ጥያቄ(107): የሰላት ጀመዓ ሸሪዓዊ ብያኔው ካወቅን ዘንድ መእሙም (ተከትሎ የሚሰግድ ሰው) ከኢማሙ ጋር ያለው ግንኙነት ቢያብራሩልን።
መልስ:
“መእሙምና” ኢማም ያላቸው ግንኙነት መሪና ተከታይ መካከል ያለው ግንኝነት ነው። ለዚህም ሲባል መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂወሰለም እንዲህ ብለዋል፦
“(ሰላት ውስጥ) ኢማም የተደረገው ሊከተሉት ነው። ስለሆነም ተክቢራ ሲያደርግ ወዲያውኑ ተከትላችሁ ተክቢራ አድርጉ፤እርሱ ተክቢራ ሳያደርግ ተክቢራ አታድርጉ። ሩኩዕ ሲያደርግ ተከትላችሁ ሩኩዕ አድርጉ። እሱ ሩኩዕ ሳያደርግ እናንተ ሩኩዕ እንዳታደርጉ። እሱ “ሰሚዐላሁ ሊመን ሀሚዳህ” ሲል እናንተ ደግሞ “አላሁመ ረበና ወለከልሀምድ” በሉ። ሱጁድ ሲያደርግ ተከትላችሁት ሱጁድ አድርጉ። ሱጁድ ሳይወርድ እናንተ ሱጁድ እንዳትወርዱ። እርሱ ቆሞ ከሰገደ እናንተም ቆማችሁ ስገዱ። እርሱ ቁጭ ብሎ ከሰገደ ሁላችሁም ቁጭ ብላቹ ስገዱ።”
እዚህ ቦታ መእሙምና ኢማም ያላቸው ግንኙነት በተመለከተ አራት ሁኔታዎች አሉ። እነሱም፦
እሱን ተከትሎ መስገድ፣እኩል መስገድ፣ኢማሙን ቀድሞ መስገድ እና ወደ ኋላ መቅረት ናቸው።
ኢማምን ተከትሎ መስገድ ለሚለው ምሳሌ፦ ሰጋጅ የኢማምን ድርጊት ተከትሎ ወዲያውኑ መፈፀም ሲሆን ኢማሙ ሩኩዕ ሲያደርግ መእሙሙ ሳይዘገይ ቶሎ ሩኩዕ ማድረግ፣ሱጁድ ሲያደርግ ተከታዩ ሳይዘገይ ሱጁድ ማድረግ ወዘተ…
አሰጋጁን እኩል መከተል ለሚለው ምሳሌ፦ እያንዳንዱን ድርጊት ከኢማሙ ጋር እኩል መፈፀም ሲሆን እኩል ሩኩዕ፣ወይም እኩል ሱጁድ አሊያም እኩል መቆም እና መቀመጥ የሚሉት ለምሳሌነት ተጠቃሽ ነው።
ኢማምን መቅደም ደግሞ፤ ምሳሌው፦ ኢማሙን ቀድሞ ሩኩዕ ወይም ሱጁድ ማድረግ እና የመሳሰሉት ተግባር ላይ መቅደም።
ወደኋላ መዘግየት ለሚለው ደግም ምሳሌው፦ ኢማሙን ከመከተል በጣም ወደኋላ መቅረት ሲሆን ኢማሙ ሩኩዕ ሲያደርግ ተከታዩ ፋቲሃን እየቀራ ቂያም ላይ ይዘገያል። ኢማሙ ሱጁድ ሲያደርግ ገና እርሱ (ተከታዩ) “ሰሚአላሁ ሊመን ሀሚዳህ” ብሎ ይቆማል። እነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል ኢማሙን ወዲያውኑ ተከትሎ ከመስገድ ውጭ ያሉ ድርጊቶች በሙሉ የተወገዙ ናቸው።
እኩል ከኢማሙ ጋር የሚንቀሳቀስ የሚከተለውን የመልክተኛውን ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲስ ጥሷል። መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፦
“ኢማሙ ተክቢራ እስኪያደርግ ጠብቃቹ ተክቢራ አድርጉ። እርሱ ሩኩዕ እስኪያደርግ ጠብቃችሁ (ከኋላው) ሩኩዕ አድርጉ።”
ኢማሙን ቀድሞ የሚሰግድ ደግሞ መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እጅግ ያወገዙትን ተግባር ፈፅሟል።
“ከኢማሙ በፊት ቀድሞ ጭንቅላቱን የሚያነሳ ወደ አህያ ጭንቅላት አላህ እንደሚቀይረው አይሰጋምን!? ወይም ደግሞ ምስሉን ሙሉ ለሙሉ ወደ አህያ እንደሚቀየር አይሰጋምን?!።”
ወደ ኋላ የሚዘገይ ደግሞ ኢማምን መከተል ላይ ያለውን የመልክተኛውን ትዕዛዝ አልጠበቀም። ምክንያቱም የአላህ መልክተኛ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦
“ ኢማሙ ተክቢራ ሲያደርግ ወዲያውኑ ከኋላው ተከትላችሁ ተክቢራ አድርጉ። እርሱ ሩኩዕ ሳያደርግ እናንተ ሩኩዕ አታድርጉ።” ይህ መልክት ከኢማሙ በጣም ወደ ኋላ መዘግየት እንደማይቻል እና የተወገዘ ተግባር መሆኑን ይጠቁማል።
ኢማምን መቅደም ሐራም ሲሆን እኩል ከኢማም ጋር መስገድ የተጠላ እንዲሁም የተከለከለ ተግባር ነው ተብሏል። ወደ ኋላ መዘግየት በትንሹ የተጠላ ተግባር መሆኑን መናገር እንችላለን። ኢማሙን መከተል ደግሞ የመልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ትዕዛዝ የመጣበት ተግባር ነውና (ተወዳጅ ነው።)