Back to Top
የሁለቱ የምስክር ቃላት ማለትም ላኢላህ ኢለሏህ ሙሐመዱ ረሱሉሏህ ትርጉም ምንድን ነው?

ጥያቄ(12): የሁለቱ የምስክር ቃላት ማለትም ላኢላህ ኢለሏህ ሙሐመዱ ረሱሉሏህ ትርጉም ምንድን ነው?
መልስ:

ሁለቱ የምስክር ቃላት ላኢላህ ኢለሏህ ሙሐመዱ ረሱሉሏህ ወደ ኢስላም መግቢያ ቁልፍ ናቸው። አንድ ሰው ወደ እስልምና መግባት ከፈለገ እነዚህን ሁለት ምስክር ቃሎች ካልሰጠ ወደ እስልምና መግባት አይችልም። ለዚህም ሲባል የአላህ መልክተኛው ሙዓዝን ወደ የመን በላኩት ግዜ የመጀመሪያ ጥሪውን ወደ ላኢላህኢለሏህ ሙሐመዱ ረሱሉሏህ እንዲያደርግ ነበር የመከሩት።

የመጀመሪያው የምስክር ቃል: ላኢላህ ኢለሏህ የሚለው የምስክር ቃል ሲሆን አንድ ግለሰብ በአንደበቱም ይሁን በቀልቡ ከአላህ በስተቀር የሚመለክ አምላክ እንደሌለ ማመን ይኖርበታል። “ኢላህ” ማለት የሚገዙት የሚያመልኩት ማለት ነው።

ላኢላህ ኢለሏህ የምትለው አ/ነገር ነፍይና ኢስባት በውስጧ ይዛለች። ነፍይ “ላ ኢላህ” የሚለው ሀረግ ውስጥ ሲሆን ኢስባት ደግሞ “ኢለ ሏህ” የሚለው ሀረግ ውስጥ ነው። ይህም ማለት ከአላህ በስተቀር በሐቅ የሚገዙት አምላክ የለም የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል። መጀመሪያ በቀልብ ከአላህ በስተቀር በሐቅ የሚገዙት አምላክ የለም የሚለውን ካረጋገጠ በኋላ በአንደበት መመስከር ይገባል።ይህ ደግሞ አምልኮትን ለአላህ ብቻ በማጥራት ከርሱ ውጭ ካሉ አካል ውድቅ ማድረግ በውስጡ ይይዛል። ላኢላህ ኢለሏህ ስንል ምናልባት ከአላህ ውጭ የሚመለኩ ብዙ አማልክቶች አሉ አይደል ብሎ የሚጠይቅ ሰው ምላሽ ይሆን ዘንድ “በሐቅ የሚለው” በውስጠ ታዋቂ ማስቀመጣችንም ለዚሁኑ ነው እንለዋለን። አላህም በቁርኣኑ አማልክት በማለት ይጠራቸዋል አላህ በቁርኣኑ እንደሚለው፦

“የአላህ ትዕዛዝም በመጣ ጊዜ እነዚያ ከአላህ ሌላ የሚገዙዋቸው አማልክቶቻቸው በምንም አላዳኗቸውም፡፡ ከማክሰርም በቀር ምንም አልጨመሩላቸውም፡፡” [ሁድ:101]

 

እንዲህም ይላል፦ “ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ።” [አልኢስራእ:39]

 

 እንዲህም ይላል፦ “ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ አትጣራ።”  [አልቀሰስ:88]

አላህ እራሱ ከርሱ ውጭ አማልክቶች መኖራቸውን እያረጋገጠ ከአላህ ውጭ የሚገዙት ሌላ አምላክ የለም እንዴት ይባላል? ከተባለ ለዚህ ምላሹ “ከአላህ ውጭ የሚገዙት ሌላ አምላክ የለም´ እነዚህ ከአላህ ውጭ የሚመለኩ አማልክቶች አዎን አማልክቶች ናቸው ነገር ግን የባጢል አማልክት እንጂ የሐቅ አማልክት አይደሉም። የአምልኮት መብት አንዱም አይገባቸውምና። ይህን የሚጠቁመው ቀጣዩ የቁርኣን አንቀፅ ነው።

“ይህ አላህ እርሱ እውነት ከእርሱም ሌላ የሚግገዙት (ጣዖት) ውሸት በመሆኑና አላህም እርሱ የበላይ ታላቅ በመሆኑ ነው፡፡” [ሉቅማን:30]

የሚቀጥለውም አንቀፅ ይህኑ ይጠቁማል፦

“አል-ላትንና አል-ዑዛን አያችሁን? ሦስተኛይቱንም ሌላኛውን መናትን (አያችሁን? የምትግገዟቸው ኃይል አላቸውን? ለእናንተ ወንድ ለእርሱም ሴት (ልጅ) ይኖራልን? ለእናንተ ወንድ ለእርሱም ሴት (ልጅ) ይኖራልን? ይህቺ ይህኔ አድላዊ ማከፋፈል ናት፡፡ እነርሱ እናንተና አባቶቻችሁ (አማልክት ብላችሁ) የጠራችኋቸው ስሞች ብቻ እንጅ ምንም አይደሉም፡፡ አላህ በእርሷ (መግገዛት) ምንም ማስረጃ አላወረደም፡፡ ከጌታቸውም መምሪያ የመጣላቸው ሲኾኑ ጥርጣሬንና ነፍሶች የሚዘነበሉበትን እንጅ ሌላ አይከተሉም፡፡” [አነጅም:19_23]

አላህ ዩሱፍ ዐለይሂሰላም የተናገረውን አስመልክቶ እንዲህ ሲል በቁርኣን ላይ አስቀምጦታል፦

«ከእርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ (አማልክት ብላችሁ) የጠራችኋቸውን ስሞች እንጅ አትገዝዙም፡፡ አላህ በእርሷ ምንም አስረጅ አላወረደም፡፡” [ዩሱፍ:40]

ስለዚህም ላኢላህ ኢለሏህ የሚለው ትርጉም ከአላህ በስተቀር በሐቅ የሚመለክ አምላክ የለም የሚለው ይሆናል።ከአላህ ውጭ ያሉ መልክተኞች፤መላኢካዎች፤ አውሊያዎች ድንጋዮች ዛፎች ፀሀይና ጨረቃ ለሎችም እነዚህ የሚያመልኩ ሰዎች አምላክ ናቸው ብለው ቢሞግቱም ትክክለኛ አምላክ ሳይሆኑ በባጢል የሚመለኩ አማልክት ናቸው። እንዲያውም ትክክለኛው የአምልኮ ተግባር ለአላህ ብቻና ብቻ ነው።




Share

ወቅታዊ