Back to Top
ከዒባዳ አይነቶች አንዱን ከአላህ ውጭ ላለ አካል አሳልፎ መስጠት በሸሪዓው ምን ብያኔ አለው?

ጥያቄ(11): ከዒባዳ አይነቶች አንዱን ከአላህ ውጭ ላለ አካል አሳልፎ መስጠት በሸሪዓው ምን ብያኔ አለው?
መልስ:

የዚህ መልስ ምናልባትም እስካሁን ከላይ ካሳለፍነው ነገር መረዳት ይቻላል። ተውሒድ ማለት አላህን በአምልኮ ነጥሎ ብቻውን ማምለክ ማለት ነው ብለናል። ከአላህ ውጭ ያለን አካል ከአምልኮቶች በአንዱ ማምለክ አይፈቀድም። እንደሚታወቀው እርድ የሚባለው የአምልኮ ዘርፍ አንድ ሰው ወደ ጌታው ከሚቃረብበት ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ምክንያም አላህ እርድ ለርሱ ብቻ እንዲሆን እንዲህ ሲል አዟልና።

“ለጌታህ ስገድ ለእርሱም ሰዋም(እረድ)።” [አልከውሰር:2]

ማንኛውም መቃረቢያ የተደረጉ ነገሮች በሙሉ ዒባዳዎች ናቸው። አንድ ሰው ለአላህ እራሱን በማስተናነስና አላህን በማላቅ ዕርድን እንደሚያቀርበው ከአላህ ውጭ ላለ አካል በማላቅ፤ እራስን በማስተናነስ ወደሱ ለመቃረብ በሚል እርድ ያቀረበ ከሆነ በዚህ ተግባሩ በአላህ ላይ አጋርቷል። ሙሽሪክ ደግሞ በርሱ ላይ ጀነት እርም እንደሆነች መኖሪያውም እሳት እንደሆነ አላህ በቁርኣኑ ገልፆታል።

ከዚህም በመነሳት አንዳንድ ሰዎች አውሊያዎች ናቸው ብለው የሚሞግቷቸው መቃብር ዘንድ በመሄድ የሚፈፅሙት የእርድ አይነት ሽርክን ከእስልምና መንገድ የሚያስወጣ ተግባር ነው። ለነዚህ ሰዎች የምንመክረው ፦ ከሚሰሩት ነገር ተፀፅተው ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መመለስ ይኖርባቸዋል። ተውበት በማድረግ ሰላትን፤ ፆምን ለአላህ ብቻ እንደሚያደርጉ ሁሉ እርድንም ለአላህ ብቻ ካደረጉ አላህ ያለፈውን በሙሉ ይቅር ይላቸዋል። አላህ እንዳለው፦

“ለነዚያ ለካዱት በላቸው፡- ቢከለከሉ ለእነሱ በእርግጥ ያለፈውን (ሥራ) ምሕረት ይደረግላቸዋል፡፡” [አልአንፋል:38]

እንዲያውም ከዚህ በላይ አላህ ያደርግላቸዋል። ያም ወንጀላቸውን ወደ መልካም ምንዳ ይቀይርላቸዋል። አላህ እንዲህ ብለዋል፦

“እነዚያም ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ የማይገዙት፣ ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ ያለ ሕግ የማይገድሉት፣ የማያመነዝሩትም ናቸው፡፡ ይህንንም የሚሠራ ሰው ቅጣትን ያገኛል፡፡ በትንሣኤ ቀን ቅጣቱ ለእርሱ ይደራረባል፡፡ በእርሱም ውስጥ የተዋረደ ኾኖ ይኖራል፡፡ተጸጽቶ የተመለሰና ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡ እነዚያም አላህ መጥፎ ሥራዎቻቸውን በመልካም ሥራዎች ይለውጣል፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” [አልፉርቃን:68_70]

ስለዚህም ለነዚህ ወደ ሙታን ለመቃረብ ብለው ቀብር ዘንድ እርድን ለሚፈፅሙ ሰዎች የምመክረው ከዚህ ተግባራቸው ተውበት እንዲያረጉ ነው ይህን ካደረጉ ከባለውለተኛው ጌታቸው ተውባ እንደሚያደርግላቸው ልናብስራቸው እንወዳለን። አላህ ተውበት በሚያደርጉ ሰዎች ይደሰታል።
Share

ወቅታዊ