Back to Top
ከእምነት ማዕዘን መካከል በቀደር ማመን የሚለው ርዕስ ይቀረናልና ስለርሱ ቢነግሩን።

ጥያቄ(26): ከእምነት ማዕዘን መካከል በቀደር ማመን የሚለው ርዕስ ይቀረናልና ስለርሱ ቢነግሩን።
መልስ:

በቀደር ማመን መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ጂብሪል መጥቶ ስለ ኢማን ጠይቋቸው ስድስቱ የኢማን ማዕዘናትን ከነገሩት ውስጥ አንዱ በቀደር ማመን የሚለው ነበር። በቀደር ማመን እጅግ በጣም ወሳኝና አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ከድሮ ጀምሮ ሰዎች በቀደር ላይ ተወዛግበዋል። በመልዕክተኛው ዘመን እንኳ በቀደር ላይ የሚከራከሩና የሚጨቃጨቁ ሰዎች አልጠፉም።ዛሬም በዘመናችን ላይ ያሉ ሰዎች በቀደር ላይ ይጨቃጨቃሉ። ነገር ግን አላህ ምስጋና ይገባውና እዚህ ላይ ያለው ሐቅ ግልፅ እና ፍንትው ያለ ነው። ምንም ጭቅጭቅና ንትርክ አይሻም። አላህ ሁሉን ነገር ወስኖ ፈጥሮታል ብለህ ማመንህ በቀደር ማመን ላይ ያለህን እምነት የተሟላ ያደርገዋል። አላህ እንዳለው

“ነገሩንም ሁሉ የፈጠረና በትክክልም ያዘጋጀው ነው፡፡” [አልፉርቃን ፡ 2]

ይህ አላህ የፈጠረውና በልኩ ያዘጋጀው ቀደር የአላህን ጥበብ ተከትሎ የሚከሰት ነገር ነው። እነዚህ ጥበቦችም የላቁና ምስጉን የሆነ ግቦችን በማስፈረዳቸው የተነሳ በስተመጨረሻ ለሰው ልጆች ለዱንያቸውም ሆነ ለአኼራቸው እጅግ ጠቃሚ ነገርን ያዘሉ ሆነው እናገኛቸዋለን።

በቀደር ማመን በአራት ነገሮች(ደረጃዎች) ላይ ይሽከረከራል።

አንደኛው/ በአላህ ፍፁማዊ እውቀት ማመን፤ ይህም ማለት አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሁሉንም መጪውንም ያለፈውንም አሁን ላይ የሚከሰተውንም እንዲሁም ከርሱ ድርጊት ሆነ ከፍጥረታት ስራ ጋር ተያያዥነት ያላቸውንም ድርጊቶች ሙሉ ለሙሉ ያውቃቸዋል ብሎ በተሟላ መልኩ ማመን በአላህ ፍፁማዊ እውቀት ማመን ተብሎ ይታወቃል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ “አዘል” (ጥንታዊ) እና ዘላለማዊ በሆነው እውቀቱ እነዚህን ነገሮች በጥቅልና በዝርዝር ጠቅልሎ ያውቀዋል።

ይህን የቀደር ደረጃ የሚጠቁሙ የቁርኣንና የሐዲስ ማስረጃዎች እጅግ በርካታ ናቸው። አላህ ተባረከ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

”አላህ በምድርም በሰማይም ምንም ነገር በርሱ ላይ አይሰወርም፡፡” [አልኢምራን:5]

