Back to Top
ኢማን ይጨምራል ይቀንሳልን? በምን እንደሚጨምርና በምን እንደሚቀንስ ማወቅ እንፈልጋለን።

ጥያቄ(27): ኢማን ይጨምራል ይቀንሳልን? በምን እንደሚጨምርና በምን እንደሚቀንስ ማወቅ እንፈልጋለን።
መልስ:

በቀደር ማመን አስመልክቶ ትንሽ የሚቀረን ነገር አለ። እሱም በቀደር ማመን የሰው ልጅ በቀልቡ በሚያደርገው ጉዞ እጅግ የላቁ ፍሬዎችን ያገኛል። ምክንያቱም ሁሉም ነገር የሚከሰተው በአላህ ውሳኔ መሆኑን ስታምን የሚያስደስት ነገር ሲገጥምህ ጌታህን ታመሰግናለህ፤በራስ ብልሃትና ሀይል እንዳልሆነ ስታውቅ በራስህ አትደነቅም። የሚያስደስትህን ነገር ያሳካህበት ሰበቡን አሟልተህ ከሆነ ውለታው ሙሉ ለሙሉ በአላህ እጅ እንደሆነ ታምናለህ። በዚህም ፀጋ እሱን ማመመስገን ትጨምራለህ።ተጨማሪ ኢባዳዎችን በታዛዝክበት መሰረት እንድትሰራ ይገፋፋሃልም። በጌታህ ላይም እንዳትመፃደቅ ይረደሃል። እንዲያውም በአንተ ላይ አላህ የዋለልህን ውለታና ፀጋ እንድታስተውል ያደርግሃል።

አላህ እንዲህ ይላል፦

“በመስለማቸው በአንተ ላይ ይመጻደቃሉ «በእስልምናችሁ በኔ ላይ አትመጻደቁ፤ ይልቁንም አላህ ወደ እምነት ስለ መራችሁ ይመጸደቅባችኋል፤ እውነተኞች ብትኾኑ» (መመጻደቅ ለአላህ ነው) በላቸው፡፡” [አልሑጅራት:17]

ልክ እንዲሁም ችግር ሲደርስብህ ከአላህ እንደሆነ በማመን ሳትፀፀት ውሳኔውን በውዴታ ትቀበላለህ። ይህም በማድረግህ ፀፀትም አይደርስብህም። መልክተኛው ያሉትን አልሰማህምን!?፦ “ጠንካራ አማኝ ከደካማው አማኝ አላህ ዘንድ በላጭና ይበልጥ ተወዳጅ ነው። በሚጠቅምህ ነገር ላይ ትጉህ ሁን።በአላህ ታገዝ፤አትስነፍ። አንዳች ነገር ቢደርስብህም ይህን ባደርግ ይህ ባልሆነ ነበር አትበል። ነገር ግን አላህ የሻውን ወሰነ ፈፀመም በል። እንዲህ ቢሆን የሚለው መላምት የሸይጣንን በር ይከፍታል።”

በቀደር ማመን ለመንፈስ እና ለቀልብ እረፍት ነው።ባለፈው ነገር ላይም ሐዘን እንዳይሰማህ ያደርጋል። ለወደፊት በሚገጥም ነገር እንዳትጨናነቅና እንዳትተክዝ ያደርግሃል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል ፦

“በምድርም በነፍሶቻችሁም መከራ (ማንንም) አትነካም ሳንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትኾን እንጅ፡፡ ይህ በአላህ ላይ ገር ነው፡፡ (ይህ ማሳወቃችን) ባመለጣችሁ ጸጋ ላይ እንዳታዝኑ አላህም በሰጣችሁ ነገር (በትዕቢት) እንዳትደሰቱ ነው፡፡” [አልሐዲድ:22 - 23]

በቀደር የማያምን ሰው አደጋ ሲደርስበት ያለምንም ጥርጥር መበሳጨቱና መማረሩ አይቀሬ ነው። ሸይጣንም የሁሉንም በር ከፍትለታል።የሚያስደስት ነገር ሲገጥመው ደግሞ በራሱ ይደነቃል ይኮፈሳልም። ነገር ግን በቀደር ማመን እነዚህ ነገሮች በሙሉ እንዳይከሰቱ ይከለክላል።

ኢማን ይጨምራል፤ይቀንሳል የሚለውን አስመልክቶ አህሉ ሱናህ ዘንድ ኢማን ማለት በቀልብ ማረጋገጥ፤በአንደበት መናገር፤በአካል መስራትን ያካተተ ነው። ኢማን እነዚህ ሦስት ነገሮችን ያቀፈ በመሆኑ መቀነስና መጨመርን ያስተናግዳል። ምክንያቱም በቀልብ ላይ ያለ እምነት ይበላለጣልና። እኛ ዘንድ እንኳ በወሬ የሰማነውን እና በአይን ያየነውን ነገር አስመልክቶ እኩል የሆነ እርግጠኝነት አይኖረንም። አንድ ሰው የነገረን እና ሁለት ሰዎች የነገሩን ነገርን አስመልክቶ እኩል እምነት እንኳ የለንም። ወዘተ …

