ጥያቄ(109): በፍቃደኝነት ስለ ሚፈፀሙ የሱና ሰላቶች ትሩፋቶቻቸውና ዓይነቶቻቸው፤ እንዲነግሩን እንሻለን።
መልስ:
አላህ ለባሮቹ ካደረገላቸው እዘነቶችና ውለታዎች መካከል ለእያንዳንዱ ግዴታዊ ተግባሮች በፍቃደኝነት የሚሰሩ መሰል ዒባዳዎችን ደንግጓል።
ሰላትን ብንመለከት እሱን የሚመስሉ ሱና ሰላቶች ተደንግገዋል። ዘካም እንዲሁ በፍቃደኝነት የሚፈፀሙ ምፅዋቶች ተደርጎለታል። ጾምም እንደዚሁ ግዴታ ያልሆኑ ሱና ጾሞች ተደርጎለታል። ሐጅም እንዲሁ። ይህ ባሮች መልካም ምንዳቸው እንዲጨምር፣ወደ እርሱ እንዲቃረቡ እና ግዴታ ተግባሮች ውስጥ የፈጠሯቸውን ክፍተቶች ይሞሉ ዘንድ አላህ አዘወጀለ ለባሮቹ ከማዘኑ የተነሳ ያደረገው ነው። ሱና ተግባሮች የቂያማ ዕለት ፈርድ (ግዴታ ተግባሮች) ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ይሞላሉ።
ግዴታ ሰላቶችን ተከትለው የሚመጡ ሱና ሰላቶች ማለትም፤ሁለቴ ከማሰላመት ጋር ወቅት ከመግባቱ በፊት ሳይሆን ወቅቱ ከገባ በኋላ የዙህር ሱና አራት ረከዓዎች፣ ከፈርድ በኋላ ደግሞ ሁለት ረከዓ ማለትም፤ባጠቃላይ ስድስቱም የዙሁር ሱና ረከዓዎች ናቸው። ዐስር ሰላት በተመለከት ከፊትም ሆነ ከኋላ ጠንከር ያሉ ሱና የለውም። መግሪብ ሰላት ደግሞ ከኋላው ሁለት ረከዓዎች አሉት።ኢሻ ሰላትም እንዲሁ ከኋላው ሁለት ረከዓ ያላቸው ሱና ሰላት አለው። የፈጅር ሰላት ደግሞ ግዴታ የሆነው ሰላት ከመሰገዱ በፊት ሁለት ረከዓ ያሉት ሱና ሰላት አለው። ሆኖም ሱናዎቹን ቀልጠፍ አድርጎ መስገድ በላጭ ተግባር ነው። በአንደኛው ረከዓ ላይ ከፋቲሃ በኋላ “ቁል ያ አዩሃል ካፊሩን” ሲቀራ ሁለተኛው ረከዓ ላይ ደግሞ ከፋቲሃ በመቀጠል “ቁል ሁወላሁ አሀድ” ይቀራል። አሊያም ፤መጀመሪያ ረከዓ ላይ፦
“ قُولُوٓا۟ ءَامَنَّا بِٱللَّهِ وَمَآ أُنزِلَ إِلَيْنَا وَمَآ أُنزِلَ إِلَىٰٓ إِبْرَٰهِۦمَ وَإِسْمَٰعِيلَ وَإِسْحَٰقَ وَيَعْقُوبَ وَٱلْأَسْبَاطِ وَمَآ أُوتِىَ مُوسَىٰ وَعِيسَىٰ وَمَآ أُوتِىَ ٱلنَّبِيُّونَ مِن رَّبِّهِمْ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِّنْهُمْ وَنَحْنُ لَهُۥ مُسْلِمُونَ”
የሚለው ሲነበብ ሁለተኛው ረከዓ ላይ ደግሞ ከፋቲሃ በመቀጠል የሚከተለውን አንቀፅ ያነባል።
“قُلْ يَٰٓأَهْلَ ٱلْكِتَٰبِ تَعَالَوْا۟ إِلَىٰ كَلِمَةٍ سَوَآءٍۭ بَيْنَنَا وَبَيْنَكُمْ أَلَّا نَعْبُدَ إِلَّا ٱللَّهَ وَلَا نُشْرِكَ بِهِۦ شَيْـًٔا وَلَا يَتَّخِذَ بَعْضُنَا بَعْضًا أَرْبَابًا مِّن دُونِ ٱللَّهِ ۚ فَإِن تَوَلَّوْا۟ فَقُولُوا۟ ٱشْهَدُوا۟ بِأَنَّا مُسْلِمُونَ”
