Back to Top
የፊርቀቱ ናጂያ መገለጫ ባህሪያቸውን አስመልክቶ የሚጨምሩት ማብራሪያ ይኖራችኋልን?

ጥያቄ(55): የፊርቀቱ ናጂያ መገለጫ ባህሪያቸውን አስመልክቶ የሚጨምሩት ማብራሪያ ይኖራችኋልን?
መልስ:

በሐቂቃው ከሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ አይኖረኝም።ምክንያቱ ከላይ የጠቀስናቸው አራት መሰረታዊ መርሆች በቂና ግልፅ ናቸው። ነገር ግን አኽላቅን አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያን ማከል እፈልጋለሁ። እርሱም አኽላቅን ተግባር ላይ ስናውል ከምናገኘው መልካም ውጤት መካከል አላህ በሐቅ ላይ እንድንሰባሰብ አደራ ባለን መሰረት የሙስሊሞች አንድነት ይጠበቃል። አላህ እንዲህ ይላል፦

“ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፡፡ ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)፡፡” [አሹራ፡13]

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሃይማኖታቸውን በመለያየት የተለያዩ አንጃ የሆኑትን በማስመልከት መልክተኛው ሙሐመድ (صلى الله عليه وسلم ) ከነርሱ እንዳልሆኑ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦

“እነዚያ ሃይማኖታቸውን የለያዩ አሕዛብም የኾኑ በምንም ከእነሱ አይደለህም፡፡ ነገራቸው ወደ አላህ ብቻ ነው፡፡ ከዚያም ይሠሩት የነበሩትን ሁሉ ይነገራቸዋል፡፡” [አልአንዐም:159]

በልቦች መካከል መቀራረብና በአንድነት መሰባሰብ ፊርቀቱ ናጂያ የሆኑት አህሉ ሱና የሚገለፁባቸው ዋነኛ መገለጫቸው ነው።  ከኢጅቲሃድ የተነሳ በመካከላቸው ልዩነት ቢፈጠር አንዱ ሌላው ላይ ጠብ፣ጥላቻና ቂም አይዝም።እንዲያውም እነዚህ ቅርንጫፋዊ ልዩነት በመካከላቸው ቢኖርም ወንድማማቾች መሆናቸውን ያምናሉ። ቅርንጫፋዊ ልዩነት ላይ ከመቻቻላቸው የተነሳ በርሱ አቋም መሰረት ውዱእ የለውም ወይም አፍርሷል ብሎ የሚያምንበት የሆነን ግለሰብ ከኋላው ተከትሎ እስከመስገድ ሊደርስ ይችላል። ለምሳሌ አንድ ኢማም(አሰጋጅ) በርሱ አቋም የግመል ስጋ መብላት ውዱን አያበላሽም የሚል እምነት(አቋም) ስላለው የግመል ስጋ በልቶ ውዱእ ሳያደርግ ቢያሰግድ ከኋላው ተከትሎ የሚሰግደው ሰው ደግሞ የግመል ስጋ መብላት ውዱ ያበላሻል የሚል እምነት ቢኖረውም ወይም እርሱ የግመል ስጋ በልቶ ቢሰግድ ሰላቱ ትክክል እንዳልሆነ ቢያምንም እንኳ ከዚህ ሰው ኋላ ተከትሎ የሚሰግደው ሰላት ግን ትክክል መሆኑን ያምናል።

እዚህ ደረጃ ሊደረስ የቻለበት ምክንያት በሙስሊም መካከል ኢጅቲሃድን የሚያስተናግዱ ልዩነቶች እንደ ልዩነት አይቆጠሩም ከሚለው እምነት የተነሳ ነው። ምክንያቱም ሁለቱም ሐቅ ላይ ለመድረስ ሊዛነፉበት የማይገባ ማስረጃ ተከትለዋል። ስለዚህም መረጃን ይዞ ቢቃረናቸውም ወንድማቸው ሌላ የሚከተለው አሳማኝ መረጃ እንዳለው ስለሚያምን በሐቁ ከሆነ እነሱን እንደተቃረናቸው ሳይሆን ከእነሱ ጋር እንደተስማማ ይቆጥሩታል። ምክንያቱም የትም ጋ ቢሆን ማስረጃን መከተል እንደሚገባ ጥሪ ያደርጋሉና። እርሱ ዘንድ አሳማኝ ማስረጃን ለመግጠም ሲል እነሱን ቢቃረንም በሐቂቃው ግን እነሱ ጥሪ ወደሚያደርጉበት ነገር ላይ በመጓዙ የተነሳ ከእነሱ ጋር በዓላማ ተስማምቷል። ምክንያቱም የሁለቱም ዓላማ ቁርኣንና ሐዲስን ማስረጃ በማድረግ ወደነሱ መፋረድ ነው።

