ጥያቄ(110): በፈርድ እና በሱና ሰላቶች መካከል ልዩነት አለን?
መልስ:
አዎን። በፈርድና በሱና ሰላቶች መካከል ልዩነቶች አሉ። አባይት ከሆኑ ልይነቶች መካከል ሙሳፊር የሆነ ግለሰብ ባይቸገርም እንኳ መጓጓዣው ላይ ሆኖ ሱና ሰላትን መስገድ ይችላል። አንድ መንገደኛ መጓጓዣው ላይ ሳለ ማለትም አውሮፕላን ወይም ግመል ላይ አሊያም ሌሎች መጋጓዣ ትራንስፖርት ላይ ሆኖ ሱና ሰላት መስገድ ከፈለገ በየትኛውም አቅጣጫ ይዙር መጓጓዣው ላይ መስገድ ይችላል። ምክንያቱም ይህ ድርጊት ከመልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ተግባር ፀድቆ መጥቷልና። በተጨማሪም በሱና እና ፈርድ ሰላቶች አባይት ከሆኑ ልይነቶች መካከል፤ አንድ ሰው ፈርድ ሰላትን ከጀመረ በኋላ እጅግ ከበድ ያለ ጉዳይ ካልገጠመው በስተቀር ሰላቱን ማቋረጥ አይፈቀድለትም። ሱና ሰላት ላይ ግን መለስተኛ ጉዳይ ከገጠመው እንኳ ከሰላት መውጣት ይፈቀድለታል። ያለ ምክንያት ሰላቱን ቢያቋርጥ እንኳ ወንጀል የለበትም። ሆኖም ተግባሩ ይጠላል ይላሉ ዑለማዎች።
አብይት ከሆኑ ልይነቶች መካከል፤ ፈርድ ሰላቶችን በጀመዓ መስገድ የሚቻል ሲሆን ሱና ሰላቶች ግን ውስን ከሆኑ ሰላቶች ማለትም “ኢስቲስቃእ”፣ “ኹሱፍ” ውጭ ዘውትር ጀመዓ መስገድ አይፈቀድም። ሆኖም አንዳንዴ ሱናን በጀመዓ አልፎ አልፎ መስገድ ይቻላል። መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም አንዳንዴ ሰሃቦችን ለሊት ላይ ያሰግዱዋቸው ነበር። አንዴ ዐብዱላህ ኢብኑ ዓበስ ረዲየላሁ ዐንሁ አንዴ ደግሞ ሁዘይፋ፣ ሌላኛው አጋጣሚ ላይ ደግሞ ዐብደላህ ኢብኑ መስዑድ ነቢዩን ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ተከትለው ሱና ሰላት ሰግደዋል።
ረመዳን ላይ ደግሞ መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ለሦስት ለሊቶች ያህል በጀመዓ ተራዊህን ካሰገዷቸው በኋላ ኡመታቸው ላይ ግዴታ እንዳይሆን በመስጋት ትተውታል። ከዚህ የምንረዳው በረመዳን ውስጥ ተራዊህን በጀመዓ መስገድ ሱና መሆኑን ነው። ምክንያቱም መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ይህን ተግባር ፈፅመውታል። ነገር ግን ኡመታቸው ላይ ግዴታ እንዳይሆን በመስጋት ትተውታል። መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ከሞቱ በኋላ ተራዊህ ግዴታ አይሆንም የሚለው ሀሳብ እሙን ነውና።