ጥያቄ(1): የሰው ልጆች በሙሉ የተፈጠሩበት ዓላማና ግብ ምንድ ነው?
መልስ:
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩኅ በጣም አዛኝ በኾነው። ምስጋና ለአላህ ይገባው። ሰላትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ፤ በቤተሰቦቻቸው እና በሁሉም ባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን ዘንድ ጌታዬን እማፀነዋለሁ። በመቀጠልም ይህን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት አላህ ስለሚፈጥረውና ስለሚደነገግው ጉዳይ አስመልክቶ አጠቃላይ መርሆዎችን ማስታወስ እወዳለሁ። ይኸውም ከአላህ ቃል የተወሰደ መርሆ ነው።
አላህ እንዲህ ይላል፦
“እርሱም ዐዋቂው ጥበበኛው ነው፡፡” [አት ተሕሪም :2]
እንዲህም ይላል፦
“አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡” [አል አሕዛብ:1]
አላህ የሚፈጥረውና የሚደነግገው ለታላቅ ዓላማና ጥበብ መሆኑን የሚያመላክቱ እጅግ በርካታ የቁርኣን አንቀፆች ይገኛሉ። (በሸሪዓዊና በይሁንታዊው ድንጋጌዎቹ) ማንኛውም አላህ በሚፈጥረውና በሚያስገኘው ነገር ላይ ጥበብ ቢኖረው እንጂ አይፈጥርም። እንዳይገኝ በሚያደርገው ነገርም ላይ እንዲሁ። ማንኛውም አላህ የሚደነግጋቸው ህግጋት ጥበብ ያዘሉ ቢሆኑ እንጂ አንድን ነገር አይደነግግም። ዋጂብ አሊያም ሐራም እና ሐላል በሚያደርጋቸው ነገሮች በሙሉ አላህ የተሟላ ጥበብ አለው።
ነገር ግን ሸሪዓዊም ሆነ ከውኒያው (ይሁንታዊ) ድንጋጌዎች በውስጣቸው የሚያካትቷቸው ጥበቦች ለኛ የሚታወቁ አሊያም ከእኛ የተሰወሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ጥበቦች ለሰዎች አላህ በሚያድላቸው የእውቀትና የግንዛቤ መጠን የተነሳ ከፊል ሰዎች ሊያውቁት ከፊሎቹ ደግሞ ላያውቁት ይችላሉ። ይህ ከተረጋገጠ ዘንድ አላህ የሰው ልጅንም ሆነ ጂኖችን የፈጠረው ለትልቅ አላማ እና ምስጉን ለሆነ ግብ ሲሆን እሱም እርሱን በብቸኝነት ለማምለክ ነው እንላለን። አላህ እንዳለው፦
“ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡” [ዛሪያት:56]
እንዲህም ይላል፦
«የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?” [አል ሙእሚኑን :115]
እንዲህም ይላል፦
”ሰው ልቅ ኾኖ መትተውን ይጠረጥራልን?” [አልቂያማ:36]
አላህ የሰው ልጅንም ሆነ ጂኖች እጅግ ለላቀ ጥበብ ነው የፈጠራቸው። እርሱም እርሱን በብቸኝነት ማምለክ መሆኑን የሚያመላክቱ ሌሎችም በርካታ አንቀፆች አሉ። (ዒባዳ)አምልኮት ማለት ሸሪዓዎቹ ላይ በመጣው መሰረት አላህን ከመውደድና ትዕዛዙን በማላቅ ክልከላውን በመራቅ ለአላህ እራስን ዝቅ ማድረግ ማለት ነው።
አላህ እንዲህ ይላል፦
“አላህን ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ አጥሪዎች ኾነው ሊግገዙት እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ ...” [አልበዪናህ:5]
የሰው ልጆችም ሆነ ጂኖች የተፈጠሩት ለነዚህ ጥበቦች ሲባል ነው። ከዚህም በመነሳት ከጌታው ያፈነገጠ እና እርሱን ከማምለክ የተኩራራ ባሮች የተፈጠሩበት አላማ የሆነው ነገር አሽቀንጥሮ እንደወረወረ ይቆጠራል። በዚህም ተግባሩ በአፉ አውጥቶ ባይናገርም እንኳ አላህ ፍጥረታቱን ለጨዋታና ለከንቱ እንደፈጠረ በተዘዋዋሪ እንደመሰከር ይቆጠርበታል። ነገርግን ከጌታው ትዕዛዝ በማፈንገጡና በመኩራቱ የተነሳ በተዘዋዋሪ ይህን መልዕክት ያስፈርዳል።
Share