እንዲህም ይላል፦

“ የሩቅ ነገርም መክፈቻዎች እርሱ ዘንድ ናቸው፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ በየብስና በባሕር ያለውንም ሁሉ ያውቃል፡፡ ከቅጠልም አንዲትም አትረግፍም የሚያውቃት ቢኾን እንጅ፡፡ ከቅንጣትም በመሬት ጨለማዎች ውስጥ የለም ከእርጥብም ከደረቅም አንድም የለም ግልጽ በኾነው መጽሐፍ ውሰጥ (የተመዘገበ) ቢኾን እንጅ፡፡” [አልአንዐም:59]
እንዲህም ይላል፦ “ሰውንም ነፍሱ (በሐሳቡ) የምትጎተጉተውን የምናውቅ ስንሆን በእርግጥ ፈጠርነው።” [ቃፍ:16]
እንዲህም ይላል፦ “አላህ በምትሰሩት ነገር ላይ አዋቂ ነው።” [አልበቀራ: 283]

የአላህ እውቀት ገደብ እንደሌለው እንዲሁም ሁሉምን ነገር በጥቅል እና በዝርዝር እንደሚያውቅ የሚያመላክቱ ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ።

ይኸኛውን የቀደር ደረጃ ያስተባበለ ሰው ካፊር ይሆናል። ምክንያቱም አላህን፤መልክተኛውንና የሙስሊሞችን ስምምነት ያስተባበለ በመሆኑ፤የአላህ ሙሉዕነት ላይ ትችትን በመሰንዘሩ ነው ፤ይህም የእውቀት ተቃራኒው አለማወቅ ወይም መርሳት ነው እነዚህ ነገሮች ደግሞ አላህ ላይ እንደ ነውርና ጉድለት ይቆጠራሉ። ፊርዐውን ሙሳን በጠየቀው ጊዜ ሙሳ የመለሰለትን አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሲያወሳ እንዲህ ይላል፦ “(ፈርዖንም) «የመጀመሪያይቱ ዘመናት ሕዝቦች እጣ ፈንታ ምንድን? (ሙሳም) «ዕውቀትዋ ጌታዬ ዘንድ በመጽሐፍ የተመዘገበ ነው፡፡ ጌታዬ አይሳሳትም አይረሳምም» አለው፡፡” “አይሳሳትም” ማለት ወደፊት የሚከሰቱትን ነገሮች አስመልክቶ አይሳሳትም ማለት ነው። ”አይረሳም” ማለት ደግሞ ያለፈውን ድርጊቶች በሙሉ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ አይረሳም ማለት ነው።

ሁለተኛው የቀደር ደረጃ ደግሞ: በለውሀል መህፉዝ (በተጠበቀው ሰሌዳ) ማመን፤ እስከ ትንሳኤ ድረስ የሚከናወነውን ነገር ሁሉ አላህ በለውሀል መህፉዝ መዝግቦታል ብሎ ማመን ነው። አላህ ቀለምን ለመጀመሪያ ጊዜ በፈጠረው ጊዜ “ፃፍ” አለው። ቀለምም፦ “ጌታዬ ምን ልፃፍ?” ብሎ ጠየቀ አላህም፦ “ወደ ፊት የሚከሰተውን በሙሉ ፃፍ “አለው። ታዲያ በዚያን ጊዜ እስከ ቂያማ ዕለት የሚሆነውን በጥቅልና በዝርዝር የሚከሰቱ የሁሉ ነገር የሁሉም ውሳኔዎች በለውሀል መህፉዝ (በተጠበቀው ሰሌዳ) ተጻፈ።

ይኸኛውና ያሳለፍነውን ደረጃ አስመልክቶ ቀጣዩ የቁርኣን አንቀፅ ማስረጃ ነው።

“አላህ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ በእርግጥ የሚያውቅ መኾኑን አታውቅምን? ይህ በመጽሐፍ ውስጥ (የተመዘገበ) ነው፡፡ ይህ በአላህ ላይ ገር ነው፡፡” [አልሐጅ:70]