ለዚህም ሲባል ኢብራሂም ዐለይሂ ሰላም እንዲህ ይላሉ፦

“ኢብራሂምም «ጌታዬ ሆይ! ሙታንን እንዴት ሕያው እንደምታደርግ አሳየኝ» ባለ ጊዜ (አስታውስ፡፡) አላህ ፡- «አላመንክምን?» አለው፡፡ «አይደለም (አምኛለሁ)፤ ግን ልቤ እንዲረጋጋ» ነው አለ፡፡” [አልበቀራ:260]

ስለዚህም ቀልብ ውስጥ ካለው ማረጋገጥ፤መረጋጋትና ስክነት አንፃር ኢማን ይጨምራል።ይህ ደግሞ አንድ ሰው ስለ ጀነት እና እሳት የሚወሳበት የኢልም መድረክ ላይ እንኳ ሲሳተፍ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ላይ የሚያስተውለው ነገር አለ። እምነቱ ከመጨመሩ የተነሳ በዓይኑ የማየት ያህል የሚሰማውም ጊዜ አለ። ከዚህ የኢልም መድረክ ተነስቶ ዝንጉነት ላይ ሲሆን ቀልቡ ውስጥ ያለው እርግጠኝነት እየተመናመነ ይሄዳል።

ልክ እንደዚሁ ከንግግር አንፃር እምነት ይበላለጣል። አላህን አስር ጊዜ በአንደበቱ ያወሳ አንድ መቶ ግዜ ካወሳው ጋር እኩል አይሆንም። ሁለተኛው ከመጀመሪያው እምነቱ እጅግ የጨመረ ይሆናል።

በአካል የሚሰሩ ኢባዳዎችንም አስመልክቶ እንዲሁ ሰዎች በእምነት ይበላለጣሉ።አምልኮትን በተሟላ መልኩ ወደ አላህ ያደረሰ ሰው በተጓደለ መልኩ ከፈፀመ ሰው በላይ እምነቱ የጨመረ ነው። አንድ ሰው ከሌላው ሰው በበለጠ መልኩ ተግባርን በብዛት ከፈፀመ ኢባዳን ካጓደለ ሰው በላይ እምነቱ ይጨምራል። እምነት እንደሚጨምርና እንደሚቀንስ የሚያሳዩና የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በቁርኣንና በሐዲስ መጥተዋል።

አላህ እንዲህ ይላል፦

“የእሳትንም ዘበኞች መላእክት እንጅ ሌላ አላደረግንም፡፡ ቁጥራቸውንም ለእነዚያ ለካዱት መፈተኛ እንጅ አላደረግንም፡፡ እነዚያ መጽሐፍን የተሰጡት እንዲያረጋግጡ፣ እነዚያም ያመኑት እምነትን እንዲጨምሩ፣” [አልሙደሲር:31]

እንዲህም ይላል፦

“ ሱራም (ምዕራፍ) በተወረደች ጊዜ ከእነሱ (ከመናፍቃን) ውስጥ ማንኛችሁ ነው᐀ ይህች (ምዕራፍ) እምነትን የጨመረችለት የሚል ሰው አልለ፡፡ እነዚያ ያመኑትማ የሚደሰቱ ሲኾኑ እምነትን ጨመረችላቸው፡፡እነዚያም በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ያለባቸውማ በርክሰታቸው ላይ ርክሰትን ጨመረችላቸው፡፡ እነርሱም ከሓዲዎች ኾነው ሞቱ፡፡” [አት ተውባ:124_125]

በሐዲስ ላይ ደግሞ የአላህ መልክተኛ (ሰለለሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፦

“አእምሮውና ሐይማኖቱ (ዲኑ) የተጓደለ፣ ጥንቁቅ የሆነን የወንድ ልቦና እንዳያመዛዝን የሚያደርግ እንደ እናንተ ሴቶች ምንንም አላየሁም፡፡” ስለዚህም ኢማን ይጨምራል ይቀንሳልም። ነገር ግን ኢማን እንዲጨምርም ሆነ እንዲቀንስ የሚያደርጉ ሰበቦች ምንድን ናቸው? ከተባለ እነሆ፦

አንደኛው ሰበብ፦ አላህን በስምቹና በባህሪያቶቹ ማወቅ። አንድ ሰው አላህን አስመልክቶ ስምቹና ባህሪያቶቹ ላይእውቀቱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ያለምንም ጥርጥር እምነቱም ይጨምራል። ለዚህም ሲባል የአላህ ስምችና ባህሪያቶች ላይ ከሌላው በበለጠ እውቀት ያላቸው የእውቀት ባልተቤቶች ከዚህ አንፃር ከሌሎች የጠነከረ እምነት ኖራቸው ታገኛቸዋለህ።

