት ፊት ለፊታቸው በመቆም ቤቶች ፈረሱ ንብረታችን በጎርፍ ተጥለቀለቀ። አላህ ዝናቡን እንዲይዝልን ለምኑልን።” አላቸው መልዕክተኛውም እጃቸውን ከፍ አድርገው “ጌታችን ሆይ!  እኛ ላይ ሳይሆን በዙሪያችን ባሉ ቦታዎች ላይ አድርገው። ብለው እጃቸው የጠቆሙበት ቦታ ላይ በአላህ ፍቃድ ደመናው ተገለጠ። ሰዎች እየተራመዱ በፀሐይ ወጥተው ሄዱ።

ሰሓቦቹ ለግላቸው ነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም )  ዱዓ እንዲያደርጉላቸው እንደጠየቁ የሚያሳዩ በርካታ ክስተቶች ይገኛሉ። ከነዚህም ክስተቶች መካከል የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) ከኡመታቸው መካከል ሰባ ሺ ሰዎች ያለምንም ቅጣት ጀነት እንደሚገቡ ተናግረው ነበር እነሱም ሩቃ እንዲደርግላቸው የማይጠይቁ፣ጣጣቴ የማይጠቀሙ፣በገድ የማያምኑ እና በጌታቸው የሚመኩ ናቸው ብለው ሲናገሩ ዑካሻህ እብኑ ሚሕሰን “አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ከነሱ እንዲያደርገኝ ዱዓ አድርጉልኝ፤አለ። እርሳቸውም ፦ “አንተ ከነሱ ነህ። አሉት”

 

ይህም ከሚፈቀዱ የተወሱል ዓይነቶች የሚመደብ ነው። ይኸውም አንድ ሰው ዱዓው ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ  የሚከጀልን  ግለሰብ ዱዓ እንዲያደርገለት መጠየቅ ነው። ሆኖም ዱዓ እንዲደርግለት የሚጠይቀው ሰው እራሱን ብቻ በማሰብ ዱዓ መጠየቅ የለበትም ይልቁንም እርሱንም ሆነ ዱዓ አድራጊውን እንዲጠቅም በማሰብ ጥያቄውን ማቅረብ ይኖርበታል። ምክንያቱም እረስህንም ሆነ ወንድምህን መጥቀም የምትሻ ከሆነ ይህ ተግባርህ ከመልካም ተግባር ይቆጠራል።ስለዚህም ወንድሙም ወንድሙ በሌለበት እሱን አስቦ ዱዓ ካደረገ መላኢካው፦ “ ላንተም ለወንድም ባደረግከው ልክ ይሁንልህ።” ብሎ ዱዓ ያደርግለታል። በዚህም ተግባሩ ከመልካም ሰሪዎች ይመደባል። አላህ ደግሞ መልካም ሰሪዎች (አሳማሪዎችን) ይወዳል።


 
Share

ወቅታዊ