ይህን አይነት ኺላፍ በሰሓቦች መካከል እንደተፈጠረ ከብዙ ዑለማዎች የሚሰወር አይደለም። በነቢዩ ዘመን እንኳ ይህ አይነቱ ኺላፍ ላይ ሰሓቦቻቸው ቢወድቁም አላወገዟቸውም። መልክተኛው ከአሐዛብ ዘመቻ ሲመለሱ የአላህ መልክተኛን ቃል ኪዳን ያፈረሱ በኒ ቁረይዛዎችን ሄደው እንዲፋለሙ ጂብሪል መጥቶ ጥቆማ ሲሰጣቸው ባልደረቦቻቸውን ጠርተው እንዲህ አሏቸው፦ “በኒ ቁረይዛ መንደር ደርሶ ቢሆን እንጂ ከእናንተ አንዳችሁም ዐስር ሰላትን እንዳይሰግድ።” ወዲያውኑ መዲናን ለቀው ወደ በኒ ቁረይዛ አቀኑ፤ መንገዳቸው ላይ ሳሉ የዐስር ሰላት ደረሰባቸው፤ከእነሱም መካከል በኒ ቁረይዛ እስኪደርሱ ወቅቱ እስኪወጣ ዐስር ሰላትን ሳይሰግዱ ለኋላ ያዘገዩ ነበሩ። ምክንያቱም የአላህ መልክተኛው (ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) “በኒ ቁረይዛ መንደር ደርሶ ቢሆን እንጂ ከእናንተ አንዳችሁም ዐስር ሰላትን እንዳይሰግድ።” ስላሉሏቸው መግሪብ ከደረሰ በኋላ እንጂ አልሰገዱም ነበር። ሌሎቹ ደግሞ መልዕክተኛው ይህን ያሉት በኒ ቁረይዛ ቶሎ ለመድረስ ፈጥነን እንድንደርስ ፈልገው እንጂ ሰላቱ ከወቅቱ እንድናሳልፈው ፈልገው አይደለም በማለት ዐስር ሰላት ወቅቱ ላይ የሰገዱ ነበሩ። በኢጅትሃዳቸው እውነታ ላይ የደረሱት እነዚህኞቹ ነበሩ። ሆኖም ከሁለቱ ቡድኖች አንዳቸውንም ኢጅትሃዳቸውን አላጣጣሉባቸውም።እንዲሁም ይህን የመልክተኛውን (صلى الله عليه وسلم ) መልዕክት አስመልክቶ በመካከላቸው የግንዛቤ ልዩነት ቢፈጠርም አንዳቸው በሌላው ላይ ጠብና ጥላቻ በልቡ አልተሸከመም።

ስለዚህም እራሳቸውን ወደ አሕሉሱና የሚያስጠጉ ሙስሊሞች በሙሉ ልዩነትን አስወግደው አንድ ህዝብ የመሆን ግዴታ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። በመሀከላቸው አንዱ ወደ እገሌ የሚባል አንጃ ሌላኛው ደግሞ ሌላ አንጃ ሦስተኛው ደግሞ ሌላ ቡድን እየተከተለ ቡድንተኝነት ሊያራምዱ አይገባም። በምላስ ቀስት እየተወራወሩ ሊጨፋጨፉ፣ኢጅቲሃድን ሊያስተናግድ በሚችል ልዩነት የተነሳ ጠብ ሊፈጥሩና ሊጠላሉ አይገባም። የግዴታ እገሌ የሚባለው ቡድን ብዬ መጥራት አይጠበቅብኝም።ምን ማለት እንደፈልግኩ ግልፅ ነውና። አህሉሱናዎች በመሃከላቸው ማስረጃዎችን እንደ አቅማቸው በመገንዘብ የተነሳ ልዩነት ቢፈጠርም እንኳ አንድነት መፍጠር ግዴታ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህ የኺላፍ ጉዳይ ለአላህ ምስጋና ይገባውና ሁላችንም የሚያቻችል ሰፊ አጀንዳ ነው። አሳሳቢው ነገር የልቦች መቀራረብ እና የቃላቸው መጋጠም ነው ። ሙስሊሞች ሲለያዩና ሲበታተኑ ጥላቻቸውን በይፋ ያወጁ አሊያም ሙስሊምን ወዳጅ መስለው ጠላት የሆኑ የኢስላም ጠላቶች ይህ መከሰቱ እንደሚያስደስታቸው ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ መሆን እና አለመበታተን ፊርቀቱ ናጂያ አህሉ ሱና ተለይተው የሚታወቁበት መገለጫቸው ነውና በዚህ መገለጫ እኛም ተለይተን ልንታወቅ ይገባል።
Share

ወቅታዊ