ጥያቄ(34): በሸሪዓው ከዋክብት መቁጠር ያለው ብይን ምን እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።
መልስ:
ኮከብ ቆጠራ ማለት፤ በከዋክብት ሁኔታ ምድር ላይ የሚከሰተውን ነገር መተንበይ ማለት ነው። ማለትም ኮከብ ቆጣሪ ምድር ላይ የሚከሰተውን ነገር ወይም ወደፊት ምድር ላይ የሚከሰተውን ከከዋክብት ጋር በማያያዝ መተንበይ።
የከዋክብትን እንቅስቃሴ፤በመውጫቸውና በመጥለቂያቸው በጥምረታቸውና በመለያየታቸው እና የመሳሰሉትን ክስተቶች በማየት መተንበይ ኮከብ ቆጠራ ይባላል። ኮከብ ቆጠራ ድግምት ውስጥ የሚካተት ሲሆን ድርጊቱም ሐራም ነው። ምክንያቱም መሰረተ ቢስ እና ምንም አይነት እውነታ በሌለው ነገር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ። ሰማይ ላይ የሚከሰተው ነገር ከምድር ጋር ምንም ተያያዥነት የለውም። ለዚህም ሲባል በጃሂሊያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ፀሐይም ሆነ ጨረቃ የሚጋረዱት ታላቅ ሰው ስለሚወለድ ወይም ስለሚሞት ነው ብለው ያምኑ ነበር። እናም በነቢዩ ዘመን ልጃቸው ኢብራሂም በሞተበት ቀን ላይ ፀሐይ ተጋርዳ ነበር። ሰዎች ዛሬ ፀሐይዋ የተጋረደችው ኢብራሂም ስለሞተ ነው አሉ።
ነቢዩ (ሰለለሁ አለይሂ ወሰለም) ሰላተል ኹሱፍ ካሰገዱ በኋላ ቀጣዩን ኹጥባ አደረጉ፦ “ ፀሐይና ጨረቃ አላህ መኖሩን የሚጠቁሙ (ታላቅ) ምልክቶች ናቸው፤አንድ ሰው ስለሞተ ወይም ስለተወለደ አይጋረዱም።” ስለዚህ ነቢዩ ምኅዋር ላይ የሚከሰተው ነገር ከምድር ክስተተ ጋር ምንም ትስስር እንደሌለው አረጋገጡ። ኮከብ ቆጠራ ይህ ከመሆኑ በተጨማሪ የድግምት አይነትም ነው።
በተጨማሪም መሰረተ ቢስና ከእውነት የራቁ ውስጣዊ ስሜቶች ማለትም መደሰት ወይም መሸበር የሚባል ስሜትን በነፍስ ውስጥ ይፈጥራሉ። ስለዚህም ይህ ደግሞ ሰዎች ማብቂያ የሌለው ምናብ ውስጥ እንዲዋኙ እና ህይወታቸውን በሙሉ በገደቢስነት ፈርጀው እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።
ሌላ የኮከብ ቆጠራ አይነት አለ። እርሱም ፦ ጊዚያት፤ወራትን እና ወቅትን ለማወቅ ከዋክብት የሚመለከቱ ሰዎች አሉ። ይህ ምንም ችግር የለውም። ለምሳሌ፦ እንዲህ ተብሎ የሚጠራው የኮከብ አይነት ከጠለቀ የዝናብ ወቅት ገብቷል ማለት ነው ሊል ይችላል።ወይም ደግሞ ፍራፍሬዎች የሚደርሱበት ወቅት ገብቷል ሊል ይችላል። ይህ አይነቱ ትንበያ በሸሪዓችን ምንም ችግር የለውም።