“ይህ በመጽሐፍ ውስጥ (የተመዘገበ) ነው፡፡” ይህ ማለት አላህ ዘንድ በመጽሓፉ የታወቀ ነው ማለት ነው። “በመጽሐፍ ውስጥ” የሚለው ደግሞ ለውሀል መህፉዝ ማለት ነው የተፈለገበት። “ይህ በአላህ ላይ ገር ነው፡፡” ይህ አጻጻፍ አንዳንዴ በዝርዝር የሚሆንበትም ጊዜ አለ። አንድ ፅንስ በእናቱ ማህፀን ሳለ አራት ወራት ካለፈው መላኢካ ወደሱ ተልኮ አራት ነገሮችን እንዲፅፍ ይደረጋል።ሪዝቁን፤እድሜውን፤ተግባሩን እና እድለኛነቱ ወይም እድለቢስነቱን ይጽፋል። ቡኻሪ በዘገቡትና ዐብደላህ ኢብኑ መስዑድን ከመልክተኛው ሰምተው እንዳስተላለፉት።

 ከእንደገናም በለይለቱ አልቀድርም በአመቱ የሚከሰቱ ነገሮች ይጻፋሉ። አላህ እንዳለው፦

“እኛ (ቁርኣኑን) በተባረከች ሌሊት ውስጥ አወረድነው፡፡ እኛ አስፈራሪዎች ነበርንና፡፡በውስጧ የተወሰነው ነገር ሁሉ ይልለያል፡፡ከእኛ ዘንድ የኾነ ትእዛዝ ሲኾን (አወረድነው)፡፡ እኛ (መልክተኞችን) ላኪዎች ነበርን፡፡” [አዱኻን:3_5]

ሦስተኛው ደረጃ: በዚህ ፍጥረተ ዓለም ላይ አላህ የሚሰራውም ሆነ የሰው ልጆች አሊያም በአጠቃላይ ፍጥረታት የሚሰሯቸው ነገሮች በአላህ ፍቃድ(መሺኣህ) ይሚከወኑ መሆናቸውን ማመን ነው። ማለትም እርሱ የሻው ይሆናል፤ እርሱ ያልሻው አይሆንም። 

አላህ ተባረከ ወተዓላ እንዳለው፦ “አላህም የሚሻውን ይሠራል፡፡” [ኢብራሂም:27]
አላህ ተባረከ ወተዓላ እንዲህም ይላል፦ “በሻም ኖሮ ሁላችሁንም በእርግጥ ባቀናችሁ ነበር፡፡” [አንነሕል:9]
እንዲህም ይላል፦ “በሻ ኖሮ ሰዎችን ሁሉ አንድ ሕዝብ ባደረጋቸው ነበር፡፡” [ሁድ:118] አላህ ተባረከ ወተዓላ እንዲህም ይላል ፦” ቢሻ ያስወግዳችኋል፡፡ አዲስንም ፍጡር ያመጣል፡፡” [ፋጢር :16]

የእርሱም ተግባር ሆነ የፍጡሮቹ ተግባራት የሚከሰቱት በርሱ ፈቃድ መሆኑን የሚያሳዩ እጅግ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።

 አላህ ተባረከ ወተዓላ እንዳለው

“አላህም በሻ ኖሮ እነዚያ ከእነርሱ (ከመልክተኞቹ) በኋላ የነበሩት ግልጽ ታምራቶች ከመጡላቸው በኋላ ባልተጋደሉ ነበር፡፡ ግን ተለያዩ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ያመነ ሰው አልለ፡፡ ከነርሱም ውስጥ የካደ ሰው አልለ፡፡ አላህም በሻ ኖሮ ባልተዋጉ (ባልተለያዩ) ነበር፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ይሠራል፡፡” [አልበቀራ:253]

ሰዎች የሚሰሯቸው ድርጊቶች በሙሉ አላህ በፈቀደው መልኩ እንዲሆኑ ይህ አንቀፅ ግልፅ ማስረጃ ነው። አላህ ድርጊቱን እንዳይፈፀም ቢፈልግ ኖሮ አይፈፀምም ነበር።