ሁለተኛው ሰበብ: ተፈጥሯዊና ሸሪዓዊ የአላህ መኖሩን የሚጠቁሙ ምልክቶችን በማስተዋል መመልከት። የሰው ልጅ አላህ የፈጠራቸውን ፍጥረታት ማለትም ሰማያትና ምድር የሰው ልጅ አፈጣጠር እና እንሰሳቶች እንዴት እንደተፈጠሩ ባየና ባስተወለ ቁጥር እምነቱ ይጨምራል። አላህ እንዲህ ይላል፦

“በምድርም ውስጥ ለሚያረጋግጡ ሰዎች ምልክቶች አልሉ፡፡ በነፍሶቻችሁም ውስጥ (ምልክቶች አሉ)፤ ታዲያ አትመለከቱምን?” [አዛሪያት:20_21]

ይህን የሚጠቁሙ የቁርኣን አንቀፆች እጅግ በርካታ ናቸው። ማለትም የሰው ልጅ ፍጥረተ ዓለሙን በማስተንተን የተመለከት እንደሆነ እምነቱ እንደሚጨምር።

ሦስተኛው ሰበብ፡ መልካም ስራዎችን ማብዛት። የሰው ልጅ መልካም ስራዎቹ በበዙ ቁጥር እምነቱ ይጨምራል።እነዚህ የአምልኮ አይነቶች ተግባራዊ ወይም አንደበታዊ የኢባዳ ዘርፎች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፦ ዚክር ማድረግ ኢማን በጥራትም ይሁን በብዛት እምነትን ይጨምራል። እንደዚሁም ሰላት፤ ጾምና ሐጅ ከጥራትም ይሁን ከብዛት አንጻር እምነትን ይጨምራሉ።

ኢማንን እንዲቀንሱ የሚያደርጉ ሰበቦች ደግሞ ከላይ የጠቅስናቸው ነገሮች በተቃራኒ የሚፈፀሙ ከሆነ። ማለትም አላህን በስምቹና በባህሪያቶቹ አለማወቅ እምነት ለመጉደል ሰበብ አንዱ ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ አላህን በስምቹና በባህሪያቶቹ የማያውቅ ከሆነ እምነቱ እንዲጎል ምክንያት ይሆናልና።

ሁለተኛው ሰበብ፤ ተፈጥሯዊና ሸሪዓዊ አላህ መኖሩን የሚጠቁሙ ምልክቶችን በማስተዋል አለመመልከትና ችላ ማለት ሲሆን ይህ ድርጊት እምነት እንዲቀንስ ወይም ባለበት ሳይጨምር እንዲቆይ ያደርጋል።

ሦስተኛው ሰበብ፤ ሐጢያት መስራት። ምክንያቱም ሐጢያቶች እጅግ ከባድ የሆነ መጥፎ ተፅእኖን ቀልብ እና እምነት ላይ ያሳድራሉ። ለዚህም ሲባል ነው የአላህ መልክተኛ (ሰለለሁ አለይሂ ወሰለም) ፦

“አንድ ሰው አማኝ በሆነበት ሰዓት ዝሙትን አይፈፅምም።” ያሉት።

አራተኛው ሰበብ፤ መልካም ስራን መተው። መልካም ስራን መተው ኢማን እንዲጎል ከሚያደርጉ ሰበቦች አንዱ ነው። ነገር ግን የተወው የአምልኮት ዘርፍ ግዴታ ከሆነና ያለምንም ሸሪዓዊ ዑዝር ካልተገበረ እምነቱ ከመቀነሱ ባሻገር ይወቀሳል ይቀጣልም። ግዴታ ያልሆኑ የኢባዳ አይነቶችን ወይንም ግዴታ ሆነው በሸሪዓዊ ዑዝር የተነሳ ከተወ ወቀሳም ሆነ ቅጣት አይኖርበትም። ለዚህም ሲባል መልክተኛው ሴቶችን አእምሯቸውና ሐይማኖታቸው (ዲናቸው) የተጓደለ መሆናቸውን ተናግረዋል።የዲን መጓደል ምክንያቱን ሲያብራሩ ፦ በወር አበባ ጊዜ ሰላት እና ጾምን በመተዋቸው የተነሳ እምነታቸው እንደሚጎድል ተናግረዋል።  በወር አበባ ጊዜ ደግሞ ሰላትና ጾምን በመተዋቸው አይወቀሱም። እንዲያውም በሐይድ ወቅት ከኢባዳ እንዲታቀቡ ታዘዋል። ሆኖም ወንዶች የሚሰሩትን ኢባዳ መስራት ስለሚያመልጣቸው ከዚህ አንጻር ሴቶች ከወንዶች በእምነት የጎደሉ ናቸው።




Share

ወቅታዊ