በጉዞ ላይ ይሁኑ በቀዬቸው የፈጅር ሱና በጥብቅ መሰገድ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሁለት የፈጅር ሱና አስመልክቶ እጅግ ከባድ ምንዳ እንዳላቸው መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል ፦
“ዱንያና በውስጧ ካዘለቻቸው ነገሮች በሙሉ የፈጅር ሁለት (የሱና) ረከዓዎች ይበልጣሉ።”
ከሱና ሰላቶች መካከል ዊትር ሰላት ይገኝበታል። ጠንከር ካሉ ሱናዎችም ይመደባል። አንዳንድ ዑለማዎች ዋጂብ ነው እስከማለት ደርሰዋል። ኢማሙ አሕመድ ረሂመሁላህ ፦
”ዊትርን የተወ መጥፎ ሰው ነውና ምስክርነቱ ተቀባይነት የለውም።” ብለዋል። የለሊት ሰላቶች በርሱ ይቋጫሉ። ለሊት ተነስቼ መስገድ አልችልም ብሎ የሰጋ ከመተኛቱ በፊት ዊትር መስገድ ይኖርበታል። ለሊት እነቃለሁ ብሎ የሚከጅል ሰው የለሊት ሰላቱን መቋጫ ዊትር ሊያደርግ ይገባል። መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦
“የለሊት ሰላታቹን ማገባደጃ ዊትር አድርጉ።” የዊትር ሰላት ትንሹ አንድ ረከዓ ሲሆን ትልቁ ቁጥር ደግሞ አስራ አንድ ረከዓ ነው። ዝቅተኛውና ሙሉዕ የሚባለው ደግሞ ሦስት ረከዓ ነው። ዊትርን ሦስት ረከዓዎችን አድርጎ ሲሰግድ በተከታታይ ማለትም ሁለተኛው ረከዓ ላይ ተሸሁድ ሳይቀመጥ በማከታተል መጨረሻ ላይ ማሰላመት ይችላል። አሊያም ሁለተኛው ረከዓ ላይ ለተሸሁድ ከተቀመጥ በኋላ ማሰላመትና አንዱን ረከዓ ለብቻ መስገድ ይችላል። አምስት ረከዓ የሚሰግድ ከሆነ ደግሞ አምስቱንም ረከዓዎች በአንድ ተሸሁድ ማሰላመት ይችላል። ዊትር ሰባት ረከዓ መስገድ የፈለገ እንዲሁ በአንድ ተሸሁድና ተስሊም ማጠናቀቅ ይችላል።ዘጠኝ ረከዓ መስገድ የሚሻ ደግሞ ስምንቱ ረከዓዎች በማከታተል ከሰገደ በኋላ ስምንተኛው ላይ ለተሸሁድ ቁጭ ማለት አለበት። ከዚያም ወደ ቀጣዩ ረከዓ በመነሳት ዘጠነኛውን ረከዓ ከሰገደ በኋላ ያሰላምታል። ስለዚህም ሁለት ተሸሁድና አንድ ግዜ ብቻ ማሰላመት ይኖርበታል። አስራ አንድ ረከዓዎች አድርጎ ዊትርን መስገድ የፈለገ ደግሞ በየሁለት ረከዓ ያሰላምትና አንዱን ረከዓ ለብቻው ይሰግዳል።
አንድ ሰው ዊትር መስገድ ከረሳ ወይም ሳይሰግድ እንቅልፍ ከወሰደው ቀን ላይ ጥንድ ረከዓ አድርጎ መስገድ ይችላል። ሦስት ረከዓዎችን መስገድ ያስለመደ ደግሞ አራት ረከዓ በማድረግ መስገድ ይኖርበታል። አምስት ረከዓዎችን ካስለመደ ስድስት ወዘተ …. እያለ ይቀጥላል። ምክንያቱ ከመልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም በተረጋገጠ ሰነድ እንዲህ መጥቷልና፦
“መልክተኛው እንቅልፍ አሸንፏቸው አሊያም አሟቸው ለሊት ለመስገድ ካልተነሱ ቀን ላይ አስራ ሁለት ረከዓዎችን ይሰግዱ ነበር።”