አራተኛው የቀደር ደረጃ፦ አላህ ነገሮችን ሁሉ የፈጠረ መሆኑን ማመን፤ ከእርሱ ጋር ሌላ ፈጣሪ የለም።አላህ የሁሉም ፈጣሪ ሲሆን ከርሱ ውጭ ያሉ ነገሮች በሙሉ ፍጡር ናቸው።ፍጡራን የሚሰሩትም ሆነ የሚናገሩት በሙሉ አላህ ነው ያስገኛቸው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ድርጊቱና ንግግሩ ከባህሪው ይቆጠራሉ። የሰው ልጅ ፍጡር ነው ከተባለ ባህሪውንም እርሱንም የፈጠረ አላህ ነው። ይህን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ይላል፦

“እናንተንም ስራችሁንም አላህ ፈጠረ።” [አሷፋት :96]

በዚህ አንቀፅ መሰረት ሰውንም ድርጊቱንም የፈጠረ አላህ መሆኑን ይጠቁማል።  እነዚህ አራት የቀደር ደረጃዎችን ሙሉ ለሙሉ ያልተቀበለና ያላመነ በቀደር አምኗል አይባልም።

ደግመንም ፦ በአላህ ፍፁማዊ እውቀት በዝርዝርም ሆነ በጥቅል በሆነው የአላህ እውቀቱ ማመን ይኖርብሃል።

ሁለተኛው፦ እስከ ትንሳኤ ድረስ የሚከናወነውን ነገር ሁሉ አላህ በለውሀል መህፉዝ ላይ መዝግቦታል ብለህ ማመን አለብህ።

ሦስተኛው ፤ማንኛውም የሚከሰት ነገር በአላህ ፍቃድ መሆኑን ማመን።

አራተኛ አላህ ነገሮችን ሁሉ የፈጠረ መሆኑን ማመን።

ከዚህም በመቀጠል በቀደር ማመን ሰበቦችን ከመስራት ጋር አይቃረንም። እንዲያውም ሰበቦችን መስራት ሸሪዓው ያዘዛቸው ነገሮች ናቸው።  እሱም ቢሆን በቀደር ነው የሚከሰተው። ምክንያቱም ሰበቦች ሰበቡ እንዲከሰት ያደረገው ነገርን አብሮ ይወልዳል።  ለዚህም ሲባል አሚሩል ሙእሚኒን ዑመር ኢብኑል ኸጣብ ወደ ሻም ጉዞ ጀምሮ ሳለ ሻም ውስጥ ወረርሽኝ እንደገባ ሰማ። ጉዞውን መቀጠል አሊያም ወደ መዲና መመለስ ይሻል ይሆን የሚለውን ጉዳይ ለሰሓቦች አማከረ።  ይቀጥል አሊያም ይመለስ በሚለው ጉዳይ የተነሳ በመሀከላቸው አለመግባባት ተፈጠረ። መጨረሻ ላይ ግን ወደ መዲና መመለስ እንዳለባቸው ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ይህን ባደረጉ ጊዜ አቡ ዑበይዳ ኢብኑ ጀራሕ (ዑመር በጣም ያከብረውና ያልቀው የነበረ ሰው ነበር።) ወደ ዑመር ጋር በመምጣት ፦ ያ አሚረል ሙእሚኒን! እንዴት ወደ መዲና ይመለሳሉ? ከአላህ ቀደር መሸሽ ፈልገው ነውን? አሏቸው። ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ፦ “ከአላህ ቀደር ወደሌላኛው የአላህ ቀደር እንሸሻለን።” ብለው መለሱለት።

ከዚህም በኋላ ዐብዱረሕማን ኢብኑ ዐውፍ በሆነ ጉዳዩ እዚህ ቦታ ላይ አልነበረምና በመጣ ጊዜ “አንድ አገር ውስጥ ወረርሽኝ መኖሩን በሰማችሁጊዜ ወደዛ አገር አትምጡ።” ብለዋል የአላህ መልክተኛ በማለት ነገራቸው።

ያም ሆነ ይህ ዋናው ቁም ነገር ዑመር፦ “ከአላህ ቀደር ወደ ሌላኛው የአላህ ቀደር እንሸሻለን።” ብለው የተናገሩት ንግግር ሰበቦችን መያዝ ከአላህ ቀደር እንደሚካተት ያሳየናል። እንበልና አንድ ሰው “እኔ በአላህ ቀደር ስለማምን ሚስትም ባይኖረኝ አላህ ልጅ ይሰጠኛል” ቢል ከአዕምሮ በሽተኞች እንቆጥረዋለን። እንዲሁም እኔ በአላህ ቀደር ስለማምን ሪዝቅ ፍለጋ አልሯሯጥም ቢለንና፤ ሪዝቁን ለማግኘት ምንም አይነት ሰበብን የማይጠቀም ከሆነ ከቂሎች እንቆጥረዋለን።

ከዚህም በመቀጠል ልታውቀው የሚገባ ነገር ቢኖር አንዳንዴ ቀደር ላይ እንደ ችግር የሚነሱ ነገር ግን ምንም ችግር የሌላቸው ነገሮች አሉ። እርሱም ፦ ይህ የምሰራው ወንጀል አላህ ወስኖብኝ የምሰራው ከሆነ እንዴት እርሱ በቀደረብኝ ነገር ይቀጣኛል? የሚለው ጥያቄ ነው። ለዚህ መልስ ደግሞ እነሆ፦

ወንጀልን በቀደር ማሳበብህ ምንም ማስረጃ አይሆንልህም፤ምክንያቱም አላህ ወንጀል እንድትሰራ አላስገደደህምና። በተጨማሪም ገና ወንጀልን ለመስራት ስታቅድ እንደተቀደረብህ የምታውቀው ነገር የለምና። የሰው ልጅ አንድ የተቀደረውን ነገር ከተከሰተ በኋላ እንጂ ስለሱ የሚያውቀው ነገር አይኖርም። ወንጀልን ከመስራትህ በፊት አላህ ዒባዳ ቀድሮብኛል ብለህ ለምን ኢባዳን አትሰራም? በዱንያህ ጉዳይ ላይ መልካም ለማግኘት እንደምትሯሯጠውና ሸር የሆነ ነገር እንዳይደርስብህ እንደምትሸሸው የአኼራንም ጉዳይ ለምን እንዲሁ አታደርግም? ለምሳሌ፦ አንድ ሰው ወደ መካ የሚወስዱ ሁለት መንገዶች ቢኖሩት፤ አንደኛው በጣም ቀላልና ሰላም የሆነ መንገድ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እጅግ አስፈሪና አደጋ ያለበት መንገድ ነው ብለን ከነገርነው በኋላ፤ እጅግ አስፈሪና አደጋ ያለበት መንገድ አላህ ቀድሮብኛልና እጓዛለው የሚል ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም። ሰምቼም ገጥሞኝም አላውቅም። አሁን በሰጠሁት ምሳሌ መሰረት ጀነትም ይሁን እሳት ሁለት መንገዶች አሉት፤ ከሚለው አባባል ጋር ምንም ልዩነት የለም። በእሳት መንገድ ላይ በምርጫህ የምትጓዝ ከሆነ እጅግ አስፈሪና ጭው ያለ በአደጋ የተከበበ የመካ መንገድን እንደተጓዘው ሰው ነው ምሳሌህ። ታዲያ ለነፍስህ የደስታውና የተድላውን መንገድ ትተህ ለምን የእሳትን መንገድ መጓዝ መረጥክላት?

የሰው ልጅ ወንጀል ለመስራቱ ማስረጃ ቢኖረው ኖሮ መልክተኞች መላክ ባላስፈለገ ነበር። አላሁ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል፦

” ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች የኾኑን መልክተኞች (ላክን)፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡” [አኒሳእ:165]

እምነት ይጨምራል፣ ይቀንሳል።




Share

ወቅታዊ